ዳሽን ቢራ አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ ‹‹ ዳኜ ››ን የክለቡ ዋና አሰልጣኝ አድርጎ መቅጠሩ ታውቋል፡፡ በአምናው የዝውውር መስኮት ዳሽን እና አሰልጣኙ ከስምምነት ደርሰው ከሃዋሳ ከነማ ጋር በነበራቸው ውል ምክንያት ሳይሳካ ቢቀርም አሁን ከክለብ ነፃ የሆኑት አሰልጣኝ ታረቀኝ እና ዳሽን ቢራ በድጋሚ ተገናኝተዋል፡፡
አሰልጣኙ ለ2 አመት የሚቆይ ኮንትራት እደፈረሙ የተነገረ ሲሆን የገንዘብ መጠኑ በይፋ ባይታወቅም ዳሽን ለአሰልጣኙ 1 ሚልዮን ብር ወጪ እንዳደረገ ከክለቡ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡ አሰልጣኙ በይፋ ስራቸውን ከጀመሩ ሰንበትበት ያሉ ሲሆን አዳዲስ ተጫዋቾችን በመመልመልና ኮንትራት በማራዘም ላይም ተጠምደዋል፡፡ ረዳታቸውን ራሳቸው እንዲመርጡም ክለቡ እንደወሰነ ተነግሯል፡፡
የታረቀኝ ረዳት ሆኖ የሚሰራው አሰልጣኝ ማንነት እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን እንደ ዛሬ ጠዋቱ የፕላኔት ስፖርት የሬድዮ ፕሮግራም ዘገባ ከሆነ ቡድኑን በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን መጨረሻ የመሩት አሰልጣኝ ካሊድ መሃመድ ከክለቡ ጋር አይቀጥሉም፡፡
የቀድሞው የሃዋሳ ከነማ ተጫዋች የሆኑት አሰልጣኝ ታረቀኝ አሰፋ በአሰልጣኝነት ከ10 አመት በላይ የቆዩ ሲሆን ከኒያላ ከፕሪሚየር ሊጉ ወርደዋል ፤ ሲዳማ ቡናን ይዘው ደግሞ ቡድኑን ወደ ፕሪሚየር ሊግ አሳድገውታል፡፡ በኢትዮጵያ ብሄራዊ ቡድን የሰውነት ቢሻው ረዳት ሆነው የሰሩ ሲሆን ሰበታ ከነማ እና ሀዋሳ ከነማ ሌሎች ያሰለጠኗቸው ክለቦች ናቸው፡፡
የዳሽን ቢራ ደጋፊዎች በአሰልጣኙ ቅጥር ደስተኛ እንዳልሆኑና ተቃውሟቸውን በተለያየ መንገድ እያሰሙ መሆኑም ተነግሯል፡፡