​ሪፖርት ፡ ፋሲል ከተማ ከሜዳው ውጪ ወሳኝ 3 ነጥቦች አሳክቷል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 3ኛ ሳምንት ጅማ ላይ ጅማ አባጅፋር እና ፋሲል ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በፋሲል ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት የጅማ አባጅፋር ክለብ ለፋሲል ከተማ ያዘጋጀውን የማስታወሻ ስጦታ በቡድን አባላቶቹ አማካይነት አስረክቧል፡፡

የመጀመሪያው የጨዋታ አጋማሽ ሳቢ የጨዋታ እንቅስቃሴ የታየበት ነበር፡፡ ጅማ አባ ጅፋሮች በሁለቱም መስመሮች በመጠቀም ተጭነው ለማጥቃት ሲሞክሩ የተስተዋለ ሲሆን በተቃራኒው ፋሲል ከተማዋች ተጠቅጥቀው በመከላከል ላይ መሰረት አድርገው ተጫውተዋል፡፡
በፈጣን እንቅስቃሴ በተጀመረው በዚህ ጨዋታ ቡድኖቹ ወደ ጎል ለመቀርብ የፈጀባቸው 2 ደቂቃ ብቻ ነበር፡፡ የመጀመሪያውን ሙከራ በማድረግ ፋሲሎች ቅድሚያ ሲወስዱ አብዱራማህን ሙባረክ ከኤፍሬም አለሙ የተሻገረትን ኳስ በአግባቡ ተቋጣጥሮ ወደጎል ሲሞክር የጅማ አባጅፋር ግብ ጠባቂ ዳምኤል አጄይ አድኖበታል፡፡

7ኛው ደቂቃ ላይም እንዲሁ ፋሲል ከተማዋች በአንድ ሁለት ቅብብል ካለፉ በኃላ አብዱራማን ሙባረክ ወደ ግብ አክርሮ የመታትን ኳስ የጅማ አባጅፋር ግብ ጠባቂ ዳንኤል አጄይ ሲተፋት ፤ ኳሷ ተዘናግተው በነበሩት የጅማ አባጅፋር ተከላካዮች እግር መሀል አልፋ ነፃ አቋቋም ላይ በነበረው ፊሊፕ ዳውዝ አማካይነት በቀላሉ ወደ ግብነት ተለውጣለች። ሆኖም ግብ አስቆጣሪው ዳውዝ በ23ኛው ደቂቃ ላይ በመጉዳቱ በመሐመድ ናስር ተቀይሮ ከሜዳ ወጥቷል፡፡

ግቧ ከተቆጠረች በኋላ መረጋጋት ተስኗቸው የታዩት አባ ጅፋሮች የተሻለ ግብ ሙከራ ለማድረግ እስከ 35ኛው ደቂቃ ጠብቀዋል፡፡ ሳምሶን ቆልቻ ከሄኖክ አዱኛ የተሻገረውን ኳስ በግንባሩ ገጭቶ ግብ ጠባቂው ያዳነበት፣ በ41ኛው ደቂቃ እንዳለ ደባልቄ እና አሚኑ ነስሩ አንድ ሁለት ተቀባብለው የፋሲል ተከላካዮችን በማለፍ አሚኑ ወደ ግብ ሲመታ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት እንዲሁም የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ እንዳለ ደባልቄ ሞክሯት ሳማኬ ያዳናት ኳስ የጅማ ተጠቃሽ ሙከራዎች ነበሩ፡፡

ከእረፍት መልስ 54ኛው ደቂቃ ላይ ሄኖክ አዱኛ በሞከረው ሙከራ አቻ ለመሆን ጥረት የጀመሩት አባ ጅፋሮች ተደጋጋሚ የግብ ሙከራዎችን በዚህ ክፍለ ጊዜ ማድረግ ችለው ነበር፡፡ በ66ኛው ደቂቃ ላይ እንዳለ ደባልቄ በግራ መስመር ሁለት የፋሲል ተጨዋቾችን በማለፍ ያሻማውን ኳስ ሳምሶም ቆልቻ በነፃ አቋቋም ሆኖ ቢያገኛትም ሳይጠቀምባት ቀርቷል፡፡ በ78ኛው ደቂቃ ላይም የፋሲል ተከላካዮች በሰሩት ስህተት ያገኘውን ኳስ እንዳለ ደባልቄ ነፃ ሆነው ለነበሩት የቡድን አጋሮቹ ያቀብላል ተብሎ ሲጠበቅ ራሱ ሞክሮ የግብ አግዳሚውን ታኮ ወጥቶበታል። እነዚህ የግብ አጋጣሚዎችም  ጅማ አባጅፋርን ወደ ጨዋታው ሊመልሱ የሚችሉ ነበሩ፡፡

ከዕረፍት መልስ ሙሉ ለሙሉ የመከላከል እቅድን ይዘው የገቡት ፋሲሎች በተከላካይ መስመራቸው ላይ ስራ በዝቶባቸው ውለዋል፡፡ በ61ኛው ደቂቃ ላይ በረጅሙ የተሻገረለትን ኳስ ተጠቅሞ አብዱራህማን ሙባረክ ከሞከረው ሙከራ ውጪም ፋሲሎች ተጠቃሽ ሙከራ ሳያደርጉ ቀርተዋል፡፡ ጨዋታውም በእንግዶቹ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

የአሰልጣኞች አስተያየት

ምንተስኖት ጌጡ (ፋሲል ከተማ)

‹‹የሁለታችንም ጨዋታ ማራኪ ነበር፡፡ የጅማ አጨዋወት ከመስመር የሚነሳ በመሆኑ የነሱን እንቅስቃሴ ማስቆም የመጀመሪያው ዓላማችን ነበር፡፡ እሱም ተሳክቶልናል፡፡ ዛሬ ኳስ ይዘን መጫወት ባንችልም በባለጋራ ሜዳ ይህን ነጥብ ይዘን መውጣት ትልቅ ነገር ነው፡፡ እንዳየኸው አጥቂያችን ተጎድቶ መውጣቱ የራሱ አሉታዊ አስተዋፁ አለው፡፡ በአጠቃላይ ቡድናችን ለማሸነፍ ያለው ተናሳሽነትና ኳስን ይዞ ለመጫወት የሚደርጉት ጥረት ትልቅ ጥንካሬያችን ነው፡፡ የጅማ ህዝብ እንግዳ ተቀባይ እና ኳስ ለሚጫወት ቡድን ድጋፍ የሚደርግ ስለነበር በጣም እናመስግናለን፡፡ ለድላችን የደጋፊያችን አስተዋፅኦ የአንበሳውን ድርሻ ይወስዳል፡፡ ለዚህም ደጋፊዎቻችንን ላመሰግን እወዳለሁ፡፡ ››

ገብረመድህን ኃይሌ (ጅማ አባ ጅፋር)

‹‹ሙሉ 90 ደቂቃው አስጨናቂ ነበር፡፡ በሜዳችን አሸንፈን ለመውጣት ያደረግነው ጥረት በመጀመሪያዋቹ ደቂቃዎች በተቆጠረው ግብ በመዳናገጣችን ሳይሳካ ቀርቷል፡፡ ከዛ በኃላ ግን ያገኘናቸውን አጋጣሚ ሳንጠቀም ቀርተናል፡፡ እነሱ ደሞ ያገኟትን አጋጣሚ ተጠቀሙበት፡፡ እንግዲህ የኳስ ተፈጥሮ እንደዚህ ነው፡፡ እኛ ባቀድነው መሰረት መሄድ አልቻልንም፡፡ በሚቀጥሉት ጊዜያት እናስተካክላለን፡፡ የፋሲል ጥሩ ስብስብ የኛን ታክቲካል ስህተት በአግባቡ ተጠቀሞበታል>>

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *