‹‹ ለተከሰተው ችግር ተጠያቂዎቹ ካሜሩኖች ናቸው ›› አበበ ገላጋይ (ከ20 አመት በታች ሴቶች የቡድን መሪ)

የኢትዮጵያ ከ20 አመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የሰሞኑ መነጋገርያ ከሆነው የበረራ ችግር እና እንግልት በኋላ ባለፈው ረቡእ ማታ አዲስ አበባ መግባታቸው ይታወሳል፡፡ ፌዴሬሽኑም ከተከሰተው ችግር እና አጠቃላይ የቡድኑ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ዛሬ በኢትዮጵያ ሆቴል መግለጫ ሰጥቷል፡፡ እኛም የመግለቻውን ዋና ዋና ሃሳቦች እንዲህ አቅርበናቸዋል፡፡

 

‹‹ ለተከሰተው ችግር ተጠያቂዎቹ ካሜሩኖች ናቸው ›› አበበ ገላጋይ (የቡድን መሪ)

‹‹ ከበረራው ችግር መከሰት በኋላ ሌሎች አማራጮችን አስበን ነበር፡፡ በቀጣዩ ቀን ላይ አውቶብስ አዘጋጅተን የ4 ሰአት መንገድ በየብስ ለመጓዝ አስበን ነበር፡፡ ነገር ግን ከዱዋላ ተደውሎ የደህንነት እና የመንገዱ ሁኔታ አስቸጋሪ እንደሆነ ስለተነገረን በመኪና ልንጓዝ አልቻልንም፡፡ ››

‹‹ ካሜሩን እንደምናስባት አይነት ሃገር አይደለችም፡፡ በእግርኳስ ስመጥር ተጫዋቾችን ብታፈራም አጠቃላይ የሃገሪቱ ሁኔታ ግን ጥሩ አይደለም፡፡ የካሜሩን እግርኳስ ፌዴሬሽን በችግር ውስጥ የሚገኝ በመሆኑ በኖርማላይዜሽን ኮሚቴ ነው የሚመራው፡፡ በዚህም ምክንያት ተቀናጅቶ የመስራት ችግር አለበት፡፡ የእንግሊዝኛ እና ፈረንሳይኛ ተናጋሪ ቢሆኑም ከነሱ ጋር ግንኙነት ማድረግ አስቸጋሪ ነው፡፡ ግዴለሽነትና ሃላፊነት የመወጣት ችግር አለባቸው፡፡ በአጠቃላይ የቸልተኝነት እና ውጤቱንም ማግኘት ባለመቻላቸው ነው ችግሮች የመጡት፡፡ ››

‹‹ እንደ ሃገር ከካሜሩን ጋር የፖለቲካ ችግር የለብንም፡፡ በሃገሪቱ ብዙ ኢትዮጵያውያን የሉም፡፡ ሃገራችንም ከሃገሪቱ ጋር በናይጄርያ በኩል ግንኙነት ካላደረግን በቀር ኤምባሲም የላትም፡፡ ››

‹‹ በአየር ማረፍያው ውስጥ ከማደር ውጭ አማራጭ አልነበረንም፡፡ bording pass 3 ግዜ ነው ያሰራነው፡፡ በዚህ ዙርያ ሁለተኛ አማራጭ ባለመያዛችን እዛው ለማደር ተገደናል፡፡ ››

‹‹ ስፖርት ላይ የሚከሰት ችግር ፓለቲካዊ መሆን የለበትም፡፡ የብቀላ ጉዳይ ይኖረናል ብለን አናስብም፡፡ ከደጋፊዎቻችንም የበቀል ጉዳይ እንዲነሳ አንፈልግም፡፡ የፌዴደሬሽኑ ግድየለሽነት ችግር ውስጥ ቢከተንም ይህ የካሜሩንን መንግስት አይወክልም፡፡ ››

‹‹ በካሜሩን ከጨዋታው በፊት በሚደረግ ስብሰባ ላይ የሚያስመሰግን ነገር ሳይሰሩልን አመስግነናል፡፡ በማመስገናችን ግን እንድንፀፀት ያደረጉ ሁኔታዎች ነው የገጠሙን፡፡ ››

‹‹ የኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ማድረግ የሚችለውን ነገር በሙሉ አድርጓል፡፡ አየር መንገዳችንም ከሱ የሚጠበቅበትን ስራ ተወጥቷል፡፡ ስለዚህ ለተከሰተው ችግር ሙሉ ለሙሉ ሃላፊነቱን የሚወስዱት የካሜሩን እግርኳስ ፌዴሬሽን እና የካሜሩን አየር መንገድ ናቸው፡፡ ››

 

‹‹ በቀላሉ ውጤት እናገኛለን ብለን አንገምትም፡፡ በቀላሉ ከውድድር እንወጣለን ብለንም አናስብም ›› አስራት አባተ (አሰልጣኝ)

‹‹ ይህ ችግር የተከሰተው በእኛ ላይ ብቻ ሳይሆን ጨዋታውን በመሩት የኮንጎ ዳኞች እና ሌሎቹም ተጓዦች ላይ ነው፡፡ ››

‹‹ ችግር በቡድኑ ላይ የሚያሳርፈው ትእኖ ይኖራል፡፡ የልምምድ እቅዳችንን ወደ ኋላ ይጎትትብናል፡፡ አየር ማረፍያው ውስጥ በቆየንበት ወቅት ከተጫዋቾቹ ጋር በክፍተቱ ዙርያ ውይይት አድርገናል፡፡ አሁንም ያለንን ቀሪ ጊዜ ተጠቅመን ነገሮችን ለማስተካከል ጥረት እናደርጋለን፡፡ ››

‹‹ የገጠመን ቡድን በጣም ጠንካራ ነው፡፡ ጥሩ እግርኳስ መጫወት የሚችል እና በአካል ብቃት ጠንካራ የሆነ ቡድንን ነው የገጠምነው፡፡ ከዚህ የሄድነው ከቡድናችን አቋም ጭላንጭሉን ለማየት ነበር፡፡ ይህንን ውድድር ማለፍ ለቀጣይ ወጣቶች መነሳሳትን ይፈጥራል ብለን ለውጤቱም መስዋእትነት ለመክፈል ተነጋግረን ነው የገባነው፡፡ ››

‹‹ የሜዳ እንቅስቃሴው ከፍተኛ ጫና የነበረበት ነው፡፡ በፍጥነት እና በማጥቃት ላይ የተመሰረተ የጨዋታ ሲስተም ይዘው በመግባታቸው የተጋጣሚያችንን ፍጥነት በማውረድ ጨዋታውን ለማረጋጋት ሞክረናል፡፡ በጨዋታው ላይ ከነሱ እኩል መሯሯጥና መፎካከር ችለናል፡፡ በ90 ደቂቃ ውስጥ 1 ተጫዋች ብቻ ነው የቀየርነው፡፡ ይህም የልጆቻችንን ሙሉ ጨዋታ የመጫወት ብቃት አይተንበታል፡፡ በጨዋታው መጨረሻ አካባቢም በሎዛ አማካኝነት ጥሩ የግብ አጋጣሚ አግኝተን ለጥቂት ወደ ውጪ ወጥቶብናል፡፡ ››

‹‹ ከካሜሩን ይዘን በመጣነው ውጤት ምን መስራት እንደምንችል ጭላንጭሉን አሳይተናል፡፡ በሜዳችን የተሻለ ነገር ማሳየት ከቻልን ውጤት ይዘን መውጣት እችላለን፡፡ በቀላሉ ውጤት እናገኛለን ብለን አንገምትም፡፡ በቀላሉ ከውድድር እንወጣለን ብለንም አናስብም፡፡ ››

‹‹ የአዲስ አበባ ስታድየም ያለበት ሁኔታ ጥሩ ባለመሆኑ ጨዋታችንን በዚህ ስታድየም እናደርጋለን ብለን አናስብም ››

 

‹‹በአምበልነቴ የሚጠበቅብኝን ሃላፊነት ተወጥቻለሁ ›› ሎዛ አበራ (አምበል)

‹‹ አምበል መሆን ብዙ ኃላፊነት ይጠይቃል፡፡ የሚጠበቅብኝን ኃላፊነት በአግባቡ ተወጥቻለሁ፡፡ በሜዳ ውስጥም ሆነ ከሜዳ ውጭ ማድረግ የሚገባንን ነገር አድርገናል፡፡ ››

‹‹ ካሜሩን ከሄድንበት ጊዜ ጀምሮ ያለው የቡድ መንፈስ ጥሩ ነበር፡፡ ከሜዳ ውጭ 0-0 አቻ መውጣታችን ጥሩ ውጤት ነው፡፡ በቀጣይ ከአሰልጣኛችን ጋር ተነጋግረን ጥሩ ውጤት ለማምጣት እንጥራለን፡፡ ››

 

 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *