​በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የመጀመርያ ጨዋታ አል አህሊ እና ዋይዳድ አቻ ተለያይተዋል

በቶታል ካፍ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ አሌክሳንደሪያ ላይ የተጫወቱት አል አህሊ እና ዋይዳድ ካዛብላንካ 1-1 ተለያይተዋል፡፡ኢትዮጵያዊው ኢንተርናሽናል አርቢትር ባምላክ ተሰማ በመራው እና 50ሺ ደጋፊዎች በተከታተሉት ጨዋታ ባለሜዳዎቹ አህሊዎች ዋይዳድ ላይ ብልጫን ቢወስዱም ማሸነፍ ሳይችሉ ቀርተዋል፡፡  

በቦርጅ ኤል አረብ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ሁለቱም ክለቦች በግማሽ ፍፃሜ የተጠቀሙት የመጀመርያ 11 በፍፃሜው በአመዛኙ ተጠቅመዋል፡፡ ባለሜዳዎቹ አል አህሊዎች ቀዳሚ መሆን የቻሉት ገና ጨዋታው በተጀመረ በሶስተኛው ደቂቃ ነበር፡፡ ሞሜን ዛካሪያ ከፍፁም ቅጣት ምት ክልሉ አክርሮ ባስቆጠረው ግሩም ግብ የካይሮ ሃያሎቹ አጀማመራቸውን አሳምረዋል፡፡ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ሞሮኳዊው ኢንተርናሽናል ዋሊድ አዛሮ የአህሊን መሪነት የሚያሰፋበትን እድል ቢያገኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡

በጨዋታው ላይ አህሊዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይ ከመሆናቸው ባሻገር በተደጋጋሚ ወደ እንግዶቹ የግብ ክልል በመቅረብ ግብ ለማስቆጠር ሲጥሩ ዋይዳዶች በመከላከል ተጠምደው ነበር፡፡ በዚህ መሐል ነበር ዋይዳዶች በ17ኛው ደቂቃ ባልተጠበቀ መልኩ የአቻነት ግብ ማግኘት የቻሉት፡፡ የቡድኑ ቁልፍ የመስመር ተጫዋች መሃመድ ኦንዠም ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ አሽራፍ ቤንሻሪኪ ከአህሊ ተከላካዮች መሃል ሆኖ በግንባሩ በመግጨት ክለባቸውን ለማበረታታት ከሞሮኮ የተጓዙ ደጋፊዎችን አስፈንድቋል፡፡ ኦንዠም ከ10 ደቂቃዎች በኃላ በጉዳት ምክንያት አብደላዲም ካድሩፍ ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

በመጀመሪያው አጋማሽ ናይጄሪያዊው ጁኒየር አጃዬ ካመከናት እድል ውጪ የሚጠቀስ አደገኛ ሙከራ ሳይደረግ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል፡፡

በሁለተኛው አጋማሽ አህሊዎች እጅግ ጠንክረው የታዩ ሲሆን ባሳደሩት ጫና ምክንያትም ዋይዳዶች ሙሉ ትኩረታቸውን መከላከል ላይ እንዲተኩሩ አስገድዷቸዋል፡፡ አጃዬ እና አብደላ ኤል-ሰዒድ ያልተሳኩ የግብ ማግባት ሙከራዎችን ሲያደርጉ አንጋፋው አጥቂ ኢመድ ሞቲብ አህሊ አሸናፊ መሆን የሚችልበትን እድል ሳይጠቀምበት ቀርቷል፡፡
ጨዋታው 1-1 የተጠናቀቀ ሲሆን የመልስ ጨዋታው ከሳምንት በኃላ በካዛብላንካው ስታደ መሃመድ አምስተኛ ይደረጋል፡፡ ዋይዳድ ከ1992 በኃላ የአፍሪካ ቻምፒዮን ለመሆን የተሻለ እድል ቢኖረውም ከሜዳው ውጪ ተጋጣሚዎቹን ለማንበርከክ የማይቸገረው የ8 ግዜ የአፍሪካ ቻምፒዮኑ አል አህሊም በቀላሉ እጅ ይሰጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡ ሆኖም ውጤቱ ለዋይዳድ ካዛብላንካ መልካም የሚባል ነው፡፡

ኢትዮጵያዊው አርቢትር ባምላክ ተሰማ የፍፃሜውን ጨዋታ ተቆጣጥሮ በመምራት ጥሩ ነበር፡፡ አርቢትሩ ለሶስት የዋይዳድ ካዛብላንካ ተጫዋቾች (ሳላዲን ሰዒዲ፣ ብራሂም ናካሽ እና ዙሄርላሮቢ) የማስጠንቀቂያ ቢጫ ካርድ አሳይቷል፡፡ አርቢትር ባምላክ ከአየለ ተሰማ እና ደነቀው መንግስቱ በመቀጥል የካፍ የክለቦች ውድድር ፍፃሜ የመራ የመሃል ዳኛ መሆንም ችሏል፡፡

የፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ውጤት

አል አህሊ (ግብፅ) 1-1 ዋይዳድ ክለብ አትሌቲክ (ሞሮኮ)

3’ ሞሜን ዛካሪያ   |     17’ አሽራፍ ቤንሻሪኪ

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *