–
አስተያየት በሳሙኤል የሺዋስ
–
በቅርቡ በኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የፀደቀው የሆነው በአንድ ክለብ ሊኖር የሚገባው የውጭ ተጫዋቾችን ቁጥር የመገደብ ህግ የበዙዎች መነጋገርያ ሆኗል፡፡ ቀጣዩ ፅሁፍ የውጭ ተጫዋቾችን በ3 ብቻ የመገደቡ ህግ አዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች እንዲሁም የመፍትሄ ሃሳቦችን ይዳስሳል፡፡
እንግሊዝ የዘመናዊ እግርኳስ ትውልድ ስፍራ እንደመሆኗ በስፖርቱ ታሪክ በርካታ ፈር ቀዳጅ ሁነቶች ተደርገውባት አልፈዋል። በሃገራት ደረጃ የመጀመሪያው የእግርኳስ ጨዋታ የተደረባትና የመጀመርያውን የእግርኳስ ሊግ የመሰረተችው ሃገር በተጫዋች ዝውውር ታሪክም ፈር ቀዳጅ ነች፡፡ ካናዳዊው የመስመር አማካይ ዋልተር ቦውማን በ1892 በዚሁ የእንግሊዝ ሊግ ለሚጫወተው አክሪንግተን ክለብ በመፈረም የመጀመሪያው ኢንተርናሽናል የእግርኳስ ተጫዋች በመሆን በታሪክ ተመዝግቧል። በወቅቱ ቦውማን በእንግሊዝ የወዳጅነት ጨዋታዎችን ሲያደርግ የነበረው ከሰሜን አሜሪካ የተወጣጣ ቡድን አባል የነበረ ሲሆን በለንደን ለመቅረት የወሰነውም በእግርኳሳዊ ምክንያት ሳይሆን ከእንግሊዛዊት ወጣት ጋር ትዳር በመመስረቱ ነበር።
በዚህ አይነት ሁኔታ የተጀመረው ጥሩ ችሎታ ያላቸውን የውጪ ሃገር ዜጎች የማስፈረም ልምድ በእንግሊዝ፣ ቀጥሎም በሌሎች የአውሮፓ ሃገራት በመስፋፋት እግርኳስን ዓለም አቀፋዊ ገፅታ አላበሰው። ወደ አህጉራችን አፍሪካ ስንመጣ ከሃገሩ በመውጣት መጫወት የቻለ የመጀመሪያው አፍሪካዊ “ናቡከደነፆር” በሚል ቅፅል ስም ይታወቅ የነበረው ግብፃዊ አጥቂ ሁሴን ሄጋዚ ሲሆን እ.ኤ.አ. በ1911 ለፉልሃም በመሰለፍ ከስቶክፖርት ካውንቲ ክለብ ጋር ብቸኛ ጨዋታውን አድርጓል።
የውጪ ተጫዋቾች ገበያ ዘግይቶ ወደሃገራችን ቢደርስም በተለይ ከጥቂት አመታት ወዲህ በገንዘብ መጠንም ሆነ በብዛት እየጨመረ መጥቷል። ከ1990ዎቹ አጋማሽ ጀምሮ በተለይ በቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ መሪነት የተጀመረው ይህ ሂደት በአሁኑ ሰዐት በአብዛኛው የፕሪምየር ሊግ ክለቦች፣ ከዚያም አልፎ በብሔራዊ ሊጉም እየታየ ይገኛል።
የውጪ ሃገር ተጫዋቾች በአንድ ሊግ መበራከት በየትኛውም ሃገር የእግርኳስ እድገት ላይ አዎንታዊ እና አሉታዊ ተፅእኖ እንደሚኖረው ሳይታለም የተፈታ ነው። በዚህ ጉዳይ ዙሪያ ባለድርሻ አካላትን የሚያከራክሩ ነጥቦች በሙሉ በአዎንታዊ እና አሉታዊ ጎኖች መካከል ሚዛናዊነት በመፍጠር ላይ ያተኮሩ ናቸው። በ20ኛው ክፍለዘመን መጀመሪያ በዘረኝነት ተነሳስተው ከዜጎቻቸው ሌላ ማንም በሊጋቸው እንዳይጫወት ካገዱ የአውሮፓ ሃገራት በኋላ የውጪ ተጫዋቾች ከናካቴው አያስፈልጉም የሚል እንቅስቃሴ በዓለም እግርኳስ አልታየም።
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን በቅርቡ ያረቀቀውና ክለቦችን እያወዛገበ የሚገኘው የውጪ ተጫዋቾችን ቁጥር ወደ ሶስት ዝቅ የሚያደርገውን ህግ ሚዛናዊነት ለመመርመር በሊጉ በርካታ የውጪ ሃገር ዜጎች መጫወታቸው የሚኖረው መልካም እና መጥፎ ጎን መመልከት ግድ ይለናል።
የውጪ ተጫዋቾች ጠቀሜታ
1. የሊጉን ደረጃ ያሳድጋል
የውጭ ተጫዋቾች በአንድ ሊግ ውስጥ መበራከት ሊጉን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ተመልካች ፣ ገንዘብ እና ውጤት ሊያስገኝለት ይችላል፡፡
ባሳለፍነው የውድድር ዘመን በተመልካች ብዛት እና በሚያንቀሳቅሰው የገንዘብ መጠን አቻ በማይገኝለት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ ከሚጫወቱ ተጫዋቾች ውስጥ 65% እንግሊዛውያን አልነበሩም፤ ይህ ቁጥር የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግን ከቆጵሮስ ሊግ በመቀጠል በዓለማችን ትልቁ የውጪ ተጫዋቾች መናኸሪያ ያደርገዋል። ሊጉ እንደ አዲስ በተዋቀረበት የ1992/93 የውድድር ዘመን በ22ቱ ተሳታፊ ክለቦች ውስጥ የሚገኙ እንግሊዛዊ ያልሆኑ ተጫዋቾች ቁጥር ድምር 11 ነበረ። በእነዚህ 22 ዓመታት ውስጥ የተፈጠሩ ለውጦችን በመመርመር የውጪ ተጫዋቾች የነበራቸውን ሚና መገንዘብ እንችላለን።
ባለፉት 22 ዓመታት የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በፋይናንስ አቅም እና በተመልካች ብዛት በፍጥነት በማደግ በብዙዎች ዕይታ የዓለማችን ምርጡ ሊግ ለመሆን ችሏል። የውጪ ሃገር ተጫዋቾች መበራከት ለዚህ መሳካት የተጫወተው ሚናም በቀላሉ የሚታይ አይደለም።
በአንድ ሊግ የተለያዩ ሃገራት ዜጎች የሆኑ በርካታ ተጫዋቾች መጫወት በቻሉ ቁጥር የሊጉ ዓለምዓቀፍ ተከታታይ (International Audience) ቁጥር ይጨምራል። በቅርብ ጊዜያት የሃገራችን ተጫዋቾች በግብፅ እና ደቡብ አፍሪካ ሊጎች መጫወት መጀመራቸውን ተከትሎ የሁለቱን ሃገራት ውድድሮች መመልከት የጀመረው ኳስ ወዳድ ኢትዮጵያዊ ለዚህ ግልፅ ማሳያ ነው። የአንድ ሊግ ተፈላጊነት በጨመረ ቁጥር ደግሞ ከቴሌቪዥን እና ስፖንሰር ሺፕ የሚያገኘው ገቢ በዚያው ልክ እየጨመረ ይመጣል። የእንግሊዝ ፕሪምየር ሊግ በ1992/93 በ304 ሚልየን ፓውንድ ከቢቢሲ እና ቢኤስቢ ጋር የቴሌቪዥን ብሮድካስቲንግ ውል ተፈራርሞ የነበረ ሲሆን ይህም በ2013 (ከስካይ ስፖርት እና ቢቲ ላይቭ ጋር) ወደ 3 ቢሊዮን ፓውንድ አድጓል። በ1992/93 ይፋዊ ስፖንሰር ያልነበረው ሊጉ በአሁኑ ሰዓት ከባርክሌይስ ባንክ ጋር በዓመት 120 ሚልየን ፓውንድ የሚያስገኝለትን ስምምነት መፍጠሩ የደረሰበትን የፋይናንስ ጥንካሬ ያሳያል።
አፍሪካን እንመልከት። በእግርኳስ ደረጃም ሆነ በሊጓ ጥንካሬ ከእኛ በማትሻለው ጎረቤታችን ኬንያ በርካታ የውጪ ተጫዋቾች ይገኛሉ። በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት (በተለይም ዩጋንዳ፣ ብሩንዲ እና ሩዋንዳ) የሚገኙ ተጫዋቾች በብዛት በኬንያ መጫወታቸው ሊጉ በእነዚህ ሃገራት ተከታታዮችን እንዲያፈራ አስችሎታል። ይህም ከደቡብ አፍሪካው የቴሌቪዥን ጣቢያ ሱፐርስፖርት ጋር የ5.5 ሚልየን ዶላር የብሮድካስት ስምምነት እንዲፈራረም ትልቅ ድርሻ ነበረው። የቢራ አምራች ፋብሪካው ተስከርም የሊጉ የስያሜ ስፖንሰር ለመሆን 1.5 ሚሊየን ዶላር መክፈል ግድ ሆኖበታል።
2. ተጫዋቾቻችን ልምድ እንዲያገኙ ይረዳል
ሌላ በፍፁም መዘንጋት የሌለበት ነገር ደግሞ ተጫዋቾቻችን ከሌሎች ሃገር ተጫዋቾች ጋር አብረው በመጫወታቸው ማግኘት የሚችሉት ልምድ እና ክህሎት ነው። በ1995 ፍራንሲስ አሙላኩ ቅዱስ ጊዮርጊስን ሲቀላቀል ለብቻው ተነጥሎ የሚታይ ተጫዋች ነበር። ኬንያዊው በመጀመርያ የውድድር ዘመኑ ከርቀት አክርሮ የሚመታቸው ኢላማቸውን የጠበቁ የግብ ሙከራዎች፣ የአካል ብቃቱ ፣ የጉልበት አጠቃቀሙ ፣ ፍጥነቱ እና የቦታ አያያዙ (በወቅቱ) በኛ ሃገር ተጫዋቾች ላይ የማይታይ ነበር፤ የጊዮርጊሱ ራሺድ ያኪኒ እስከመባልም ደርሶ ነበር። የሃገራችን አጥቂዎች ከሱ አይነት ተጫዋች ብዙ ነገር ሊማሩ ይችላሉ፣ ተከላካዮቻችን ከሱ አይነት አጥቂ የሚደርስባቸውን ጥቃት ለመመከት ጠንክረው ሊሰሩና ብቃታቸውን ሊያጎለብቱ ይችላሉ። የኤሌክትሪኩ ቶምፕሰን አይካጃ ሳሙኤል ፣ የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አብርሃም ኩዲሞር ፣ ኢሳኒ ባጆፔ ፣ ዳንኤል ኦፓኩ ፣ ፕሪንስ ፣ ኡቼ ፤ የደደቢቶቹ ሳሙኤል ሳኑሚ እና ጂብሪል አህመድ በእርግጥም ከሊጋችን ኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች የተሻሉ በመሆናቸው የቡድኖቻችንን ብሎም የሊጋችንን ደረጃ የማሳደጉ አቅም ነበራቸው/አላቸው። ባለፉት 20 አመታት በዴኒስ ኦኒያንጎ ደረጃ ኢትዮጵያ ውስጥ የታየ ሌላ ግብ ጠባቂ ማግኘት በፍፁም የማይቻል ነው። ለ4 ተከታታይ አመታት የሊጉ ኮከብ ግብ ጠባቂ የሆነው ሮበርት ኦዶንግካራ ብቃትም ከኢትዮጵያውያን የተሻለ በመሆኑ ከአትዮጵያውያን በላይ የቡድኖቻችንን እና የሊጉን ደረጃ የማሻሻል ብቃት አላቸው።
ከላይ እንደተጠቀሱት አይነት ተጫዋቾች በቡድን ውስጥ መኖር ከሃገር አልፎ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ተወዳዳሪ ለመሆን ያስችላል። እንዳለመታደል ሆኖ የጠቀስናቸው ተጫዋቾች በሊጋችን ከተጫወቱ አጠቃላይ የውጭ ተጫዋቾች 10 በመቶ የማይሞላ ድርሻን ብቻ የሚይዙ መሆናቸው ነው።
3. የአለም አቀፍ አሰራር ልምዳችንን ያጎለብታል
የውጭ ተጫዋቾችን ለማምጣት ክለቦች ከአለም አቀፍ ወኪሎች እና ክለቦች ጋር መነጋገራቸው አይቀርም። የመደራደር ብቃት የሚጎድላቸው ክለቦችም በጊዜ ሂደት ወደ ዘመናዊ አሰራር ሊያመሩ ይችላሉ። ይህም ክለቦቻችን አለም አቀፍ ግንኙነታቸውን ሊያዳብርላቸው ይችላል። ከረጅም ጊዜ በኋላ የክለቦቻችን እና ተጫዋቾቻችን ደረጃ ቢያድግ ከውጭ ክለቦች ጋር ያላቸው ግንኙነት የሚጨምር በመሆኑ የተደራዳሪነት አቅማቸውን እና ልምዳቸውን ያሳድግላቸዋል።
የውጪ ተጫዋቾች መበራከት አሉታዊ ጎን
1. በኢትዮጵያ የሚጫወቱ የውጪ ተጫዋቾች የወረደ ደረጃ
ጥሩ ብቃት ያላቸው የውጪ ተጫዋቾች የሉጉን ደረጃ ለማሳደግ አቅሙ እንዳላቸው ሁሉ በዚያው ልክ አቋማቸው የወረደ ተጫዋቾች የሊጉን ደረጃ ያወርዱታል።
በአፍሪካ ያለው ደካማ የሳተላይት ቴክኖሎጂ የአፍሪካን የውስጥ ሊጎች ለመከታተል አመቺ አይደለም። የተሻለ የቴሌቪዝን ሽፋን የሚያገኙት ደግሞ ደረጃቸው ከፍ ያሉ ሊጎች ናቸው። የኢትዮጵያ ክለቦች ደግሞ በቻምፒዮስ ሊግ እና በትልልቅ ሊጎች የሚመለከቷቸውን ተጫዋቾች ለማዘዋወር የገንዘብም ሆነ የሳቢነት አቅም የላቸውም። በዚህም ምክንያት ከኢትዮጵያ ብዙም የማይሻል ደረጃ ባላቸው ሃገራት ተጫዋቾች አልያም በእግርኳሱ ትልቅ ስም ባላቸው ሃገራት ውስጥ የሚጫወቱ ነገር ግን ደረጃቸው የወረዱ ተጫዋቾች ላይ ትኩረት ያደርጋሉ።
በኢትዮጵያ በተገቢው ሁኔታ በመልማይ/አሰልጣኝ ታይቶ እና በውድድሮች ያሳየው አቋም ተገምግሞ የመጣ ተጫዋች መኖሩ ጥያቄ ያስነሳል። ክለቦች የውጭ ተጫዋቾችን የሚያስፈርሙበት ብቸኛ መንገድ የሙከራ እድል በመስጠት በመሆኑ የተጫዋቾችን ትክክለኛ ችሎታ፣ የአጨዋወት ባህርይ፣ ተሰጥኦ እና ያለፉ ሪኮርዶችን መረዳትና አገናዝቦ ማስፈረም አስቸጋሪ ነው። በኢትዮጵያ ሊግ ብቃታቸው ጥያቄ የሚያጭሩ በርካታ የውጭ ሃገራት ተጫዋቾችን የተመከለትንበት ምክንያትም ተጫዋቾቹ በአንድ ሳምንት የሙከራ ጊዜ በሚያሳዩት ብቃት ተማምነን የማስፈረማችን ጣጣ ነው።
ካሜሩናዊው ማጆ ቤንትራንድ ለኢትዮጵያ ቡና በፈረመበት ወቅት ስካይ ስፖርት ከተሰኘ የሃገራችን ጋዜጣ ጋር ባደረገው ቃለምልልስ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ ተጫዋቾች ደረጃ ከካሜሩን እጅግ ዝቅተኛ ሊጎች እንደማይሻል በምፀት መልክ ተናግሮ ነበር። ማጆ ከካሜሩን ትልቁ ሊግ የመጣ በመሆኑና ካሜሩንም በአፍሪካ እግርኳስ መልካም ስም ያላት ሃገር በመሆኗ (በተለይ ከ10 አመት በፊት) በኢትዮጵያ አቻ የማይገኝለት ተጫዋች ይሆናል ተብሎ ተጠብቆም ነበር። ነገር ግን አብዛኛዎቹ የቡና ደጋፊዎች ችሎታውን ሊያስታውሱ ቀርቶ ማጆ ቤርትራንድ የሚባል ተጫዋች ቢጫውን ማልያ መልበሱንም አያውቁም። እንደውም ሊታወስ የሚችለው በ1996 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ባደረገው የመጀመርያ ጨዋታው በቀይ ካርድ የወጣበት ክስተት ብቻ ነው። ጂሚ ጋቴቴን ልናስታውሰው የምንችለው ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአል ሜሪክ ጋር ባደረገው የቻምፒዮንስ ሊግ ጨዋታ ላይ ባሳየው እጅግ የወረደ ብቃት ብቻ ነው። ካሲቡላ ሃሪንግተን የቅዱስ ጊዮርጊስን በር ለ2 አመታት ቢጠብቅም አንድ ግብ ጠባቂ ሊኖሩት የሚገቡት መሰረታዊ ክህሎቶች እንኳ አልነበሩትም። ጃኮብ (ደደቢት/ግብ ጠባቂ)፣ ኢቮ ማፑንዳ (ቅዱስ ጊዮርጊስ/ግብ ጠባቂ)፣ ፊቨርሰማ ኔልሰን (ቡና፣ ወልቂጤ ከነማ/ግብ ጠባቂ)፣ ዛብሎን አማናካ (ቅዱስ ጊዮርጊስ/አጥቂ)፣ ጆርጅ ኦውዲ (ቅዱስ ጊዮርጊስ/አጥቂ)፣ አዩላ ሞሰስ (ኒያላ፣ ኤሌክትሪክ/አማካይ)፣ ኦሊቨር ዋረን (ቡና/ተከላካይ)፣ ቶኒ ቶኒ (ቡና/አማካይ)፣ ቤንዊት ፊልስ (ባህርዳር ዩኒቨርሲቲ/አማካይ)፣ ጄምስ ኦሞንዲ (ቅዱስ ጊዮርጊስ/አጥቂ) እና የመሳሰሉት ተጫዋቾች ደረጃ በውጪ ተጫዋቾች ላይ ያለንን ከልክ ያለፈ እምነት ጥያቄ ውስጥ የሚከቱ ነበሩ።
2. ገንዘብ
የክለቦቻችን አመታዊ በጀት ከፍተኛ ቢሆንም የሚመድቡትን ገንዘብ በተገቢው ሁኔታ አውለውታል ለማለት አያስደፍርም። የተንዛዛ የውድድር ካሌንደሩ በራሱ ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣ ቢሆንም ክለቦቻችን የጠራ የዝውውር ፖሊሲ አልባ በመሆናቸው የሚመድቡትን በጀት በአግባቡ እንዳይጠቀሙ ያደርጋቸዋል። በዚህም ምክንያት ደረጃው ከፍ ያለ የውጭ ተጫዋች እንዳያስፈርሙ ያግዳቸዋል። ክለቦቻችን በአፍሪካ ደረጃ ለመፎካከር ከታላላቅና ሃብታም ክለቦች ጋር ተፎካክረው ምርጥ ተጫዋቾችን ማስፈረም ይጠበቅባቸዋል። በአፍሪካ ምርጥ የሚባሉ ተጫዋቾችን ለማምጣት ደግሞ ከፍተኛ ወጪ ይጠይቃል። እንደ ምሳሌ የሱዳኖቹ አል ሜሪክ እና አል ሂላል በአፍሪካ ውጤታማ ከሚባሉ ክለቦች ይጠቀሳሉ። እነዚህ ክለቦች በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ የተቻላቸው ባላቸው ሱዳናዊ ተጫዋቾች ጥራት ሳይሆን ባላቸው ከፍተኛ የገንዘብ አቅም በአፍሪካ አሉ የሚባሉ ተጫዋቾችን ማምጣት በመቻላቸው ነው። አል ሂላል ከጥቂት አመታት በፊት የ2008 የአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ኮከብ ግብ አግቢ የነበረውን ናይጄሪያዊ አማካይ ስቴፌን ዎርጉ የአፍሪካ ሪከርድ የሆነ 3 ሚሊዮን ዶላር በማውጣት ማስፈረሙ ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።
3. ብሄራዊ ቡድኑ ላይ ተፅእኖ ይኖረዋል
የውጪ ተጫዋቾች መበራከት ሃገር በቀል ተጫዋቾች በቂ ትኩረት እና ዕድል እንዳያገኙ ዕንቅፋት በመሆን በብሔራዊ ቡድኑ ላይ ተፅእኖ ሊያሳድር ይችላል የሚለው የበርካታ ስፖርት ባለሙያዎች ስጋት ነው። ሃገራት በሊጋቸው መጫወት የሚችሉ የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር ላይ ገደብ እንዲያደርጉ የሚያስገድዳቸው ዋነው ነገርም ይህ ስጋት ነው። እግርኳስ ተጫዋቾች በቴክኒክ፣ በታክቲክ እንዲሁም በስነልቦናው ረገድ እየዳበሩ እንዲመጡ በተደጋጋሚ የመጫወት ዕድል ሊሰጣቸው ይገባል። ቋሚ ተሰላፊነቱን በውጪ ዜጋ ተጫዋቾች የተነጠቁ የሃገር ልጆች ይህንን ዕድል ማግኘት ባለመቻላቸው ብሔራዊ ቡድኑ የልምድ እና የተጫዋቾች እጥረት ሊገጥመው ይችላል። ከዚህም በተጨማሪ ክለቦች ከአካዳሚዎች እና ወጣት ቡድኖች ተጫዋቾችን የማሳደግ ባህል እንዳይኖራቸው ሊያደርግ ይችላል።
ምን ይሻላል?
የውጪ ሃገር ተጫዋቾችን ቁጥር ለመገደብ እና ክለቦች በሃገር በቀል ተጫዋቾች እንዲጠቀሙ ለማበረታታት የተለያዩ ሃገራት የተለያዩ ህጎችን በማውጣት ይጠቀማሉ። ከዚህ በመቀጠል እነዚህ ሃገራት መፍትሄ ይሆነኛል ብለው የተገበሯቸውን አሠራሮች እንቃኛለን።
1. የሃገር ውስጥ ተጫዋቾችን ዝቅተኛ ቁጥር ማስቀመጥ
በርካታ የአውሮፓ ሃገራት የውጪ ተጫዋቾች በሊጋቸው ላይ ያለውን አዎንታዊ ተፅእኖ ላለማጣት ሲሉ የቁጥር ገደብ ለማስቀመጥ አይፈልጉም። ከዚህ ይልቅ በአንድ ክለብ መኖር የሚጠበቅበትን ዝቅተኛ ሃገር በቀል ተጫዋቾች ቁጥር ማስቀመጥ ይቀናቸዋል። በእንግሊዝ አንድ ክለብ ከሚያስመዘግባቸው 25 ተጫዋቾች ውስጥ 8ቱ በሃገር ውስጥ ያደጉ (የእንግሊዝ ዜጎች ወይንም በእንግሊዝ አካዳሚዎች ከ3 ዓመት በላይ የተጫወቱ የሌላ ሃገር ዜጎች) መሆን ይኖርባቸዋል። የእንግሊዝ እግርኳስ ማህበር ሊቀመንበር ግሬግ ዳይክ ይህንን ቁጥር ወደ 12 ለማሳደግ ሃሳብ እንዳላቸው ያሳወቁ ሲሆን በተጨማሪም የውጪ ተጫዋቾች የእንግሊዝ የስራ ፈቃድ ለማግኘት የሚኖርባቸውን ውጣ ውረድ በመጨመር ክለቦች እንግሊዛዊ ተጫዋቾች ላይ እንዲያተኩሩ ግፊት ለማድረግ አቅደዋል።
2. የውጪ ተጫዋቾችን ደሞዝ ከፍ በማድረግ የክለቦችን የፋይናንስ አቅም መፈታተን
በሆላንድ ተግባራዊ እየተደረገ ባለው አሠራር ክለቦች የውጪ ሃገር ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾቻቸውን ከሆላንዳዊ ተጫዋቾቻቸው በ1.5 ጊዜ የሚበልጥ ገንዘብ መክፈል ይኖርባቸዋል። በአሁኑ ወቅት የአንድ ደች ተጫዋች አማካይ ዓመታዊ ደሞዝ 233 ሺህ ዩሮ ሲሆን ክለቦች የሌላ ሃገር ዜጋ ማስፈረም ከፈለጉ ቢያንስ በዓመት 350 ሺህ ዩሮ መክፈል ግድ ይላቸዋል። በኢትዮጵያ የውጪ ሃገር ዜጎች አሁንም ከኢትዮጵያውያን ተጫዋቾች በእጅጉ የሚልቅ ገንዘብ የሚከፈላቸው ከመሆኑ አንፃር ይህን ህግ መተግበር ምንም ፋይዳ አይኖረውም።
3. ክለቦች የውጪ ተጫዋች ሲያስፈርሙ ለአካዳሚ የሚውል ገንዘብ እንዲከፍሉ ማድረግ
አፍሪካዊቷ ታንዛኒያ ከመጪው ዓመት ጀምሮ በምትተገብረው በዚህ ህግ ክለቦች ለሚያስፈርሙት አንድ የውጪ ተጫዋች ለወጣት አካዳሚው ግብአት የሚሆን 2ሺህ ዶላር ለፌዴሬሽኑ ገቢ ያደርጋሉ። ይህ አሠራር ለሙስና የተጋለጠ ቢሆንም ክለቦች ወደ ሃገራቸው ተጫዋቾች እንዲመለከቱ ሊያስገድድ ይችላል።
4. ሃገሪቱ እጥረት ባለባት የጨዋታ ስፍራዎች ላይ እገዳ ማድረግ
የግብፅ ሊግ ክለቦች እያንዳንዳቸው 3 የውጪ ተጫዋቾችን ብቻ እንዲይዙ ይፈቀድላቸዋል፤ እነዚህ ተጫዋቾች ግን ግብ ጠባቂ መሆን የለባቸውም። ይህ ህግ የግብፅ ብሔራዊ ቡድን አጋጥሞት የነበረውን ኢሳም ኤል ሃድሪን የሚተካ ጥሩ ብቃት ያለው ግብ ጠባቂ እጥረት ለመፍታት በማሰብ እ.ኤ.አ. በ2009 የፀደቀ ነበር። ግብፅ በዚህ አሠራር ስር በአፍሪካ እግርኳስ ውድድሮች ውጤታማ የሆኑ ግብ ጠባቂዎችን ማፍራት ችላለች። በተመሳሳይ የግብ ጠባቂ ችግር ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ እግርኳስ አማራጭ የሚሆን መንገድ ይመስላል።
5. በተመሳሳይ ሰዓት መጫወት የሚችሉ የውጪ ተጫዋቾችን ቁጥር መወሰን
የውጪ ተጫዋቾች ቁጥር ገደብ ባላቸውም ሆነ በሌላቸው ሀገራት ይህንን ህግ ተግባራዊ ያደርጋሉ። በሩስያ ክለቦች የፈለጉትን ያህል የውጪ ተጫዋቾችን የማስፈረም መብት ቢኖራቸውም በአንድ ጨዋታ የመጀመሪያ 11 አሠላለፍ ውስጥ መግባት የሚችሉት ግን 7ቱ ብቻ ናቸው። በተመሳሳይ በደቡብ ኮርያ ክለቦች በጨዋታ ቀን በሚመርጡት 18 አባላት ባለው ቡድን ውስጥ 4 የውጪ ተጫዋቾችን ማካተት ቢችሉም 3ቱ ብቻ በጨዋታው መሰለፍ ይችላሉ።
ይህ መንገድ በሃገራችን ሊተገበር ባለው ህግ ላይ ያለውን ውዝግብ የመፍታት አቅም አለው። ቅዱስ ጊዮርጊስ ክለብ በአህጉራዊ ውድድሮች ላይ ጠንካራ አቋም ይዞ ለመቅረብ 5 የውጪ ተጫዋቾች ሊኖሩኝ ይገባል በሚል የህጉን መፅደቅ በፅኑ ይቃወማል። ይህ አሠራር በሃገራችን የሚተገበር ከሆነ ክለቡ በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ እና ጥሎ ማለፍ ውድድር ላይ በአንድ ጊዜ 3 የውጪ ዜጎችን ብቻ ማሰለፍ የሚችል ቢሆንም በአፍሪካ ውድድሮች ግን ምንም አይነት ገደብ አይኖርበትም።
አዲሱ ህግ ከፀደቀ ምን መደረግ ይኖርበታል?
የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የውጪ ሃገር ዜጋ የሆኑ ተጫዋቾችን ቁጥር ወደ 3 ዝቅ የሚያደርገውን አዲስ ህግ ካፀደቀ ክለቦች የተጫዋች ምልመላ ሂደታቸው ላይ ለውጥ ማድረግ ግድ ይላቸዋል።
ከብዛት ይልቅ ጥራትን ማስቀደም
ክለቦቻችን በርካታ የውጭ ተጫዋቾች በማምጣት ብቻ ውጤታማ መሆን እንደሚቻል የሚያስቡበት መንገድ የተሳሳተ ነው። አለም ላይ በስኬታማነታቸው የምናውቃቸው ክለቦች የስኬት ምስጢር ለበርካታ ተጫዋቾች ከፍተኛ ገንዘብ በማፍሰስ ብቻ አይደለም፤ በቡድኑ ውስጥ የሚገኙ ተጫዋቾችን ብቃት በማሻሻልና የቡድኑን ደረጃ ከፍ የሚያደርጉ ወይም ክፍተታቸውን እንደሚደፍን የሚተማመኑባቸውን ተጫዋቾች በቡድናቸው ላይ በመጨመር እንጂ።
ቡድኖች ከውጪ ተጫዋች ሲያስመጡ የቡድን አባል ከማድረግ በዘለለ የቡድኑን ደረጃ ከፍ ሊያደርጉለት ይገባል። ለምሳሌ በኤሌክትሪክ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን 6 የውጪ ተጫዋቾችን ተጠቅሟል። አዎይኒ ሚካኤል፣ ሲሴ ሃሰን፣ ማንኮ ካዌሳ፣ ዊልያም ኤሳድጆ፣ ሳውረን ኦልሪሽ፣ ፒትር ኑዋድኬን እና ሳሙኤል ጋንሳህ (አንድም ጨዋታ ሳይጫወት ወደ ሃገሩ ሄዷል) የያዘው ኤሌክትሪክ ከመውረድ የተረፈው ለጥቂት ነበር። በተመሳሳይ ወልድያ 2፣ ሙገር ሲሚንቶ 1 የውጪ ተጫዋች ቢጠቀሙም ከመውረድ አልተረፉም። ወላይታ ድቻ፣ መከላከያ እና አርባምንጭ ከነማ አንድም የውጭ ተጫዋች ሳይጠቀሙ የመውረድ ስጋት እንኳ ሳያንዛብብባቸው የውድድር ዘመናቸውን አጠናቀዋል። እዚህ ጋር የውጭ ተጫዋቾች ጠቀሜታ የቱ ጋር እደሆነ ጥያቄ ያጭራል። በሊጉ አንዳንድ የውጪ ተጫዋቾች አመቱን ያሳለፉት በተጠባባቂ ወንበር ላይ መሆኑም ሌላ ጥያቄ ያጭራል። አገልግሎት ለማይሰጥ ተጫዋች ከፍተኛ ወጪ ማውጣት ከኢትዮጵያ ውጪ በየትም አልተለመደም።
ብልጠትን በመጠቀም ጥራትን ማምጣት
በአንድ የዝውውር መስኮት 3 መካከለኛ ደረዳ ያላቸውን የፊት አጥቂዎችን በአንድ ጊዜ ስላስፈረምን ብቻ ቡድኑ የግብ መጠኑ ይጨምራል ብለን ልንናገር አንችልም። ከሶስት መካከለኛ አጥቂዎች ይልቅ አንድ ግብ አዳኝነቱ የተመሰከረለትን አጥቂ በማስፈረም በቡድኑ የሚገኙት ሌሎች አጥቂዎችን ብቃት በማሻሻል ግን ከመጀመርያው በተሻለ ከቡድናችን በርካታ ጎሎች ልናገኝ እንችላለን። ለምሳሌ 5 ተጫዋቾችን ለእያንዳንዳቸው 50 ሺህ ዶላር ከፍለን ብናመጣ አጠቃላይ የፊርማ ወጪ 250 ሺህ ዶላር (5 ሚልዮን ብር) ይሆናል። በዚህ 250 ሺህ ዶላር ከመጀመርያዎቹ በእጥፍ የተሻሉ ሁለት ተጫዋቾችን ለእያንዳንዳቸው 100 ሺህ ዶላር ከፍለን ማስፈረምና በቀሪው 50 ሺህ ዶላር ደረጃው ያነሰ ተጫዋች ማስፈረም እንችላለን። አምስት ምንም ከማይፈይዱ ተጫዋቾች ይልቅ 2 የተሻለ ብቃት ያላቸውን ተጫዋቾችን ማስፈረም ለቡድን ስብስቡ የተሻለ ጥራት ይጨምራል።
በአፍሪካ ቻምፒዮንስ ሊግ ምድብ ሀ 18 የውጪ ተጫዋቾችን የያዘውን የኮንጎ ክለብ ቲፒ ማዜምቤ 3 የውጪ ተጫዋች ብቻ የሚፈቀድላቸው የሞሮኮው ማግሬብ ቴቱዋን እና የግብፁ ስሞሃ እየፈተኑት ይገኛሉ። ይህም በቂ ገንዘብ በማውጣት በአፍሪካ ክለቦች ውድድር ልምድ ያላቸውን 3 ጥሩ ተጫዋቾች በማስፈረም በቻምፒዮንስ ሊጉ ተወዳዳሪ መሆን እንደሚቻል ያሳየናል።