​ሱፐር ካፕ ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ| ቅዱስ ጊዮርጊስ ከ ወላይታ ድቻ

ጨዋታ፡ የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ

ተጋጣሚዎች፡ ቅዱስ ጊዮርጊስ (ሊግ) ከ ወላይታ ድቻ (ጥሎ ማለፍ)

ቦታ: አዲስ አበባ ስታድየም

ሰአት፡ 10:00

ዳኞች፡ አማኑኤል ኃ/ስላሴ (ዋና ዳኛ)፣ ትግል ግዛው እና በላቸው ይታዩ (ረዳቶች)፣ ለሚ ንጉሴ (4ኛ ዳኛ)


የኢትዮጵያ አሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ጨዋታ የአምና ፕሪምየር ሊግ ቻምፒዮኑ ቅዱስ ጊዮርጊስን ከኢትዮጵያ ዋንጫ ባለቤቱ ወላይታ ድቻ ጋር ያገናኛል። ነገ 10:00 ስለሚደረገው ፍልሚያ ዋና ዋና ነጥቦችም በዚህ ፅሁፍ ቀርበዋል፡፡


የቡድኖቹ ሰሞነኛ ሁኔታ 

ቅዱስ ጊዮርጊስ ከሳምንት በፊት በተጠናቀቀው የአዲስ አበባ ዋንጫ ተሳትፎው በፍፃሜው ኢትዮጵያ ቡናን በመርታት ሻምፒዮን መሆን መቻሉ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። ወላይታ ድቻ በበኩሉ በተከካፈለበት የደቡብ ካስቴል ዋንጫ ላይ በግማሽ ፍፃሜው በሲዳማ ቡና እንዲሁም በደረጃ ጨዋታው በፋሲል ከተማ ተሸንፎ በአራተኝነት አጠናቋል።

የፍፃሜው ጨዋታ ሁለት በለውጥ ላይ ያሉ ቡድኖችን እንደሚያገናኝ ይጠበቃል። ቅዱስ ጊዮርጊስ ከአሰልጣኝ ቫዝ ፒኒቶ መምጣት በኃላ በአጨዋወቱ ላይ ለውጥ በማድረግ ኳስን ከኃላ መስርቶ በመጫወት ዕድሎችን ለመፍጠር ሲሞክር ተስተውሏል። ወላይታ ድቻ በበኩሉ በተጨዋቾች ምልመላው ላይ ስር ነቀል ለውጥ አድርጓል። በቀደመው ጊዜ በጥቂት በጀት ይንቀሳቀስ የነበረው ድቻ ዘንድሮ በአፍሪካ ውድድር ላይ ተሳታፊ እንደመሆኑ በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጪ ተጨዋቾችን በማስፈረም ራሱን አጠናክሯል። የነገው የፍፃሜ ጨዋታም ክለቦቹ ከተስተዋለባቸው ለውጦች በኃላ የሚያደርጉት የመጀመሪያው የፉክክር ጨዋታ ይሆናል።


ጨዋታው ምን መልክ ሊኖረው ይችላል?

ሁለቱ ቡድኖች ሲገናኙ በብዛት በሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ወላይታ ድቻ በጥልቀት በመከላከል እና የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም በመሞከር እንዲሁም ቅዱስ ጊዮርጊስ አብዛኛውን ሰዐት በተጋጣሚው ሜዳ ላይ ክፍተትን ለማግኘት በመጣር የሚያደርጉት እንቅስቃሴ በነገውም ጨዋታ ላይ ይጠበቃል። 

በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ እንደተመለከትነው  በፖርቹጋላዊው አስልጣኝ ስር የግብ ዕድሎችን በብዙ የኳስ ንክኪዎች ለመፍጠር የሚነቀሳቀሰው ቅዱስ ጊዮርጊስ በቡድን ግንባታው በኩል በሂደት ላይ ይገኛል። የአሰልጣኙ ለቡድኑ አዲስ የሆኑ የጨዋታ ሀሳቦች በተጨዋቾች ዐዕምሮ ውስጥ ባልሰረፀበት እና አጨዋወቱ በሚጠይቀው መጠን ቡድኑ ባልተዋሀደበት ጊዜ ላይ እምብዛም ክፍተት ከማይሰጥ የተከላካይ ክፍል ጋር መግጠሙ እንዲቸገር ሊያደርገው ይችላል። ቡድኑ ለመተግበር እየጣረ በሚገኘውና የኳስ ቁጥጥር የበላይነትን በማግኘት ላይ በተመሰረተው አጨዋወት ከድቻ የተከላካይ መስመር ጀርባ ለመግባት በሁለተኛው የሜዳው አጋማሽ ላይ ስኬታማ የሆኑ በርካታ ቅብብሎችን ማድረግ ይጠበቅበታል። ሆኖም ከዚህ ይልቅ በአዲስ አበባ ዋንጫ ላይ እንደተመለከትነው በቡድኑ የቀደመ አጨዋወት ስልት ከመስመር አጥቂዎች እና መሀል ሜዳ አካባቢ ከሚቆሙት የመስመር ተከላካዮች የሚነሱ ቀጥተኛ ኳሶች የግብ ዕድል ምንጭ ሊሆኑ ይችላሉ።

የአሰልጣኝ መሳይ ተመራጭ የጨዋታ ቅርፆች በሶስት የመሀል ተከላካዮች ይጀምራሉ። አሰልጣኙ ቡድናቸው ጫና ውስጥ በሚገባባቸው እና ለመከላከል ቅድሚያ በሚሰጥባቸው ጨዋታዎች ደግሞ የመስመር ተመላላሾቻቸውንም ጭምር ወደ ኃላ በመግፋት የተከላካዮቻቸውን ቁጥር ወደ አምስት ከፍ በማድረግ ይታወቃሉ። በነገውም ጨዋታ ወላይታ ድቻ በአምስት ተጨዋቾች በተዋቀረ እና ከፊቱ በሁለት የአማካይ ተከላካዮች ሽፋን የሚሰጠው የኃላ መስመርን እንደሚጠቀም ይጠበቃል። ይህም ቡድኑ በተለይ በሜዳው ስፋት ተጋጣሚው የሚታወቅበትን ከመስመሮች የሚነሳ ጥቃት ለመመከት የተሻለ አማራጭ ሊሰጠው ይችላል። የሁለቱ አማካዮች ከተከላካይ መስመሩ ብዙም አለመራቅ ደግሞ ለተጋጣሚ የአጥቂ አማካዮች ክፍተትን የማይተው መሆኑ በሜዳው መሀል ለመሀል ተመስርተው የሚመጡ ኳሶችን ለማቋረጥ ይረዳል። ሆኖም ወደኃላ የሚሳበው የቡድኑ አጨዋወት የመልሶ ማጥቃት ዕድሎችን ለመጠቀም በተቃራኒ ሜዳ ላይ በቂ የሆነ የተጨዋቾች ቁጥር እንዳያገኝ እንቅፋት ሊሆንበት እንደሚችል ይገመታል።


አስተያየቶች

ፋሲል ተካልኝ (የቅዱስ ጊዮርጊስ ረዳት አሰልጣኝ)  

“የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ የምንፈልገው ዋንጫ ነው። በእርግጥ በ2009 የውድድር ዘመን መጨረሻ ጨዋታው ቢደረግ ጥሩ ነበር፡፡ አሁንም ቢሆን እንደ አንድ መዘጋጃ እናየዋለን፡፡ ደጋፊዎቻችንም ጨዋታውን እንድናሸንፍ ስለሚጠብቁ ለማሸነፍ የምንችለውን ሁሉ እናደርጋለን።

ጨዋታውን ማሸነፍ ለቀጣይ ውድድር የሚኖር መነሳሳት አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ ማሸነፍ ሁልጊዜ ቡድኖች ላይ የሚፈጥረው ተነሳሽነት አለ፡፡በማሸነፍ ውስጥ ጠንካራ ጎን ከማየት ባሻገር  ስህተቶችህን ታይበታለህ፡፡  ስለዚህ ማሸነፍ በለመደ ቡድን ውስጥ ስታሸንፍ ፣ ዋንጫ ስትወስድ በተጨዋቾቹ ላይ የሚያሳድረው ተፅእኖ ፣ በደጋፊዎቻችን ላይ የሚያመጣው የስነ ልቦና ተፅእኖ መልካም በአሰልጣኞችም ጭምር በመሆኑ የአሸናፊ አሸናፊ ዋንጫ ትልቅ የዋንጫ ጨዋታ ነው ። 

ስለተጋጣሚያችን ብዙም የማውቀው ነገር የለም፡፡ ሆኖም አዳዲስ ተጨዋቾች አስፈርመዋል፡፡ ድቻ በሊጉ ከመጣበት ጊዜ አንስቶ ተነሳሽነታቸው ከፍተኛ የሆነ ፣ ታክቲክ ላይ በጣም ትኩረት አድርገው የሚንቀሳቀሱ ናቸው። ቀላል ተጋጣሚ ይሆናሉ ብዬ አላስብም።

መሳይ ተፈሪ (የወላይታ ድቻ አሰልጣኝ)

ጥሩ ተነሳሽነት አለን፡፡ ሁሌም ለማሸነፍ ነው ወደ ሜዳ የምንገባው፡፡ ለጨዋታውም በቂ ዝግጅት አድርገናል። በጥንቃቄ እና በትኩረት በመጫወት ለማሸነፍ የሚቻለን ነገር ሁሉ እናደርጋለን። እሁድ ደጋፊዎቻችን የሚደሰቱ ይሆናል።  

በቁጥር ደረጃ በእርስ በእርስ ግኑኝነት በማሸነፍ ቅዱስ ጊዮርጊስ የተሻለ ነው። ጊዮርጊስ የምታከብረው ጥሩ የማሸነፍ ባህል ያለው ቡድን ነው። ቢሆንም ግን በዘጠና ደቂቃ ውስጥ የምታሳየው ብቃት ነው የሚወስነው፡፡ የእኛ ቡድን ከፍተኛ የሆነ የማሸነፍ ተነሳሽነት ላይ ይገኛል።


የቡድን ዜናዎች 

በወላይታ ድቻ በኩል የአጥቂ አማካዩ በዛብህ መለዮ፣ አጥቂው ዳግም በቀለ፣ ግብ ጠባቂው ወንድወሰን ገረመው እና የመስመር አማካዩ አምረላ ደልታታ በጉዳት ጨዋታው የሚያልፋቸው ተጫዋቾች ናቸው፡፡ በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል አዳነ ግርማ በቅጣት ፣ ናትናኤል ዘለቀ፣ በኃይሉ አሰፋ እና ታደለ መንገሻ በጉዳት የማይሰለፉ ተጫዋቾች ናቸው፡፡  


ግምታዊ አሰላለፍ

ቅዱስ ጊዮርጊስ (4-3-3)

ሮበርት ኦዶንካራ

አብዱልከሪም መሐመድ – ሳላህዲን በርጊቾ – ደጉ ደበበ – አበባው ቡታቆ 

ምንተስኖት አዳነ – ሙሉአለም መስፍን – አብዱልከሪም ኒኪማ

ኢብራሂማ ፎፋና – ሳላህዲን ሰዒድ – አቡበከር ሳኒ

ወላይታ ድቻ (3-5-2)

ኢማኑኤል ፌቮ 

ተክሉ ታፈሰ – ማሳማ አሴልሞ – ሙባረክ ሽኩሪ

እሸቱ መና – ኃይማኖት ወርቁ – ሒላሪ ኢኬና – ጸጋዬ ብርሀኑ – አሳልፈው መኮንን

ተመስገን ዱባ – ጃኮ አራፋት  


እውነታዎች 

-ቅዱስ ጊዮርጊስ ይህን ጨዋታ ካሸነፈ 16ኛ የሱፐር ካፕ ድሉን ያሳካል፡፡ በተቃራኒው ለወላይታ ድቻ በታሪክ የመጀመርያው ድል ይሆናል፡፡

– ሁለቱ ቡድኖች በአሸናፊዎች አሸናፊ ውድድር ሲገናኙ ይህ ለመጀመርያ ጊዜ ነው፡፡ በአጠቃላይ ሁለቱ ክለቦች 8 ጊዜ በፉክክር ጨዋታ ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 4 በማሸነፍ የበላይ ሲሆን ወላይታ ድቻ 1 ድል ብቻ አሳክቷል፡፡ በ3 ጨዋታ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል፡፡

በ1977 የተጀመረው ይህ ውድድር ለ25 ጊዜያት ሲካሄድ ቅዱስ ጊዮርጊስ 15 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ቀዳሚ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ቡና 5 ፣ ኤሌክትሪክ 3 ጊዜ ዋንጫውን በማንሳት ይከተላሉ፡፡

ውድድሩ በተለያዩ ምክንያቶች ለ10 ጊዜያት ያህል መካሄድ ያልቻለ ሲሆን በመንግስት ለውጥ ወቅት (በ1983 እና 1984) ፣ አንድ ክለብ ሁለቱንም ዋንጫ በማሸነፉ ምክንያት ( 1991፣ 1993 ፣ 2001 እና 2008) በክለቦች እና ፌዴሬሽኑ ውዝግብ (1999) ያልተካሄዱ አመታት ናቸው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ  በ2004 ፣ 2005 እና 2006 በጊዜ መጣበብ እና ሌሎች ያልታወቁ ምክንያቶች የአሸናፊዎች አሸናፊ ዋንጫ ሳይደረግ ቀርቷል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *