መቐለ ከተማ ሶስት የውጭ ዜጋ ተጫዋቾችን አስፈርሟል

አዲሱ የፕሪምየር ሊግ ክለብ መቐለ ከተማ ሁለት ጋናዊያን እና አንድ የኢኳቶርያል ጊኒ ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾችን ማስፈረሙን አስታውቋል፡፡

ኢኳቶሪያል ጊኒያዊው ግብ ጠባቂ ፊሊፔ ኦቮኖ ምባንግ ለመቐለ ከፈረሙት ተጫዋቾች መካከል ነው፡፡ ከ2009 ጀምሮ በዋና ቡድን ደረጃ እየተጫወተ የሚገኘውና ለሀገሩ 10 ጨዋታዎቸች ማድረግ የቻለው ምባንግ በሀገሩ ክለቦች ሶኒ ንጉኤማ እና ዴፖርቲቮ ሞኞሞ ከተጫወተ በኋላ በአመዛኙ በተጠባባቂነት ባሳለፈበት የደቡብ አፍሪካው ኦርላንዶ ፓያሬትስ ለሁለት አመታት ቆይቶ ወደ መጀመርያ ክለቡ ሶኒ ንጉኤማ ተመልሶ የተጠናቀቀውን አመት አሳልፏል፡፡

የተከላካይ አማካይ ስፍራ ተጫዋቹ ሚካኤል አኩፉ ሌላው ለክለቡ የፈረመ ተጫዋች ነው፡፡ ጋና ከሚገኘው የፌይኖርድ አካዳሚ የተገኘው የ29 አመቱ ሚካኤል ባለፉት 10 አመታት በኤሴክ ሚሞሳ ፣ ኤፍ ሲ ፖፓ ፣ አሻንቲ ኮቶኮ እና አልናስር ክለቦች ተጫውቷል፡፡ የጋና ብሔራዊ ቡድን የቻን ስብስብ አባልም ነበር፡፡

ለክለቡ የፈረመው ሶስተኛው ተጫዋች አዳም ማሳላቺ ነው፡፡ የ23 አመቱ ጋናዊ የመሀል ተከላካይ በሀገሩ ክለብ ስቲድፋስት 4 የውድድር ዘመናትን ሲያሳልፍ በሊባኖሱ ኢግታሚ ትሪፖሊ ያለፉትን ሁለት የውድድር ዘመናት አሳልፏል፡፡

መቐለ ከተማ በዝውውር መስኮቱ ሰፊ እነንቅስቃሴ በማድረግ ላይ ሲሆን ከውጪ ዜጎቹ ተጫዋቾች በተጨማሪ በርካታ የሀገር ውሰጥ ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *