ሞሮኮ የቻን 2018 አዘጋጅ ሆና ተመርጣለች

የአፍሪካ እግርኳስ ኮንፌድሬሽን (ካፍ) ሞሮኮን በጥር ወር የሚዘጋጀውን የአፍሪካ ሃገራት ቻምፒዮንሺፕ (ቻን) እንድታስተናግድ መርጧታል፡፡ ካፍ ኬንያ ውድድሩን ለማስተናገድ ብቁ አይደለችም በማለት የማዘጋጀት መብትን ከምስራቅ አፍሪካዋ ሃገር መቀማቱ ይታወሳል፡፡

ቅዳሜ በሌጎስ ናይጄሪያ በተደረገውና የካፍ ፕሬዝደንት አህመድ አህመድ በመሩት የኢመርጀንሲ ኮሜቴ ስብሰባ ኮንፌድሬሽኑ ሞሮኮ አዘጋጅ እንድትሆን ተስሟምቷል፡፡ ሞሮኮ ከኤኳቶሪያል ጊኒ የተሻለ የማስተናገድ አቅም ያላት መሆኑ እንድትመረጥ አስችሏታል፡፡ ካፍ በገለፃው ከሞሮኮ እና ኤኳቶሪያል ጊኒ ባሻገር የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ውድድሩን ለማስተናገድ ፍላጎት ማሳየቱን አስታውሶ አስፈላጊ የነበረው የመንግስት ድጋፍ ያገኘበትን ደብዳቤ አለመላኩ ከፉክክሩ ውጪ እንዳደረገው ተገልጿል፡፡ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌድሬሽን ፕሬዝደንት ጁነይዲ ባሻ ውድድሩን ለማስተናገድ ፌድሬሽኑ አለመጠየቁን መናገራቸው ይታወሳል፡፡

ሞሮኮ ከጥር 4-27 በአራት ከተሞች ውድድሩን ታስተናግዳለች፡፡ አጋድር፣ ካዛብላንካ፣ ማራካሽ እና ታንገ ውድድሩን ለማስተናገድ የተመረጡ ከተሞች ናቸው፡፡ የሞሮኮ እግርኳስ ፌድሬሽን በቅርብ ወራት ከካፍ ያለው ግንኙነት መጠናከሩን ተከትሎ የቻን የማዘጋጅት እድሉን ማግኘቱ የሚያስገርም አይሆንም፡፡ የፌድሬሽኑ ፕሬዝደነት ፋውዚ ሌካ የአህመድ አህመድ የቅርብ ወዳጅ ሲሆኑ የካፍ ምክትል ፕሬዝደንትም በመሆን ያገለግላሉ፡፡

ሞሮኮ ከምዕራብ ሳህራ ጋር በነበራት ቅራኔ ምክንያት ከአፍሪካ ህብረት አባልነት ለረጅም ግዜ እራሷን አግልላ የነበረ ሲሆን አሁን ላይ ወደ ህብረቱ መመለሷን ተከትሎ አህጉሪቱ ፓለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ጉዳዬች ላይ ተፅዕኖ ለመፍጠር እየሰራች ትገኛለች፡፡ በተለይ በእግርኳሱ ከፍተኛ መዋዕለ ንዋይ በማፍሰስ በተለያዩ የአፍሪካ ሃገራትን መደገፍ ጀምራለች፡፡ በገንዘብ እጥረት የማላዊ እግርኳስ ማህበር እራሱን ከአፍሪካ ዋንጫ ማጣሪያ እንዳያገል ሞሮኮ በድጋፍ ያደረገች ሲሆን በቅርቡ ለኢትዮጵያ አሰልጣኞች የስልጠና ትምህርት አዘጋጅታ ነበር፡፡ በሩዋንዳ በተመሳሳይ አራት በተለያዩ አውራጃዎች 3000 ተመልካች የመያዝ አቅም ያላቸው ስታዲየሞች እየገነባ ይገኛል፡፡ በሩዋንዳ የሚገነቡት ስታዲየሞች በብድር መልኩ በመሆኑ የሃገሪቱ መንግስት ከ3-6 ዓመታት ውስጥ የስታዲየሞቹ ግንባታ የማካካስ ግዴታ አለበት፡፡

ሞሮኮ አስቀድማ ሰሜን ዞን ማጣሪያ ግብፅን አሸንፋ ለቻን ማለፏ ይታወቃል፡፡ ይሁን እና አሁን ላይ አዘጋጅ ሃገር እንደመሆኗ 16 ሃገራት በሚሳተፉበት ውድድር ላይ የሚሳተፈውን አንድ ቀሪ ሃገር ካፍ በቅርቡ ይፋ እንደሚያደርግ ይጠበቃል፡፡ ግብፅ ሌላኛዋ ተካፋይ ሃገር የመሆን እድሏ የሰፋ ነው፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *