ቅድመ ውድድር ዝግጅት ፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የፕሪምየር ሊጉ ክለቦች የቅድመ ውድድር ዝግጅታቸውን በተለያዩ የክልል ከተሞች መጀመራቸው ይታወቃል። ሶከር ኢትዮዽያም የክለቦቻችንን የቅድመ ውድድር ዝግጅት እንቅስቃሴዎች የምትቃኝ ሲሆን ዛሬ በአዳማ ከተማ እየተዘጋጀ ከሚገኘው ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ የምንጀምር ይሆናል።


የ29 ጊዜ የኢትዮጵያ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2010 የውድድር ዘመን ለ5ኛ ተከታታይ አመት የፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮን በመሆን አዲስ ታሪክ ለመጻፍ በማለም የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በአዳማ ከተማ ዩኒቲ ሜዳ እያደረገ ይገኛል፡፡

ቅዱስ ጊዮርጊስ በ2009 የውድድር ዘመን ከነበሩ ተጨዋቾች መካከል ከፍሬው ጌታሁን ፣ ተስፋዬ አለባቸው ፣ ምንያህል ተሾመ ፣ ራምኬል ሎክ ፣ አንዳርጋቸው ይላቅ ፣ ፕሪንስ ሰቬሪንሆ ፣ ቡሩኖ ኮኔ እና ያስር ሙገርዋ ጋር ሲለያይ የአንድ አመት ቀሪ ውል ያለው ዘካርያስ ቱጂ ውሉን አፍርሶ ክለቡን ሊለቅ የሚችል ተጫዋች ነው፡፡

ፈረሰኞቹ ለቀጣይ የውድድር ዘመን ተጠናክረው ለመቅረብ ይረዳቸው ዘንድ በሊጉ መልካም አቋማቸውን ያሳዩ ተጨዋቾችን አስፈርመዋል። ለዐለም ብርሃኑ ፣ አብዱልከሪም መሐመድ ፣ ሙሉአለም መስፍን ፣ ታደለ መንገሻ ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ ኢብራሂማ ፎፋና እና አሜ መሐመድም ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው።

ሶከር ኢትዮዽያ ማክሰኞ ጠዋት በዩኒቲ ሜዳ በነበራቸውን ልምምድ ጠንክረው ሲሰሩ የተመለከተች ሲሆን በልምምድ ወቅት 25 ተጨዋቾች ተሳተፈዋል፡፡ ከነበሩት መካከል 20 ተጨዋቾች ነባርና አዲስ ፈራሚ ተጨዋቾች ሲሆኑ የተቀሩት አምስት ተጨዋቾች ከተስፋ ቡድን ያደጉት ሳሙኤል ተስፋዬ ፣ አቤል አንበሴ ፣ ተስፋዬ በቀለ ፣ ዮሐንስ እና ባህሩ ነጋሽ ናቸው፡፡ ተጫዋቾቹ ከ17 አመት በታች ቡድን ጨምሮ ዘንድሮም ከ20 አመት በታች ቡድን ውስጥ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴ ያሳዩ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞ ወደ ዋናው ቡድን ማደጋቸው ተገቢ ሆኖ ሳለ ግብ ጠባቂው ባህሩ ነጋሽ ያለፉትን አራት ተከታታይ አመታት ወደ ዋናው ቡድን ማደግ ቢችልም የመሰለፍ እድል በማጣት ተመልሶ ወደ ተስፋ ቡድን እየወረደ ፣ እየወጣ ይገኛል። ተጨዋቹ በትዕግስት ይህን ያህል ጊዜ መጠበቁ እንዳለ ሆኖ ወደ ዋና ቡድኑ በቋሚነት እስካሁን አለማደጉ አስገራሚ ሆኗል።

ዝግጅት ከጀመሩት 25 ተጫዋቾች በተጨማሪ ሳላዲን ሰኢድ ፣ አብዱልከሪም ኒኪማ ፣ ታደለ መንገሻ (በጉዳት) ፣ አስቻለው ታመነ ፣ ምንተስኖት አዳነ እና ኢብራሂም ፎፋና እስካሁን ዝግጅት ያልጀመሩ ተጫዋቾች ሲሆን ሮበርት ኦዶንካራ በቡድኑ ያለው ቆይታ እስካሁን ያልተረጋገጠ ተጫዋች ነው፡፡

ክለቡ ተጨማሪ ተጫዋቾችን ከውጪ ለማስፈረም የሙከራ እድል እየሰጠ ሲሆን ከተለያዩ የምዕራብ አፍሪካ ሀገራት የአጥቂ መስመር ተጨዋቾች ለሙከራ የመጡ ቢሆንም በነበራቸው ቆይታ በእንቅስቃሴያቸው አሰልጣኞቹን ማሳመን ባለመቻላቸው ወደመጡበት ተመልሰዋል። በዚህ ሁለት ቀናት ውስጥም ሌሎች ለሙከራ የሚመጡ የምዕራብ አፍሪካ ተጨዋቾች መኖራቸውን ለማወቅ ችለናል።

ፈረሰኞቹ በአሁኑ ሰአት በምክትል አሰልጣኞቹ ፋሲል ተካልኝ እና ዘሪሁን ሸንገታ እየተመሩ በቀን ሁለት ጊዜ ጠንካራ የትንፋሽ እና የአካል ብቃት ልምምዶችን እየሰሩ ይገኛሉ። ከማክሰኞው የልምምድ መርሀ ግብር በኋላ ከሶከር ኢትዮዽያ ጋር አጭር ቆይታ ያደረጉት አሰልጣኝ ፋሲል ተካልኝ ዝግጅታቸውን በሚገባ እየሰሩ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡
” በዘንድሮ አመት የነበሩብንን ችግሮች ለማስተካከል ሀገር ውስጥ አሉ የሚባሉ ወሳኝ ተጨዋቾችን አስፈርመናል፡፡ ያም ቢሆን የቀሩን ያላስተካከልናቸው የሚያስፈልጉን ከውጭ የሚመጡ ተጨዋቾች ይኖራሉ። ” ያሉት አሰልጣኝ ፋሲል የመስመር ተጫዋቾች በቡድኑ በብዛት መገኘታቸውን አስመልክቶም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡ “እንደሚታወቀው በአለም እግር ኳስ የመስመር ተጨዋቾች በጣም ተፅዕኖ ፈጣሪዎች ናቸው። ባለፈው አመት የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ እንዳየነው ብዙ ክለቦች የመስመር ተጨዋቾቻቸው ጠንካራ ናቸው። ከዛ ቦታ የሚነሱ ተጫዋቾች የሚፈጥሩትን ጫና እያየን ነው። ከዚህ አንፃር የመስመር ተጨዋቾች ልናበዛ ችለዋል፡፡ ሌላው አንዳንድ ተጨዋቾች በተለያየ ቦታ ይጫወታሉ፡፡ ለምሳሌ ጋዲሳ ከመስመር በተጨማሪ አማካይ መሆን ይችላል ፤ አሜ መሐመድን ስታይ ቀጥተኛ አጥቂ እንዲሁም መስመር ላይ መጫወት ይችላል፡፡ ካለን ልምድ እና የጨዋታ ብዛት እነዚህን ተጫዋቾች ማግኘታችን ይጠቅመናል” ብለዋል።

በዝውውር መስኮቱ ካለፉት ጥቂት አመታት በተለየ ሁኔታ በስፋት የተንቀሳቀሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስብስቡ በአማራጭ የተሞላ እና ሰፊ ሆኗል፡፡ አሰልጣኝ ፋሲልም በየቦታው ለተሰላፊነት ከፍተኛ ፉክክር እንደሚኖር ጠቁመዋል፡፡

“በየቦታቸው መጫወት የሚችሉ ተመጣጣኝ የሆኑ ሁለት ሁለት ተጨዋቾችን ይዘናል። በየክለባቸውም በቋሚነት መጫወት የለመዱ ተጫዋቾች ናቸው። ምን አልባት ባለው ፉክክር ወደ ተጠባባቂ ወንበር መውረዱን መቀበል ሊቸግራቸው ይችላል። ክለባችን ቅዱስ ጊዮርጊስ በአመቱ ብዙ ጨዋታ ስለሚያደርግ እነዚህ ተጨዋቾች ለእያንዳንዱ ቦታ ያስፈልጋሉ፡፡ እኛ ቤት ደግሞ ወቅታዊ ብቃትን መሰረት ያደረገ ምርጫ ነው የሚደረገው፡፡ ከዚህ አንፃር ሁሉንም የሚያሳምን ምርጫ የሚደሰትበት ቡድን ይኖራል ብለን እናስባለን። ካለን ብዙ ጨዋታ አንፃር ሁሉም ተጨዋቾች የመጫወት እድል ይኖራቸዋል” ብለዋል።

እስካሁን ባለው የክለቡ ሁኔታ ጥርት ብሎ መልስ ያላገኘው ቀጣዩ የቅዱስ ጊዮርጊስ ዋና አሰልጣኝ ማን እንደሆነ ሲሆን ባለፉት ቀናት ከአንጎላው ሪክሬቲቮ ሊቦሎ ክለብ የተለያዩት ፖርቱጋላዊው አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ይሆናሉ ተብሎ ይገመታል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *