ኤሌክትሪክ በቃል ደረጃ ከስምምነት ላይ የደረሳቸውን ተጫዋቾች ፌዴሬሽን ወስዶ ማስፈረሙን በመቀጠል ዛሬ ደግሞ አሸናፊ ሽብሩን የግሉ አድርጓል፡፡ ተጫዋቹ የ2 አመት ኮንትራት ለመፈረም 1.2 ሚልዮን እንደተከፈለው ታውቋል፡፡
ባለፉት 2 አመታት በወላይታ ድቻ የአማካይ መስመር ላይ ከብሩክ ቃልቦሬ ጋር በፈጠሩት ምርጥ ጥምረት የብዙ ተመልካቾችን ቀልብ የሳበው አሸናፊ የኮንትራቱን መጠናቀቅ ተከትሎ እንደ አብዛኛዎቹ የድቻ ተጫዋቾች ክለቡን ለቆ ወደ ኤሌክትሪክ ማምራቱን አረጋግጧል፡፡ ሌላው የድቻ ተከላካይ ተስፋዬ መላኩም በቀጣይ ቀናት ለኤሌክትሪክ ፊርማውን እደመያኖር ይጠበቃል፡፡
አሸናፊ 4ኛው የኤሌክትሪክ አዲስ ፈራሚ በመሆን ቡድኑን ተቀላቅሏል፡፡ ከሱ በፊት ብሩክ አየለ ፣ አለምነህ ግርማ እና ሃታሙ መንገሻ ከቀዮቹ ጋር የ2 አመት ኮንትራት ተፈራርመዋል፡፡ አዲስ ነጋሽ ፣ በኃይሉ ተሻገር ፣ አሳልፈው መኮንን ፣ አወት ገ/ሚካኤል ፣ በረከት ተሰማ እና ገመቹ በቀለ ደግሞ በክለቡ ለመቆየት ውላቸውን ያደሱ ተጫዋቾች ናቸው፡፡