አርባምንጭ ከነማ ከዋና አሰልጣኙ አለማየሁ አባይነህ ጋር ከተለያየ በኋላ ቀጣዩ አሰልጣኝን ለመቅጠር እቅስቃሴ እያደረገ እንደሆነ ከክለቡ የሚወጡ መረጃዎች አመልክተዋል፡፡
በዝውውር መስኮቱ እምብዛም እንቅስቃሴ ማድረግ ያልቻለው አርባምንጭ ስሙ ከቡራዩ ከነማው አሰልጣኝ ጳውሎስ ፀጋዬ ጋር ስሙ የተያያዘ ሲሆን አሰልጣኙ ወደ ትውልድ ከተማው ክለብ መመለስ የሚፈልግ በመሆኑና ከፍተኛ ወጪ የማያስወጣ በመሆኑ ክለቡን ሊይዝ ይችላል ተብሎ ቢጠበቅም ክለቡ በሃሳብ ደረጃ እንጂ አሰልጣኙን ለማስፈረም እንቅስቃሴ እንዳልጀመሩ ተነግሯል፡፡ ቡድኑ ተስፋዬ ፈጠነን ከመሳሰሉ አሰልጣኞች ጋር ስሙ ቢያያዝም የአለማየሁ ረዳት አሰልጣኝ ሆኖ ሲያገለግል የነበረው ግርማ ካሳዬን ዋና አሰልጣኝ አድርጎ ለመሾም እንዳሰበ ተነግሯል፡፡
አሰልጣኝ ግርማ በተጫዋችነት ዘመናቸው ኃይል በቀላቀለ አጨዋወታቸው ምክንያት ‹‹ቄራ›› የሚል ቅፅል ስም የወጣላቸው ሲሆን በአብዛኛው ስፖርት ቤተሰብ ተለይተው የሚታወቁትም በከፍተኛ ድምፅ ለተጫዋቾች ትእዛዝ በመስጠትና ከተጠባባቂ ወንበር ውጪ መሬት ላይ በመቀመጥ በስሜት ጨዋታ የሚመለከቱበት መንገድ ነው፡፡
ክለቡ አመታዊ በጀታቸው አነስተኛ ከሆኑ የሊግ ክለቦች ግንባር ቀደሙ ሲሆን የአሰልጣኝ ሽግሽግ በማድረግ እና ብሄራዊ ሊግ ተጫዋቾችን በማስፈረም አነስተኛ በጀቱን ያብቃቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡