ኢትዮጵያዊው አማካይ ቢኒያም በላይ ለክለቡ ስኬንደርቡ ለመጀመሪያ ግዜ በአልባኒያ ሱፐርሊጋ ተሰልፎ መጫወት ችሏል፡፡ ቢንያም በሁለተኛው 45 ተቀይሮ በመግባት ነው በስኬንደርቡ መለያ ለመጀመሪያ ግዜ በአልባኒያ ሱፐርሊጋ መጫወት የቻለው፡፡
እሁድ በተደረገው ጨዋታ ስኬንደርቡ በሜዳው ኬኤስ ሉሻና አስተናግዶ 4-1 በሆነ ውጤት ማሸነፍ ችሏል፡፡ የስኬንደርቡን የድል ግቦች አፍሪም ታኩ (ሁለት)፣ አሊ ሶዊ እና ጄምስ አዲኒዬ አስቆጥረዋል፡፡ ለእንግዶቹ ፋትጆን ሴታ በ29ኛው ደቂቃ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ ሶስተኛውን የሴኬንደርቡ ግብን ያስቆጠረው አሊ ሶዊ በ78ኛው ደቂቃ በቢኒያም በላይ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡ ቢኒያም ወደ ስኬንደርቡ ካመራ በኃላ በሁለት የአልባኒያ ዋንጫ ጨዋታዎች ላይ ተሰልፎ አንድ ግብ ማስቆጠር የቻለ ሲሆን ለመጀመሪያ ግዜ እሁድ በተደረገው የሊግ ጨዋታ መሰለፍ ችሏል፡፡
ስኬንደርቡ አሁን በሊጉ አናት ላይ ሲገኝ ከስድስት ጨዋታዎች 16 ነጥቦችን መሰብሰብ ችሏል፡፡ ባሳለፍነው አርብ ያደረገውን የሊግ ጨዋታም ኬኤፍ ላሲን 2-1 መርታት ችሏል፡፡ በመጪው ሐሙስ በዩኤፋ ዩሮፓ ሊግ ጨዋታ ስኬንደርቡ በሜዳው የሰርቢያውን ሃያል ፓርቲዛን ቤልግሬድን ያስተናግዳል፡፡ ከዩጎዝላቪያ መበታተን እና የባልካን ጦርነት በኃላ በኃላ በአልባኒያ እና ሰርቢያ መካከል የፖለቲካ ቁርሾ መኖሩን ተከትሎ ጨዋታው ከወዲሁ ተጠባቂ እንዲሆን አድርጎታል፡፡