​ሪፖርት | ደደቢት የአመቱን የመጀመሪያ ሶስት ነጥብ አስመዘገበ

የሦስተኛው ሳምንት የሊጉ ጨዋታዎች ዛሬ ቀጥለው ሲደረጉ 9:00 ላይ ሀዋሳ ከተማን ያስተናገደው ደደቢት በጌታነህ ከበደ እና አቤል ያለው ጎሎች 2-1 አሸንፏል።

የጌታነህ ከበደን መመለስ ተከትሎ ፋሲካ አስፋውን ወደ ተጠባባቂ ወንበር ያወረደው ደደቢት ጨዋታውን በ4-4-2 አሰላለፍ ጀምሯል። ፍሬው ሰለሞንን እና ደስታ ዮሀንስን ከቤሔራዊ ቡድን ግዳጅ መልስ ያገኘው ሀዋሳ ከተማ በበኩሉ ለሙላለም ረጋሳ የመጀመሪያ የመሰለፍ ዕድል በመስጠት እና ዳዊት ፍቃዱን በብቸኛ አጥቂነት በማሰለፍ በ4-2-3-1 ቅርፅ ቀርቧል።

ጨዋታው በሀዋሳ ከተማዎች የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ሲጀምር በመጀመሪያዎቹ አስር ደቂቃዎች ሁለቱም ቡድኖች ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል ዘልቀው ሳይገቡ እና ጨዋታው ኢላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎች ሳያስተናግድ ዘልቋል። በሂደት ፍሬው ሰለሞን በተሰለፈበት ቀኝ መስመር ባጋደለ የማጥቃት እንቅስቃሴ የደደቢትን የኃላ ክፍል ማስጨነቅ የጀመሩት ሀዋሳዎች ሙከራዎችን በማድረግ ቅድሚያውን ወሰዱ። 10ኛው ደቂቃ ላይ ከሳጥን ውጪ ፍሬው ሞክሮት ኩሊባሊ ተደርቦ የመለሰውን ኳስ ዳዊት ፍቃዱ በድጋሜ አክርሮ ሲመታ  የግቡ ቋሚ አጥቶበታል። በዚህ መልኩ የተነቃቁት ሀዋሳዎች ከአራት ደቂቃዎች በኃላ በተመሳሳይ መልኩ ታፈሰ ሰለሞን ከ ደደቢት ሳጥን ውስጥ ባገኘው እና አክርሮ በመታት ባስቆጠረው ጎል ቀዳሚ ሆኑ።  የሀዋሳዎች የመሀል ሜዳ የበላይነት በጨዋታው ቀጥሎ 24ኛው ደቂቃ ላይ ዳዊት ፍቃዱ ክሌመንትን ካታለለ በኃላ የሞከረው ኳስ በሚያስገርም መልኩ በግቡ አናት ወጣ እንጂ የቡድኑ መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ሊል ተቃርቦ ነበር።

የመሀል ብልጫ የተወሰደባቸው ደደቢቶች በሁለቱ አጥቂዎቻቸው እንቅስቃሴ እድሎችን ለመፍጠር ቢሞክሩም እስከ 28ኛው ደቂቃ ድረስ ስኬታማ መሆን አልቻሉም ነበር። በዚሁ ደቂቃ አቤል ያለው በአስገራሚ ብቃት የሀዋሳ ተከላካዮችን አልፎ የሞከረውን እና ተክለማሪይም የተፋውን ኳስ ጌታነህ ከበደ አስቆጥሮ ቡድኑን አቻ ማድረግ ችሏል። ከደቂቃዎች በኃላም በግራ መስመር አማካይነት ጨዋታውን የጀመረው እና 30ኛው ደቂቃ ላይ ከሽመክት ጋር ቦታ የተቀያየረው አቤል እንዳለ በሰነጠቀለት ድንቅ ኳስ ጌታነህ ከተክለማሪያም ጋር ፊት ለፊት ቢገናኝም ሳይጠቀምበት ቀርቷል።

33ኛው ደቂቃ ላይ ያቡን ዊልያምን በዮሀንስ ሴጌቦ ቀይረው ያስገቡት ሀዋሳዎች አሰላለፋቸውን ወደ 4-3-3 በመቀየር ደስታ ዮሀንስን ወደ ግር መስመር አማካይነት ሲመልሱት ዳዊት ድቃዱን ወደ ግራ መስመር አጥቂነት በማውጣት ለያቡን ዊልያም የፊት አጥቂነቱን ሀላፊነት ሰጥተውታል። ከቅያሪው በኃላ በነበሩት የመጀመሪያው አጋማሽ ቀሪ ደቂቃዎችም ሀዋሳ የቀደመውን የመሀል ሜዳ የበላይነቱን መልሶ ማግኘት አቅቶት ጨዋታውም በተደጋጋሚ የሜዳ ላይ ግጭቶች እና ጉዳቶች እየተቆራረጠ ሄዶ ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ ሲጀመር ኤፍሬም አሻሞን እና ፋሲካ አስፋውን በአቤል እንዳል እና ያብስራ ተስፋዬ ቀይረው ያስገቡት ደደቢቶቹ በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች የተሻለ ጫና ፈጥረዋል። 51ኛው ደቂቃ ላይም አቤል ያለው በግል ጥረቱ ይዞት የገባውን ኳስ ወደ ግብነት ቀይሮ ደደቢትን መሪ ማድረግ ችሏል። ከሁለት ደቂቃዎች በኃላም የጌታነህ እና የአቤል ጥምረት የፈጠረውን ዕድል ተክለማሪያም ሁለት ጊዜ አዳነው እንጂ ሀዋሳ ሶስተኛ ግብ ሊያስተናግድ ተቀርቦ ነበር። በመጀመሪያዎቹ 30 ደቂቃዎች የነበረውን የኳስ ቁጥጥር የበላይነት እያጣ የመጣው የሀዋሳ የአማካይ ክፍል የሚፈጥራቸው የጎል ዕድሎች እና አጠቃላይ የማጥቃት እንቅስቃሴው ተዳክሞ ታይቷል። 60ኛው ደቂቃ ላይ አዲስአለም በረጅሙ የላከለትን ኳስ ፍሬው ሞክሮ ወደውጪ ከወጣበት አጋጣሚ ሌላም ቡድኑ በሁለተኛው ግማሽ ይህ ነው የሚባል ሙከራ ሳያደርግ ጨዋታውን አገባዷል። 68ኛው ደቂቃ ላይ አለምአንተ ካሳን በአቤል ያለው ቀይሮ ያስገባው ደደቢትም የመሀል ክፍሉ በተጋጣሚ ተመሳሳይ ክፍል ላይ የቁጥር ብልጫ እንዲያገኝ ቢያደርግም የግብ ዕድሎችን ሲፈጥር አልታየም። ይልቁኑም የቁጥር ብልጫው የሀዋሳን የመሀል ክፍል የኳስ ፍሰት እንዲቆራረጥ ረድቶት ነበር። ሆኖም እየተዳከመ የመጣው እና የመጀመሪያ ውበቱን ያጣው ጨዋታ የውጤት ለውጥ ሳይታይበት በደደቢት አሸናፊነት ተገባዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *