የደቡብ ካስትል ዋንጫ የሚጀመርበት ቀን ተራዝሟል

ከመስከረም 6-14 ድረስ በሀዋሳ ከተማ ይደረጋል ተብሎ መርሃ ግብር የወጣለት የደቡብ ክልል ካስትል ዋንጫ መራዘሙ ታውቋል።

የደቡብ እግር ኳስ ፌደሬሽን የፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ወልደሚካኤል መስቀሌ ለሶከር ኢትየጵያ እንደገለፁት ለውድድሩ መራዘም ክለቦች በበአል ምክንያት ቡድናቸውን እንደበተኑ እና በድጋሚ ተሰባስበው ወደ ጨዋታ መንፈስ ለመምጣት ጊዜ እንደሚያስፈልጋቸው በመግለፃቸው ነው ብለዋል።

ለስድስተኛ ጊዜ የሚካሄደው ይህ ውድድር እስካሁን ድረስ ሁሉም በውድድሩ የሚካፈሉ ቡድኖች በግልፅ እንዳልታወቁ የተናገሩት የፅህፈት ቤት ኃላፊው አቶ ወልደሚካኤል ከደቡበ ክልል ተሳታፊዎቹ አርባምንጭ ከተማ ፣ ሀዋሳ ከተማ ፣ ሲዳማ ቡና እና ወላይታ ድቻ ውጪ ከተጋባዥ ክለቦች መካከል በአዲስ አበባ ከተማ ዋንጫ ላይ ይሳተፋል ተብሎ ሲጠበቅ የነበረው ኢትየጵያ ቡና እና የጎንደሩ ፋሲል ከተማ ብቻ በውድድሩ ላይ ተሳታፊ እንደሚሆኑ ማረጋገጫ መስጠታቸው ገልፀዋል። ነገር ግን ውድድሩ መራዘሙን ተከትሎ እነዚህም ተጋባዥ ክለቦች ምን አልባት የሃሳብ ለውጥ አምጥተው በውድድሩ ላይ ላይሳተፉ ይችላሉ የሚሉ መረጃዎች እየተሰሙ ይገኛሉ።

ፌዴሬሽኑ ውድድሩን ከማራዘሙ ውጪ በርግጠኝነት መቼ እንደሚደረግ ያልታወቀ ሲሆን ፌደሬሽኑም በቅርብ ጊዜ ውስጥ መቼ እንደሚጀምር ፣ የተሳታፊ ክለቦችን ስም ዝርዝር እና የእጣ አወጣት ስነ-ስርዓቱ ቀን ይፋ እንደሚያደርግ ተገልጿል።

የአዲስ አበባ እግር ኳስ ፌደሬሽን የሚያዘጋጀው የአዲስ አበባ ዋንጫ(ሲቲ ካፕ) ውድድርም ከመስከረም 20 እስከ ጥቅምት 4 ድረስ እንደሚደረግ ከዚህ በፊት መገለፁም ይታወሳል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *