​የእለቱ ዜናዎች፡ ሰኞ ጥቅምት 27 ቀን 2010

ኢትዮጵያ ቡና

አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች በይፋ የኢትዮጵያ ቡና አሰልጣኝ ሆነው ተሹመዋል፡፡ አሰልጣኙ ወደ ኢትዮዽያ ከመጡ የሳምንት ጊዜ ቢሆናቸውም እስካሁን የልምምድ ሜዳ በመገኘት የቡድኑ አባላትን ከመተዋወቃቸው በቀር ስራቸውን በይፋ ያልጀመሩ የቆዩ ሲሆን ዛሬ 10:00 ላይ ቡድኑ በኒያላ ሜዳ ባደረገው ልምምድ የማሰልጠን ስራቸውን ጀምረዋል፡፡ እስካሁን የመዘግየታቸው ምክንያት ድርድሩ በቶሎ አለመጠናቀቁ እንደሆነ ክለቡ ሲያስታውቅ የ2 አመት ኮንትራት መፈራረማቸውም ይፋ ሆኗል፡፡

ምክትል አሰልጣኙ ገዛኸኝ ከተማ ወደ ሌላ ስራ ያሸጋሸገው ክለቡ ለአሰልጣኝ ፓፒች ረዳት በመሆን አሰልጣኝ ሐብተወልድ ደስታ እንደሚሰሩ እና በቴክኒክ ዳሬክተሩም እገዛ እንደሚደረግላቸው ሰምተናል።


ጅማ አባ ጅፋር

ጅማ አባ ጅፋር ከከፍተኛ ሊግ ወደ ፕሪምየር ሊግ መግባቱን ተከትሎ የጅማ ከተማ አስተዳደር የገንዘብ እና የመሬት ሽልማት ለተጫዋቾቹና ለቡድኑ አባላት እንደሚሰጥ ቃል መግባቱ ይታወቃል። ሆኖም እስካሁን በተለያዩ ምክንያቶች ቃል የተገባው ሽልማት አለመፈፀሙን ቃል የተገባላቸው አካላት ለሶከር ኢትዮዽያ ገልፀዋል፡፡ ይህን ቅሬታ ይዘን ወደ ጅማ አባጅፋር ክለብ አመራሮች ጥያቄ ያቀረብን ሲሆን ቃል የተገባላቸው የገንዘብ ክፍያ ሊፈፀም የቃለ ጉባዔ ፊርማ ብቻ እንደቀረና ሌሎች የሚፈልጉት ቅድመ ሁኔታዎች ሲሟሉ በሂደት እንደሚፈፅሙ ተገልፆልናል፡፡


ሴቶች ፕሪምየር ሊግ

ፋሲል ከተማ እና ሻሸመኔ ከተማ የሴቶች ቡድን አቋቋሙ። ከዚህ ቀደም የሴቶች ቡድን ያልነበራቸው እነዚህ ክለቦች ለኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን የእንሳተፍ ጥያቄ በደብዳቤ ማቅረባቸው ሲታወቅ ፌዴሬሽኑ በምላሹም ጉዳዩን ትኩረት እንደሰጠበት፣ የሴቶች እግርኳስ እንዲስፋፋ እንደሚፈልግና የሴቶች ፕሪምየር ሊግ የዕጣ ማውጣት ስነ ስርአት ላይ ወደፊት በአዲስ መልክ የሚመጡ ክለቦች ካሉ እንደሚያስተናግድ መግለፁን ተከትሎ በቅርቡ ሁለቱ ክለቦችን በአዲስ መልክ የሁለተኛ ዲቪዚዮን መርሀ ግብር ውስጥ እንደሚካተቱ ታውቋል።


ኤፍሬም ዘካርያስ

ኤፍሬም ዘካርያስ በአንድ አመት ኮንትራት አዳማ ከተማን ተቀላለቀለ። ከሀዋሳ ከተማ እና በኢትዮ ኤሌትሪክ መካከል ባለፈው አመት ከተካሄደው ጨዋታ በፊት ውጤት ለማስቀየር መሪ ተዋናይ ነው በማለት ክለቡ ሀዋሳ ከተማ 2 አመት እና የገንዘብ ቅጣት ቢጥልበትም ፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ ተጨዋቹ ነፃ ነው በማለት ማሰናበቱ ይታወቃል። በዚህም ምክንያት ኤፍሬም ዘካርያስ በነፃ ዝውውር አዳማ ከተማን ሲቀላቀል ቅዳሜ ከወልድያ በነበረው የፕሪምየር ሊግ ጨዋታ ላይ በ72ኛው ደቂቃ ተቀይሮ በመግባት የመጀመርያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል።


ወልዋሎ

የወልዋሎ አዲግራት ዩኒቨርሲቲ ሜዳ ለጨዋታ አመቺ አይደለም በማለት ክለቦች ጥያቄ እያቀረቡ ይገኛል። እሁድ የኢትዮዽያ ፕሪምየር ሊግ የመጀመርያ ሳምንት ሜዳው ጨዋታ የተካሄደበት ሲሆን መጠነኛ ዝናብ መዝነቡን ተከትሎ ሜዳው ላይ ጨዋታ ከመጀመሩ አስቀድሞ የተለያዩ ጥገናዎች ሲደረጉበት የነበረ ሲሆን ይህን መሰረት አድርገን ለፌዴሬሽኑ ባቀረብነው ጥያቄ የሜዳውን ተገቢነት በተመለከተ ጉዳዩን እያጤነበት እንደሆነና በቅርቡ ሜዳውን በተመለከተ ምላሽ እንደሚሰጥበት ታውቋል።

በተያያዘ ዜና ትላንት የወልዋሎ ከፋሲል ከተማ ባደረጉት የመጀመርያ ሳምንት ጨዋታ ላይ የተፈጠረው የስፖርታዊ ጨዋነት ጉድለት ፌዴሬሽኑን እንደሚያሳስበው ገልፆ የኮሚሽነሩን ሪፖርት ተከትሎ አስፈላጊውን የእርምት ውሳኔ እንደሚሰጥ ሰምተናል።


የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር

የኢትዮዽያ ቡና ደጋፊዎች ማህበር ጠቅላላ ጉባኤ ህዳር 10 በአምባሳደር አዳራሽ ከጠዋቱ 03:00 ጀምሮ የክለቡ የቦርድ አመራሮች ፣ ደጋፊዎች በተገኙበት እንደሚካሄድ የደጋፊ ማህበሩ ፕሬዝደንት አቶ ክፍሌ አማረ ተናግረዋል ። በጠቅላላ ጉባኤው ላይ ከሚነሱ አጀንዳዎች መካከል በዋናነት አዲስ የስራ አስፈፃሚ ምርጫ ከመደረጉ ባሻገር በስፖርታዊ ጨዋነት ዙርያ ሰፊ ውይይት እንደሚደረግ ገልፀዋል።


ብሔራዊ ቡድን

የኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በቻን ውድድር  የግብፅን ቦታ ተክቶ ለመግባት ትላናት የመጀመርያ ጨዋታውን ከሩዋንዳ አቻው ጋር አድርጎ 3 – 2 መሸነፉ ይታወቃል። ከጨዋታው አስቀድሞ ከተመዘገቡት 18 ተጨዋቾች መካከል 10 የፓስፖርት ችግር አጋጥሟቸው የነበረ መሆኑ ሲታወቅ በተደረገ ከፍተኛ ጥረት ለጨዋታ እንዲቀርቡ መደረጉ ተሰምቷል። ችግሩ የተከሰተው ተጨዋቾቹ አዲስ ፓስፖርት ሲያወጡ ቀድሞ ከነበረው ፓስፖርት የዕድሜ ልዩነት መፈጠሩ ሲሆን የዕለቱ ኮሚሽነርን የማሳመን ከፍተኛ ጥረት ባይደረግ ኖሮ ኢትዮዽያ የመጀመርያ 11 ተጨዋቾችን የማግኘት እድሏ ጠባብ ሊሆን እንዲሁም ጨዋታውን በፎርፌ የምትሸነፍበት እድል ሰፊ ነበር።

በተያያዘ ዜና ብሔራዊ ቡድኑ ዛሬ በእረፍት ምክንያት ልምምድ እደማይሰራ የታወቀ ሲሆን ከነገ ጀምሮ ለመልሱ ጨዋታ ዝግጅቱን እንደሚጀምር ተነግሯል፡፡ የተወሰኑ ተጫዋቾችም ለክለባቸው አገልግሎት እንዲሰጡ ወደ የክለቦቻቸው እንዳመሩ ለማወቅ ችለናል። ከነዚህም መካከል ትላንት ሙሉ 90 ደቂቃ የተጫወተው ጌታነህ ከበደ ዛሬ ክለቡ ከወላይታ ድቻ ጋር ባደረገው ጨዋታ ሙሉ ክፍለ ጊዜ ተጫውቷል፡፡ ቡድኑ ለመልሱ ጨዋታ ብሔራዊ ቡድኑ አርብ ወደ ሩዋንዳ እንደሚያቀና ሰምተናል።


ጠቅላላ ጉባኤ

ጥቅምት 30 ሊደረግ ቀጠሮ የተያዘለት የኢትዮዽያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ጠቅላላ ጉባኤ ከወዲሁ አስገራሚ ነገሮች በየዕለቱ እየተከሰቱበት ይገኛል። ዛሬ የተሰማው ዜና ደግሞ ከአምስቱ የፕሬዝደንት ምርጫ እጩ ውስጥ መካከል አንድ ግለሰብ ለፊፋ ደብዳቤ እንዳስገቡ ተሰምቷል ። እንዳገኘነው መረጃ ከሆነ የደብዳቤው ይዘት ጠቅላላ ጉባኤው በሚካሄድበት ጥቅምት 30 ቀን ምርጫው እንዲደረግ ፊፋን መጠየቅ መሆኑን ሰምተናል። ፊፋ ባሳለፍነው ሳምንት ጠቅላላ ጉባኤው በተባለው ቀን እንዲካሄድ እና ምርጫው እንዲዘገይ ማሳሰቡ ይታወሳል።


ደምሴ ዳምጤ

በስፖርት ጋዜጠኝነት ረጅም አመት በትጋት ያገለገለው ተወዳጁ ጋዜጠኛ ደምሴ ዳምጤ ህልፈተ ሞቱ የተሰማው ልክ የዛሬ  አመት ጥቅምት 26 ሲሆን ግብአተ መሬቱ የተፈፀመው ደግሞ ልክ የዛሬ 5 አመት በዛሬው ዕለት ነበር።


ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ኢትዮ ኤሌትሪክ ያለ አግባብ ስሜ ጠፍቷል በሚል ወደ ህግ ሊያመራ እንደሆነ ተሰምቷል። የሀዋሳ ከተማ  እና የኢትዮ ኤሌትሪክ ጨዋታ ከመካሄዱ አስቀድሞ የጨዋታ ውጤት ለማስቀየር ተሞክሯል በሚል የተለየዩ መረጃዎች ሲወጡ እንደነበር ይታወሳል፡፡ ጉዳዩን ፀረ ሙስና ኮሚሽን ለአቃቢ ህግ ቢልከውም አቃቢ ህግም ሆነ የፌዴሬሽኑ ዲሲፒሊን ኮሚቴ በመጨረሻው ውሳኔ ላይ ምንም አይነት በወንጀልም ሆነ በዲሲፒሊን ኮሚቴ የሚያስጠይቅ ድርጊት አልተፈፀመም በማለት ያሳለፈውን ውሳኔ ተከትሎ ከኢትዮ ኤሌትሪክ ክለብ እየተሰማ እንዳለው መረጃ ከሆነ የተቋሙን እና የክለቡን ስም አጉድፈዋል ባላቸው አካላት ላይ ክስ ሊመሰርት እንደሆነ ታውቋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *