​አአ ከተማ ዋንጫ፡ ከምድብ ሀ ኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል

የአአ ከተማ ዋንጫ የምድብ ሀ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ተደርገው ኢትዮጵያ ቡና እና ጅማ አባ ጅፋር ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያሻገራቸውን ውጤት አስመዝግበዋል፡፡ ጨዋታዎቹ የተጀመሩትም የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርስቲ ስራ አስኪያጅ የነበሩትና ለክለቡ በድጋሚ መመስረት እንዲሁም ፕሪምየር ሊጉን መቀላቀል ትልቁን ድርሻ የተወጡት አቶ ሰለሞን ገ/ፃድቅ ህልፈትን ምክንያት በማድረግ በአንድ ደቂቃ የህሊና ፀሎት በማሰብ ነበር፡፡

ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ተመጣጣኝ ፉክክር በታየበት የአዲስ አበባ ከተማ እና ጅማ አባጅፋር ፍልሚያ የመጀመሪያ ደቂቃዎች ላይ ጠንካራ የግብ ሙከራዎች አልተስተዋሉም ። ሆኖም 12ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አበባ ከተማዎች የፈጠሩትን የግብ ዕድል ለማክሸፍ የአባጅፋር ተከላካዮች ከግብ ክልላቸው በረጅሙ ያራቁትን ኳስ ብቸኛ አጥቂ ሆኖ ጨዋታውን የጀመረው ሳምሶን ቆልቻ ረጅም ርቀት ከተከላካዮች ጋር በመፋለም ግብ ላይ ደርሶ በጥሩ አጨራረስ የመጀመሪያ ግብ አስቆጥሯል። ከዚህ በተጨማሪም ከጨዋታ ውጪ ሆነ እንጂ 19ኛው ደቂቃ ላይ የአባጅፋሩ የመስመር አማካይ  ተመስገን ገ/ኪዳን በግንባሩ ሁለተኛ ጎል አክሎ ነበር ። አዲስ አበባዎች ግብ ከተቆጠረባቸው በኃላ በተሻለ ገፍተው ለመጫወት ቢሞክሩም 21ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ እንዳለማው ታደሰ ሞክሮ በጅማው ግብ ጠባቂ ዳዊት አሰፋ ከተመለሰበት ኳስ ውጪ ወደ ሶስተኛው የሜዳ ክፍል ሰብረው መግባት ከብዷቸው ታይቷል ። በዚህም ምክንያት በአብዛኛዎቹ ደቂቃዎች የቡድኑ አጥቂዎች በቂ የግብ ዕድል እንዳያገኙ እና ከፊት ተነጥለው እንዲታዩ ሆኗል ።

እንደመጀመሪያው ሁሉ በሁለተኛውም አጋማሽ ጥሩ መነሳሳት የታየበት እንቅስቃሴ በሁለቱም በኩል የታየ ሲሆን በሙከራ ረገድ ግን የተቀዛቀዘ ነበር ማለት ይቻላል ። የመጀመሪያውን ግብ ያስቆጠረው ሳምሶን ቆልቻ ከእረፍት መልስ ከሔኖክ አዱኛ የተሻገረለትን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ከሞከረ በኃላ ሌላ ጠንካራ ሙከራ ሳንመለከት ነበር በ 77ኛው ደቂቃ ላይ አዲስ አበባዎች በገናናው ረጋሳ አማካይነት አቻ የሆኑበትን ግብ ያስቆጠሩት ። ገናናው አጋጣሚዋን ያገኘው ከግቡ ቅርብ ርቀት ላይ ሲሆን ጌታነህ ወርቅነህ ከሳጥን ውጪ የሞከረው ኳስ በተከላካዮች ተጨርፎ ወደሱ ሲመጣ በተረጋጋ አጨራረስ ከዳዊት መረብ ላይ ማሰሳረፍ ችሏል። ሆኖም ይህች ግብ አዲስ አበባዎችን አቻ ያደረገቻቸው ለ ቀጣዮቹ 6 ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በሁለት አጋጣሚዎች ከቀኝ መስመር ተከላካዩ ሄኖክ አዱኛ የተነሱ ኳሶችን በግንባሩ ሞክሮ ያልተሳካለት ሳምሶን ፤ ሔኖክ በ86ኛው ደቂቃ ላይ የፈጠረለትን ሶስተኛ የአየር ላይ አጋጣሚ በግንባሩ አስቆጥሮ አባጅፋርን በድጋሚ መሪ አድርጓል ። ከዚህ በኃላ በነበሩት ደቂቃዎች አቻ ለመሆን የጣሩት አዲስ አበባዎች በተጨማሪ ደቂቃ ላይ ከግቡ በቅርብ ርቀት ላይ  በእንዳለማው ታደሰ አማካይነት ጥሩ ዕድል ቢፈጥሩም ግብ ማስቆጠር ሳይችሉ ጨዋታው ተጠናቋል ። የሳምሶን ሁለተኛ ግብ ጨዋታውን ከማሸነፍ ባለፈ ጅማ አባጅፋር ብዙ ባገባ በሚለው ህግ መሰረት ደደቢትን በልጦ ምድቡን በሁለተኛነት እንዲያጠናቅቅ ወሳኝ ነበረች ።

በእለቱ ሁለቱን ግቦች ያስቆጠረው የቀድሞው የሀድያ ሆሳዕና አጥቂ ሳምሶን ቆልቻ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል ።

በመቀጠል በተደረገው እና በአመዛኙ በኢትዮጵያ ቡና የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እንዲሁም በደደቢት የመልሶ ማጥቃት እንቅስቃሴ የታጀበው ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ስኬታማ ያልሆኑ የማጥቃት ሂደቶችን አሳይቶን አልፏል ። በ8ኛው እና 18ኛው ደቂቃ ላይ በሳምሶን ጥላሁን ቅጣት ምቶች አማካይነት የተሻለ ሙከራ ያደረጉት ቡናማዎቹ በተለይ በመጀመሪያዎቹ  ደቂቃዎች የነበራቸውን የኳስ ቁጥጥር ወደ ፍሪያማነት መቀየር ተስኗቸው ታይቷል ።

የተለመደው የመስመር ተከላካዮች የማጥቃት እንቅስቃሴ ተዳክሞ በታየበት አጋማሽ የማጥቃት እንቅስቃሴው ወደመሀል የጠበበ መሆኑ እና በፍጥነትም ረገድ የተቀዛቀዘ መሆኑ ቡድኑን ወደተጋጣሚ ሜዳ ከገባ በኃላ በቁጥር ለመበለጥ እና ለላልተሳኩ ቅብብሎች አጋልጦታል ። በአመዛኙ በመከላከል ላይ ያሳለፈው ደደቢት በተለይ በአቤል ያለው አማካይነት ይፈጠሩ የነበሩ የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም አልቻለም። በተለይ በ31ኛው ደቂቃ ላይ በቀኝ መስመር ከተነሳ መልካም የሚባል የመልሶ ማጥቃት አጋጣሚ አቤል ወደመሀል ያሳለፈውን ኳስ ሌላው አጥቂ ሮበን ኦባማ  በሚስቆጭ መልኩ ሳይደርስበት ቀርቷል ። በመጨረሻዎቹ የመጀመሪያ ግማሽ  15 ደቂቃዎች የተወሰደባቸውን ብልጫ በተወሰነ መልኩ ማርገብ የቻሉት ደደቢቶች 43ኛው ደቂቃ ላይ በያብስራ የተፈጠረውን ዕድል አቤል ሞክሮ ወደላይ ከወጣበት አጋጣሚ ውጪ ሌላ ዕድል መፍጠር አልቻሉም ። በአጨዋወት ደረጃ በመልሶ ማጥቃት አጋጣሚዎች ላይ የቀድሞው የቡድኑ ጠንካራ ጎን የነበረው የመስመር እንቅስቃሴ በእጅጉ ተዳክሞ ታይቷል፡፡

ሁለተኛው አጋማሽ በተለይም የመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ቀዝቃዛ እንቅስቃሴ የታየባቸው ነበሩ ። ከ52ኛው ደቂቃ የእያሱ ታምሩ ሙከራ በኃላም ሌላ የግብ ሙከራ የታየው 68ኛው ደቂቃ ላይ ሮቤል ከቀኝ መስመር ያሻማው ኳስ ከግቡ አፋፍ ላይ ተቀይሮ ለገባው ማናዬ ፋንቱ በፈጠረው ንፁህ እድል ነበር ። ሆኖም ማናዬ የሞከረው ኳስ የግቡን ቋሚ ለትሞ ተመልሷል። በሁለቱ ቡድኖች ፍጥነት የታከለበት ሌላ የማጥቃት እንቅስቃሴ ለማየት የቻልነው በ71ኛው ደቂቃ ነበር ። በዚህ አጋጣሚም  በደደቢት በኩል በግራ ሳጥን ጠርዝ ላይ አቤል እንዳለ ያደረገው ሙከራ እና በተቃራኒው ግብ ደግሞ ኤልያስ ማሞ ከሳጥን ውጪ የሟከረው ኳስ ሁለቱም ኢላማቸውን ቢጠብቁም በግብጠባቂዎቹ ጥረት ከሽፈዋል ። እነዚህ ዕድሎችም የጨዋታው የመጨረሻ ማራኪ ፍሰት የታየባቸው ሆነው በሁለቱም ብኩል ግብ ሳይቆጠር ቀሪ ደቂቃዎች ተጠናቀዋል ።  ከዚህ ውጪ በሁለተኛው አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡና ስድስት ደደቢት ደግሞ አምስት ተጨዋቾችን ቀይረው በማስገባት ተጨዋቾቻቸውን ለመገምገም መሞከራቸው የጨዋታው ጥሩ ጎን ሆኖ ታይቷል ።

በጨዋታው ሙሉ 90 ደቂቃ ሜዳ ላይ ከቆዩ ጥቂት ተጨዋቾች መሀል አንዱ የነበረው እያሱ ታምሩ የጨዋታው ኮከብ ሆኖ ተመርጧል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *