​ቻምፒየንስ ሊግ፡ አል አሃሊ፣ ዩኤስኤም አልጀር እና ዋይዳድ ግማሽ ፍፃሜውን ተቀላቅለዋል

በካፍ ቶታል ቻምፒየንስ ሊግ የሩብ ፍፃሜ ጨዋታ ቅዳሜ በተደረጉ ሶስት ጨዋታዎች ሲጀመሩ ወደ ቱኒዝ ያቀናው አል አሃሊ ከኃላ በመነሳት በአስደናቂ መልኩ ጠንካራውን ኤስፔራንስ ሲረታ ዩኤስኤም አልጀር እና ሌሎቹ የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ክለቦች መሆናቸውን አረጋግጠዋል፡፡

ዩኤስኤም አልጀር 0-0 ፎሬቫያሪዮ ደ ቤይራ

ከሳምንት በፊት ቤይራ ሞዛምቢክ ላይ 1-1 መለያየታቸውን ተከትሎ የማለፍ ቅድመ ግምቱ ለአልጄሪያው መዲና ክለብ ዩኤስኤም አልጀር አጋድሎ ነበር፡፡ ይህ ግምት እውን ሆኖ ዩኤስኤም አልጀር ከ2015 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለግማሽ ፍፃሜ ማለፍ የቻለበትን ውጤት ከፌሮቫያሪዮ ቤይራ ላይ ማግኘት ችሏል፡፡ ያለግብ በአቻ ውጤት በተጠናቀቀው ጨዋታ የሞዛምቢኩ ቻምፒዮን ጠንካራ እንቅስቃሴ በማሳየት ለተጋጣሚ ፈተና ሆኖ አምሽቷል፡፡ ቤይራዎች በተለይ በሁለተኛው 45 ያደረጓቸውን ሙከራዎች ወደ ግብነት መቀየር አልቻሉም እንጂ አሸንፈው የማለፍ እድልም ነበራቸው፡፡ በዩኤስኤም በኩል ግብ አዳኙ ኦሳማ ዳራፋሎ ያገኘውን ግልፅ የማግባት እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡ 

ኤስፔራንስ 1-2 አል አሃሊ

እጅግ በጣም በተጠበቀው የሰሜን አፍሪካ ደርቢ ልማደኛው አል አሃሊ ኤስፔራንስን ከሜዳው ውጪ 2-1 በማሸነፍ ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማምራቱን አረጋግጧል፡፡ ከሳምንት በፊት አሌክሳንደሪያ ላይ 2-2 ቡድኖቹ መለያየታቸው ተከትሎ በፋውዚ ቤንዛርቲ እየተመራ ጠንካራ አቋም ላይ ለተገኘው ኤስፔራንስ መልካም ቢመስልም የቱኒዚ ሃያል ለምዕት አመቱ የአፍሪካ ምርጥ ክለብ እጁን ለመስጠት ተገዷል፡፡ ቀይ እና ወርቃማዎቹ በጠሃ ያሲን ኬኔሲ ላይ የአሃሊው ግብ ጠባቂ ሻሪፍ ኤክራሚ የሰራውን ጥፋት ተከትሎ የተሰጠው የፍፁም ቅጣት ምት የቱኒዚያው ኢንተርናሽናል ኬኔሲ ወደ ግብነት ቀይሮ በመጀመሪያው አጋማሽ መምራት ሲችሉ ቱኒዚያዊው የመስመር ተከላካይ አሊ ማሎል አሃሊን ሁለተኛው አጋማሽ ከተጀመረ ከአምስት ደቂቃ በኃላ አቻ ማድረግ ችሏል፡፡ጠሃ ያሲን ኬኔሲ የግብ መጠኑን ሰባት በማድረስ ከቅዱስ ጊዮርጊሱ አጥቂ ሳላዲን ሰዒድ ጋር መስተካከል ችሏል፡፡ ከ12 ደቂቃ በኃላ ናይጄሪያዊው አጥቂ ጁኒየር አጃዬ በምሽቱ ድንቅ የነበረው አሊ ማሎል ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት አል አሃሊን አሸናፊ ማድረግ ችሏል፡፡ ከመሪነት ወደ ተመሪነት የተሸጋገሩት ባለሜዳዎቹ ለአሃሊ ግቦችን አፀፋውን መመለስ ሳይችሉ ከቻምፒየንስ ሊጉ ውጪ ሆነዋል፡፡ በ2012 የቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ኤስፔራንስ በየሱፍ ሳክኒ ፊት አውራሪነት ካይሮ ላይ ከአል አሃሊ ጋር አቻ ቢለያይም በመልሱ ጨዋታ በሜዳው ተሸንፎ ዋንጫውን አጥቷል፡፡ የአል አሃሊው አሰልጣኝ ሆሳም ኤል ባድሪ ክለቡን ከዚህ ቀደም የቻምፒየንስ ሊግ ባለድል ያደረጉ ሲሆን ለዘጠነኛ ግዜ ቻምፒየንስ ሊጉን ወደ ካይሮ የማምጣት እድል አሁን አላቸው፡፡

ዋይዳድ ካዛብላንካ 1-0 ማሜሎሲ ሰንዳውንስ

በሞሮኮ መዲና ራባት ላይ በተደረገ ጨዋታ ዋይዳድ ካዛብላንካ የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒዮን ማሜሎዲ ሰንዳውንስን በመለያ ምት 3-2 በመርታት ከውድድር ውጪ አድርጓል፡፡ በመጀመሪያው አጋማሽ በተለይ ብልጫን የወሰዱት ባለሜዳዎቹ በተደጋጋሚ ብራዚሎቹ ላይ ጫና ማሳደራቸው በ25ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጥር እንዲችሉ ረድቷቸዋል፡፡ ሳላዲን ሰዒዲ አማካዩ መሃመድ ኦንዠም ከመስመር ያሻገረለትን ኳስ በግንባሩ በመግጨት ዋይዳድን መሪ አድርጓል፡፡ ሰንዳውንሶች በመጀመሪያው 45 ተዳክመው የታዩ ሲሆን ግብ ጠባቂው ዴኒስ ኦኒያንጎ ግብ መሆን የሚችሉ ኳሶችን በማምክን ረገድ ጥሩ ተንቀሳቅሷል፡፡ ከእረፍት መልስ ብራዚሎቹ በንፅፅር ጥሩ መንቀሳቀስ ሲችሉ ሆሎምፖ ኬካና ያመከነውን ኳስ ምንአልባትም የደቡብ አፍሪካውን ክለብ አቻ የማድረግ አቅም ነበራት፡፡ አላፊውን ቡድን ለመለየት በተሰጠው የመለያ ምት ዋይዳድ 3-2 አሸንፏል፡፡ አሚን አቶቺ ከዋይዳድ በኩል እንዲሁም ፐርሲ ታኦ፣ ኮትዲቯሮቹ ያኒክ ዛክሪ እና ባንጋሊ ሱማሆሮ ከሰንዳውንስ በኩል የፍፁም ቅጣት ምቶቻቸውን ሳይጠቀሙባቸው ቀርቷል፡፡ በሁሴን አሞታ የሚመሩት ዋይዳዶች ለተከታታይ ሁለተኛ ግዜ ግማሽ ፍፃሜውን ሲቀላቀሉ በአሰልጣኝ ፒትሶ ሞሲማኔ የሚመራው ሰንዳውንስ የአምና ክብሩን የመድገም እድሉን አበላሽቷል፡፡ 

የማሜሊዲ ሰንዳውንስ እና ፌሮቫያሪዮ ቤይራ ከውድድሩ ውጪ መሆናቸውን ተከትሎ አራቱም የግማሽ ፍፃሜ ተፋላሚ ክለቦች ከሰሜን አፍሪካ ሁነዋል፡፡ የአልጄሪያው ኢኤስ ሴቲፍ በ2014 ቻምፒየንስ ሊጉን ካሸነፈ በኃላ ለተከታታይ ሁለት አመታት ዋንጫውን የሰሜን አፍሪካ ክለቦች ማሸነፍ ተስኗቸው ቆይቷል፡፡ 

ውጤቶች

ዩኤስኤም አልጀር 0-0 ክለብ ፌሮቫያሪዮ ደ ቤይራ (1-1)

ኤስፔራንስ ስፖርቱቭ ደ ቱኒዝ 1-2 አል አሃሊ (3-4)

ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ 1-0 ማሜሎዲ ሰንዳውንስ (0-1) (3-2 በመለያ ምት)

የዛሬ ጨዋታ

02፡30 – ኤትዋል ስፖርቲቭ ደ ሳህል ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ (0-0) (ስታደ ኦሎምፒክ ደ ሶስ)

ቀጣይ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎች

ዩኤስኤም አልጀር ከ ዋይዳድ አትሌቲክ ክለብ

አል አሃሊ ከ አል አሃሊ ትሪፖሊ እና ኤትዋል ደ ሳህል አሸናፊ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *