​መሐመድ ናስር ወደ ፋሲል ከተማ አምርቷል

መሐመድ ናስር ከጅማ አባ ቡና የአንድ ዓመት ቆይታ በኃላ ወደ ፋሲል ከተማ ማምራቱን ክለቡ ይፋዊ የፌስቡክ ገፁ አስታውቋል፡፡ ፋሲል ከናይጄሪያዊው አጥቂ ክርስቶፈር አሞስ ኦቢ ጋር መለያየቱን ጨምሮ የገለፀ ሲሆን በምትኩም በፕሪምየር ሊጉ በበርካታ ክለቦች የተጫወተው መሐመድን አስፈርሟል፡፡

መሐመድ የ2009 የውድድር ዓመትን በትውልድ ከተማው ክለብ ጅማ አባ ቡና ያሳለፈ ሲሆን በውድድር ዓመቱ ከአሜ መሃመድ ጋር ጥምረትን ፈጥሮ ለአባ ቡናን ሲጫወት ቆይቷል፡፡ ፋሲል ከዚህ ቀደም ዩጋንዳዊው ሮበርት ሴንቴጎ እና ናይጀየሪያዊውን የቀድሞ የኤሌክትሪክ እና ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የፊት መስመር ተሰላፊ ፊሊፕ ዳውዝን ማስፈረሙ የሚታወስ ሲሆን የመሐመድ ለክለቡ መፈረም ለአሰልጣኝ ምንትስኖት ጌጡ በፊት መስመር ላይ አማራጮች እንዲሰፋላቸው ያስችላል፡፡

መሐመድ በጅማ አባ ጅፋር በጀመረው የእግርኳስ ህይወቱ በመከላከያ፣ ኢትዮ ኤሌክትሪክ፣ ቅዱስ ጊዮርጊስ፣ አዳማ ከተማ፣ ኒያላ፣ ኢትዮጵያ ቡና፣ ኢትዮጵያ መድን እና በሱዳኑ አል አሃሊ ሸንዲ ክለቦች መጫወት ችሏል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *