​የ2010 የፕሪምየር ሊግ ክለቦች አመታዊ ስብሰባ ዛሬ ተካሂዷል

የኢትየጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የ2009 የኢትየጵያ ፕሪምየር ሊግ የክለቦች አመታዊ ስብሰባ እና የ2010 ዓም የእጣ ማውጣት ስነስርዓት ዛሬ በጁፒተር ኢንተርናሽንል ሆቴል አከናውኗል።

የእለቱ መርሃ ግብር የኢትየጵያ እግርኳስ ፌደሪሽን ፕሬዝዳንት አቶ ጁነይዲ ባሻ በመክፈቻ እና በእንኳን ደህና መጣችሁ ንግግር ሲከፈት ወደ ፕሪምየር ሊጉ ያደጉት ጅማ አባ ጅፋር ፣ ወልዋሎ አዲግራት ዩንቨርሲቲ እና መቐለ ከተማን እንኳን ደህና መጣችሁ በማለት በቀጣይ የ2010 የእግር ኳስ ሂደቱ በሰላም እምዲጠናቀቅ እና የተሳካ እንዲሆን በመመኘት ንግግራቸውን አጠናቀዋል።

በስብሰባው ላይ አምስት የተለያዩ ኮሚቴዎች የየራሳቸውን የስራ አፈፃፀም ግምገማ ያቀረቡ ሲሆን በ2009ዓም የነበሩ ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች በየሪፖርቶቹ ቀርበው ለታዳሚያኑ ገለፃ ተደርጎባቸዋል።

የሊግ ኮሚቴ አባል የሆኑት አቶ ከበደ ወርቁ የ2009 ዓም የፕሪምየር ሊጉን ጠንካራ እና ደካማ ጎኖች ለታዳሚያኑ ሲያቀርቡ ከሞላ ጎደል ጥሩ እንደነበር ነገር ግን ብዙ ሊሻሻሉ የሚገባቸው ነገሮች እንደነበሩበት ገልፀዋል። 240 የሊግ ጨዋታዎች እንዲሁም 20 የጥሎ ማለፍ በአጠቃላይ 260 ጨዋታዎች ሲደረጉ 846 ቢጫ እና 48 ቀይ ካርዶች እንደተመዘገቡ ተገልጿል።

* የጨዋታ ሜዳዎች የቁጠወጥር መላላት ችግር

* የዳኝነት ስህተቶች

* የውድድር ሰዓት መዘግየት

* የመጫወቻ ሜዳ ምቹ አለመሆን እንዲሁም በአንዳንድ የጨዋታ መርሃ ግብሮች ላይ የስፖርት ቤተሰቡ ወደ ስታዲየም አለመግባት እና የተመልካች ቁጥር ማነስ በአመቱ የታዩ ደካማ ጎኖች እንደነበሩ ሲገለጽ እነዚህን ችግሮች በቀጣይ ለማሻሻል ስራዎች እንደሚሰሩ ተናግረዋል።

የዳኞች ኮሚቴ ሰብሳቢ እና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌደሬሽን የስራ አስፈጻሚ አባል የሆኑት አቶ ልዑልሰገድ የዳኞችን ሪፖርት ሲያቀረቡ በተለይ አንዳንድ ክለቦች ኢንተርናሽናል ዳኞች እንዲያጫውቷቸው አለመለፈለጋቸው እና በአንዳንድ ሜዳዎች ላይ የፀጥታ ተቆጣጣሪዎች ኃይል በቂ አለመሆን በአመቱ የተስተዋለ ችግር እንደነበር ተናግረዋል። በአጠቃላይ በሊጉ ላይ የነበረውን የዳኞች እንቅስቃሴ የዳኞች ኮሚቴው ገምግሞ 87% ጥሩ የዳኝነት ሂደት እንደነበር ማስቀመጣቸውን ገልፀዋል።

የዲሲፒሊን ኮሚቴው ሪፖርት በአቶ ተፈራ ደምበል ሲቀርብ ፌደሬሽኑ በአጠቃላይ 626 ሺ ብር በዲሲፕሊን ቅጣት ከክለቦች እና ከተጨዋቾች እንደተገኘ ሲገለፅ ይህ ገንዘብ ግን ወደ ፌደሬሽኑ ሙሉ ለሙሉ ገቢ እንዳልተደረገ ተናግረዋል።

ኮሚቴው በተለይ የስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል ምክንያቶች በመተንተን ሊሻሻሉ እንደሚገባቸውም በማሳሰብ ምክንያቶቹን አስረድተዋል።

በኮሚቴው በኩል ለስፖርታዊ ጨዋነት መጓደል

*ውጤትን በፀጋ አለመቀበል

*በክለቦች ዘንድ የተዛባ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት

*የክለብ ተጨዋቾች እንዲሁም የክለብ አሰልጣኞኝ ደጋፊዎችን በምልክት ለረብሻ ማነሳሳት እና መሳደብ

*ክለቦች ለተጨዋቾ እና ለደጋፊዎቻቸው የዳኝነት ህግ በአግባቡ አለማስተማር

*ረብሻዎች ሲነሱ ክለቦች ደጋፊዎቻቸውን ለማረጋጋት አለመሞከር እንዲሁም ሌሎችም እንደነበሩ ተገልጿል።
ከሪፖርቶቹ በኃላ ከ2010 እስከ 2012 ድረስ የሚያገለግል የወንዶች የፕሪምየር ሊግ የውድድር ደንብ ማሻሻያ ከፌደሬሽኑ በኩል ቀርቦ ያሉ አዳዲስ ነገሮች ሲገለፁ ክለቦችም በደንቦቹ ላይ የመሻሻያ ሃሳቦች በማንሳት ውይይቶች ተደርገዋል።

የውድድሮች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ በደንቡ ዙርያ ያሉ ጉዳዩችን ያስረዱ ሲሆን በደንቡ ላይ በተለይ በምዕራፍ 7 አንቀፅ 1 ላይ በተደነገገው የሚወርዱ እና የሚወጡ ክለቦች ብዛት ወደ አራት ከፍ ብሏል የሚለው ላይ ክለቦች በርካታ ሃሳቦችን አንስተዋል።

ከክለቦች በኩል ይህ በምዕራፍ 7 አንቀጽ 1 ላይ የተደነገገውን የማሻሻያ ደንብ የተቃወሙ ሲሆን በሀገራችን ባለው ወቅታዊ የእግር ኳስ እድገት አንጻር ተቀባይነት እንደማይኖረው እና መሆን እንደሌለበት ተናግረዋል።

ፌደሬሽኑም የክለቦች ጥያቄ ተቀብሎ ይህንን አዲስ ደንብ መሻሩን ያስታወቀ ሲሆን ደንቡን ግን ለማውጣት በከፍተኛ ሊጉ ላይ የሚታየውን ከፍተኛ የሜዳ ላይ ፉክክር ለማበረተታት እንደሆነ ገልጿል።

በስብሰባው ላይ የሊጉ የአደረጃጀት ሁኔታ ስለማስተካከል ፣ ስለ ተጨዋቾች የዝውውር ገንዘብ አከፋፈል መንገድ ፣ ስለ ስፖርታዊ ጨዋነት እና ስለ ዳኝነት ችግሮች ከክለቦች ጥያቄዎች ቀርበው የመፍትሄ ሃሳቦች የተነሱ ሲሆን ለቀጣይ መደረግ አለባቸው ብለው የሚታሰቡ ጉዳዮች ላይም ውይይቶች ተደርገዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *