​የኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት ክለብ ባለቤትነት ወደ ኢ/ኮ/ስ/ኮ ተሸጋገረ

የከፍተኛ ሊጉ ክለብ ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት ባለቤትነት ወደ ኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን (ኢኮስኮ) መለወጡን ክለቡ ለሶከር ኢትዮጵያ አስታውቋል፡፡
ያለፉትን 11 አመታት በኢትዮጵያ እግርኳስ ላይ የቆየውና በ2000 እና 2005 የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ተሳታፊ መሆን ችሎ የነበረው ኢትዮጵያ ውሀ ስፖርት በኢትዮጵያ ውሀ ስራዎች ኮንስትራክሽን ድርጅት ባለቤትነት ሲተዳደር የቆየ ሲሆን ከዘንድሮው የውድድር ዘመን በኋላ ግን ባለቤትነቱን ሙሉ ለሙሉ ለኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ስራዎች ኮርፖሬሽን አዘዋውሮታል፡፡ ስያሜውም በአዲሱ ባለቤት ድርጅት ተቀይሯል፡፡

ክለቡ በአዲሱ ድርጅት መተዳደሩን ተከትሎ የአሰልጣኝ ለውጥ ባያደርግም  የቡድን ስብስቡ ላይ ስር ነቀል ለውጥ በማድረግ 18 ተጫዋቾችን ማስፈረም ችሏል፡፡ በፕሪምየር ሊጉ ልምድ ያላቸው ተጫዋቾች እና በከፍተኛ ሊጉ ጥሩ አመት ማሳለፍ የቻሉ ተጫዋቾችንም ሰብስቧል፡፡ (የጫዋቾችን ዝርዝር በሌላ ዘገባ ይዘን እንመለሳለን)

በኢትዮጵያ እግርኳስ ከዚህ ቀደም እንደ ኒያላ (ብሔራዊ ትምባሆ ድርጅት) እና ሴንትራል ጤና ኮሌጅ የመሳሰሉ ክለቦች ቡድኖቻቸውን ወደ ሌሎች ድርጅቶች ማዞራቸው የሚታወስ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *