ሳላዲን ሰዒድ ለአልጄሪው ክለብ ኤምሲ አልጀር ለመጫወት የሁለት አመት ውል ፈርሟል፡፡ የዋሊያዎቹ አምበል ሳላዲን የምዕተ አመቱን የአፍሪካ ምርጥ ክለብ የግብፁን አል አሃሊን ለቆ ወደ ኤምሲ አልጀር ማምራቱ ተረጋግጧል፡፡
ከአል አሃሊ ጋር ያልተሳካ ግዜያትን ያሳለፈው ሳላዲን በካይሮው ክለብ ለአንድ ዓመት ብቻ ቆይታ አድርጓል፡፡ ሳላዲን በአል አሃሊ ቆይታው በ17 ጨዋታዎች 4 ግቦችን ማስቆጠር እንዲሁም 2 ግብ የሆኑ ካሶችን ማቀበል ችሏል፡፡ ኤምሲ አልጀር ሳላዲንን ለመውሰድ ከፍተኛ ፍላጎት የነበረው ክለብ ነው፡፡ የክለቡ ፕሬዝደንት አብዱልከሪም ሬሲ ሳላዲን ለማዘዋወር የሚፈልጉት ዓይነት ተጫዋች መሆኑን መናገራቸው ይታወቃል፡፡ አል አሃሊ ጋቦናዊውን ማሊክ ኢቮና ከሞሮኮው ዋይዳድ ካዛብላንካ እና ጋናዊውን ጆን አንትዊን ከሳዑድ አረቢያው አል ሻባብ ማስፈረመ በመቻሉ የሳላዲን ከአሃሊ መልቀቅ አፋጥኖታል፡፡ ቀሪ የሁለት ዓመት ውል ከአሃሊ ጋር የነበረው ሳላዲን በነፃ ዝውውር ኤምሲ አልጀርን ሊቀላቀል ችሏል፡፡ ዝውውሩ ዕረቡ ጠዋት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ሳላዲን የህክምና ምርመራውን ከኤምሲ አልጀር ዋና ፅህፈት ቤት አቅርያቢያ በሚገኝ ሆስፒታል ውስጥ አድርጓል፡፡
በሙሉ ስሙ መውሊዲያ ክለብ ደአልጀር በሚል የሚጠራው ኤምሲ አልጀር የዋና ከተማዋ አልጀርስ ክለብ ሲሆን፤ በ1921 ተመስርቷል፡፡ የአልጄሪያን ሊግ አንድን 7 ግዜ አሸንፏል፡፡ ከጄኤስ ካቤሌ በመቀጠል የሊጉን ዋንጫ ቡዙ ግዜ ያነሳ ክለብ ነው፡፡ የጥሎ ማለፉን ውድድር 7 ግዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡ ይህም ከዩኤስኤም አልጀር እና የወቅቱ የአፍሪካ ቻምፒየንስ ሊግ አሸናፊ ኢኤስ ሴቲፍ በመቀጠል በውድድሩ ስኬታማ መሆን የቻለ ክለብ ያደርገዋል፡፡ በ1976 የአፍሪካ ክለቦች ሻምፒዮናን ያሸነፈ የመጀመሪያው የአልጄሪያ ክለብ ነው፡፡ ኤምሲ አልጀር በፖርቹጋላዊው የቀድሞ ፖርቶ፣ ቤኔፊካ፣ ፒኤስጂ እና የካሜሮን ብሄራዊ ቡድን አሰልጣኝ አርተር ሆርጌ ይመራል፡፡
የሳላዲን በአልጄሪያ ሊግ ለመጀመሪያ ግዜ የተጫወተ ኢትዮጵያዊ ይሆናል፡፡ ሳላዲን በኤምሲ አልጀር 20 ሺህ ዩሮ ወርሃዊ ደሞዝ የሚከፈለው ይሆናል፡፡ ሳላዲን ከአል አሃሊ ጋር ዛማሌክን በመለያ ምት አሸንፎ የግብፅ ሱፐር ካፕን ማሸነፍ ችሏል፡፡ ሳላዲን በኢትዮጵያ ለሙገር ሲሚንቶ እና ቅዱስ ጊዮርጊስ ፣ በግብፅ ለዋዲ ደግላ እና አል አሃሊ እንዲሁም በቤልጂየም ለሊርስ መጫወት ችሏል፡፡
የአልጄሪያ ሊግ አንድ በነሃሴ ወር አጋማሽ ይጀመራል፡፡ ኤምሲ አልጀር ባሳለፍነው የውድድር ዓመት በ12ተኛ ደረጃነት አጠናቅቋል፡፡