የወቅቱ የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊ ውዱስ ጊዮርጊስ በዝውውር ላይ ዝምታን መርጦ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን ወሳኝ ተጫዋቾችን ለማዘዋወር ከጫፍ መድረሱን ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
የደደቢቱ ተከላካይ አስቻለው ታመነ እና የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ አስቻለው ግርማ ፈረሰኞቹን ይቀላቀላሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ በቃል ደረጃም ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአስቻለው ታመነ ጋር መስማማቱ ተነግሯል፡፡ አስቻለው ታመነ ውሉን ለማደስ ከደደቢት ጋር ተስማምቷል ተብሎ መዘገቡም አይረሳም፡፡ አስቻለው ታመነ በደደቢት እና በዋሊያዎቹ መለያ ያሳየው ድንቅ ብቃት ወደ 12 ግዜ ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አሸናፊዎቹ ዕይታ ውስጥ ከቶታል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ ለአስቻለው ታመነ ዝውውር ምን ያህል ገንዘብ እንደሚያወጣ አልተገለፀም፡፡
የመስመር አጥቂው አስቻለው ግርማ ሌላኛው ቅዱስ ጊዮርጊስን ይቀላቀላል ተብሎ የሚጠበቅ ተጫዋች ነው፡፡ የኢትዮጵያ ቡናው ተጫዋች በአሁን ሰዓት ለዕረፍት ባሌ ይገኛል፡፡ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር ውሉን ለማደስ ድርድር ላይ ነው የተባለው አስቻለው ለቡና ባላንጣ ወደ ሆነው ጊዮርጊስ ለማምራት ከጫፍ መድረሱን ያገኘናቸው መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
ቅዱስ ጊዮርጊስ በተያያዘ የደደቢቱን የመስመር ተጨዋች ታደለ መንገሻን ለማስፈረም ፍላጎት አለው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ መለያ በ2001 የተጫወተው ታደለ ወደ ቀድሞ ክለቡ የመመለስ ዕድሉ ሰፊ ነው ተብሏል፡፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካዩን ሳላዲን በርጌቾ እና የመሃል ሜዳ ተጫዋቹን ምንያህል ተሾመ ውል ለማደስ ከጫፍ ደርሷል፡፡ አምና ከኢትዮጵያ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን የተቀላቀለው ፋሲካ አስፋው ክለቡን የመልቀቅ ዕድሉ በጣም የሰፋ ነው፡፡
የዋሊያዎቹ አጥቂ ባዬ ገዛኸኝ ከቅዱስ ጊዮርጊስ ጋር ድርድር ጀምሮ የነበረ ቢሆንም ለመከላከያ በመፈረሙ ዝውውሩ ዕውን መሆን ሳይችል ቀርቷል፡፡
የአስቻለው ታመነ መምጣት ዩጋንዳዊውን አይዛክ ኢዜንዴ በፈረሰኞቹ የሚኖረው ቆይታ አጠራጣሪ ያደርገዋል፡፡ በተያያዘም ጊዮርጊስ አንድ ጋናዊ ተጨዋች ለማምጣት ድርድር ላይ መሆኑ ታውቋል፡፡