ሀድያ ሆሳዕና የለቀቁበትን ወሳኝ ተጫዋቾች በመተካት ተጠምዷል

በ2009 የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የውድድር ዘመን ወደ ፕሪምየር ሊጉ ለማደግ እስከመጨረሻው የመለያ ጨዋታ ደርሶ ከመቐለ ከተማ ጋር ባደረገው የመለያ ጨዋታ (Playoff) 2-1 በሆነ ውጤት ተሸንፎ ሳይሳካ የቀረው ሀድያ ሆሳዕና በ2010 ለሚኖረው የከፍተኛ ሊግ ተሳትፎ በአዲስ አሰልጣኝ የሚቀርብ ይሆናል፡፡

አሰልጣኝ እዮብ ማለን ( አሙካቺ ) ዋና አሰልጣኝ አድርጎ የቀጠረው ሀድያ ሆሳዕና በከፍተኛ ሊግ በነበረው ጠንካራ ጉዞ ትልቁን ሚና ሲወጡ የነበሩት አሚኑ ነስሩ ፣ እንዳለ ደባልቄ ፣ ሳምሶን ቆልቻ ፣ አምራላ ደልታታ እና ዱላ ሙላቱን የመሳሰሉ ተጫዋቾችን ማጣቱ ለአሰልጣኝ እዮብ እና ቡድኑ አመቱን ፈታኝ ሊያደርገው እንደሚችል ቢገመትም ክለቡን ጠንካራ ተፎካካሪ አድርጎ በማቅረብ ወደ ፕሪምየር ሊጉ ዳግም ለመመለሰ ለቡድኑ ይመጥናሉ ብለው ያሰቧቸውን ተጨዋቾች በማስፈረም ላይ ይገኛሉ።

ሀድያ ሆሳዕና እስካሁን ባለው የዝውውር እንቅስቃሴ የ7 ተጨዋቾችን ፊርማ ማግኘቱን አረጋግጧል፡፡ ፍሬው ገረመው (ግብ ጠባቂ ፤ ደቡብ ፖሊስ) ፣ መሐመድ ከድር (አማካይ ፤ ስልጤ ወራቤ) ፣ አብነት አባተ (ተከላካይ ፤ ወሎ ኮምቦልቻ) ፤ ሙልቀን ተስፋዬ (አማካይ ፤ ንግድ ባንክ) ፣ ፍሬው አለማየሁ (አማካይ ፤ ሀላባ ከተማ) ፣ ኢብሳ በፍቃዱ (አጥቂ ፤ ነቀምት ከተማ) እና እንዳለ መለዮ (አጥቂ ፤ ወላይታ ድቻ) ክለቡን የተቀላቀሉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡

ክለቡ ሙሉ ለሙሉ ተጨዋቾችን አስፈርሞ እንዳላጠናቀቀ የገለፀ ሲሆን በቀጣዮቹ ቀናትም ተጨማሪ ተጨዋቾችን ወደ ክለቡ እንደሚያመጣ ተገልጿል።

ሀድያ ሆሳዕና የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በቅርብ ቀናት ውስጥ በሆሳዕና ከተማ እንደሚጀምር ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *