“የቅዱስ ጊዮርጊስ አካዳሚ አወቃቀር ከስፔን ፕሮፌሽናል ክለቦች ጋር ተመሳሳይ ይሆናል” ዴቪድ ሎፔዝ እና ሁሊዮ ፓዞ

የስፔኖቹ ሶክስና የእግርኳስ ማዕከል እና ኢ ፎር ኢ የኢንቨስትመን አማካሪ ድርጅት ከኢትዮጵያው ቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ማህበር ያስገነባውን የይድነቃቸው ተሰማ የእግርኳስ አካዳሚን ለማስተዳደር የአምስት አመት ውል ሐሙስ መፈፀማቸው ይታወሳል፡፡ የሶክስና ምክትል ፕሬዝደንት ዴቪድ ሎፔዝ እና የኢ ፎር ኢ ማኔጂንግ ፓርትነር ሁሊዮ ፓዞ ስለውል እና ተያያዥ ጉዳች ላይ ለጋዜጠኞች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ስለውሉ አጠቃላይ ሁኔታ

ዴቪድ ሎፔዝ፡ የተፈራረምነው የአምስት ዓመት ውል ሲሆን ከህዳር 1 (በፈረንጆቹ) ጀምሮ ነው ተፈፃሚ የሚሆነው፡፡ አምስት አሰልጣኞች ለአካዳሚው ስልጠና ወደ አዲስ አበባ የምናስመጣ ይሆናል፡፡ በመጀመሪያ በሁለት የእድሜ እርከኖች ከፍለን 50 ታዳጊዎችን የምናሰለጥን ይሆናል፡፡ ከአምስቱ አሰልጣኞች ሁለቱ የቡድኖቹን ስልጠና ሃላፊነት የሚወስዱ ሲሆኑ አንድ የአካል ብቃት አሰልጣኝ እንዲሁም አንድ መልማይ ይኖረናል፡፡ አምስተኛው አሰልጣኝ የግብ ጠባቂ አሰልጣኝ ነው የሚሆነው፡፡

በመጀመሪያ ደረጃ የምናደርገው እምቅ ችሎታ ያላቸውን ተጫዋቾች የመመልመል ስራ ነው፡፡ በአጠቃላይ የቅዱስ ጊዮርጊስ የወጣቶች አካዳሚ አወቃቀር ከስፔን ፕሮፌሽናል አንደኛ ዲዚቪዮን ክለቦች ጋር ተመሳሳይ ይሆናል፡፡ ኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች በምክትል አሰልጣኝነት በአካዳሚው የሚያገለግሉም ይሆናል፡፡

ሊሰራ ስለታቀደው የጨዋታ ስልት እና አሰለጣጠን

ሁሉም ወደ አዲስ ስፍራ ስትጓዝ ማድረግ ያለብህ በቦታው ስላለው ነባራዊ ሁኔታ ማጥናት ነው፡፡ ስፔናዊያን ስለሆንን ሁሉንም ነገር እንቀይራለን ማለት አይደለም፡፡ እዚህ ያለውን ነገር መመልከት እና ማጥናት ይገባናል፡፡ ስለተጫዋቾች ባህሪ ካወቅን በኃላ የትኛው ስልት እና አሰለጣጠን ዘዴ አዋጪ እንደሆነ የምንወስን ይሆናል፡፡

ሁሊዮ ፓዞ፡ እውነት ለመናገር ስምንጠቀመው የአሰለጣጠን ዘዴ፣ እንዴት አንድን ታዳጊ ብቁ እንደምናሳድግ ገና በጥናት ላይ ነን፡፡ ነገርግን ይህ ሲጠናቀቅ ታዳጊዎቹ በጥሩ ስልጠና ብቁ የሚሆኑበትን ነገር ይመቻቻል፡፡ ይህ ደግሞ የሶክስና ስኬት ዋናው ሚስጥር ነው፡፡ ሶክስና በስፔን ያለውን የእግርኳስ ስርዓት መለወጥ የቻለ እና ለውጡም ስኬታማ መሆኑ የታየ ነው፡፡ በተለያዩ ሃገራትም ጥሩ ልምዶች አሉት፡፡ በቻይና እና ካዛኪስታን ጥሩ ልምዶችን ማካበት ችሏል አሁን ደግሞ ወደ ኢትዮጵያ መጥቷል፡፡ በአፍሪካ ውስጥ ሶክስና ሲሰራ ይህ ለመጀመሪያ ግዜ ነው እናም ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የችሎታ ደረጃ በጥሩ እና ሳይንሳዊ ስልጠና መልካም ውጤት እንድናመጣ ያስችለናል፡፡ እዚህ አሰልጣኞችን ማምጣት ብቻ ሳይሆን የእግርኳስ ልማት ትምህርትንም ሃገሪቱ እንደሚጠቅም አድርጎ ማቅረብ ነው፡፡ ኢትዮጵያ በአህጉሪቱ እግርኳስ በግንባር ቀደምትነት መጠቀስ ያለባት ሃገር ነች ነገር ግን አሁን ባለው ደረጃ ፕሬዝደንት አብነትም እንዳስረዱን ኢትዮጵያ በታዳጊዎች ስልጠና ላይ ያልተሳካ ስርዓትን የገነባች ሃገር መሆኗን ነው፡፡

ስለእድሜ እርከን

አሁን ላይ መቶ በመቶ ውስኔ ላይ አልተደረሰም፡፡ ነገር ግን በመጀመሪያ በእድሜ ያነሱ ተጫዋቾች አይኖሩንም፡፡ ምንአልባት ከ15 ዓመት ጀምሮ ነው ስልጠናው የሚሰጠው፡፡ ሃሳባችን ተጨማሪ አሰልጣኞች አመጥቶ ከ15 ዓመት በታች ያሉ ታዳጊዎችንም ማሰልጠን ነው የቀጣይ አመት እቅዳችን፡፡ እድሜ እየጨመሩ በመጡ ቁጥር ታዳጊዎችን ማሰልጠን በዛው ልክ እየከበደ ነው የሚመጣው፡፡

ከአምስት አመት በኃላ ስለሚኖረው የክለቡ እና ተቋማቱ ግንኙነት

ከአምስት ዓመት በኃላ ከፕሬዝደንት ጋር አብነት ለተጨማሪ አመታት ውል እንደምንፈራረም ተስፋ አለኝ፡፡ እንደሚታወቀው የኢትዮጵያ እግርኳስ ቀጣይ ህልውና በኢትዮጵያዊያን አሰልጣኞች እጅ ነው የሚኖረው፡፡ በተፈጥሮ ይህ ነው ሊሆን የሚገባው፡፡ ከአምስት ዓመት በኃላ ልንረዳ የምንችለው ጉዳይ ካለ እዚሁ ለመስራት እንፈልጋለን፡፡ ምን አልባት ትብብራችን እንዳሁኑ ሳይሆን የተለየ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁን ላይ እኛ ትኩረታችን በአምስት አመቱ ላይ ነው፡፡

ወደ ሌሎች የአፍሪካ ሃገራት የመስፋፋት እቅድ

ከሌሎች የአፍሪካ ሃገራት ጋር ለመስራት እቅድ ይዘን እየተንቀሳቀስ ነው ያለነው፡፡ ለምሳሌ ደቡብ አፍሪካ፡፡ በሚቀጥለው ሳምንት ወደ ደቡብ አፍሪካ አቅንተን በትብብር ለመስራት ውይይቶችን የምናደርግ ይሆናል፡፡ እዘህ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ካደረግነው የትብብር ስምምነት የሚለይ ሲሆን ትብብራችን ከደቡብ አፍሪካ መንግስት ጋር ነው የሚሆነው ቢሆንም ቅዱስ ጊዮርጊስ እኛ ወደ አፍሪካ ስራችንን ለመጀመሪያ ግዜ ያስፋፋንበት ክለብ ስለሆነ በልባችን የተለየ ቦታ አለው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *