​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ሀ | ሰበታ ሁለተኛ ተከታታይ ድሉን ሲያስመዘግብ አክሱም በጎል ተንበሽብሿል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ የምድብ ለ 2ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ በተደረጉ 7 ጨዋታዎች ቀጥለው ሲውሉ ሰበታ ከተማ ፣ ለገጣፎ ፣ መድን ፣ አአ ከተማ ፣ ቡራዩ ከተማ እና አክሱም አሸንፈዋል።

ሰበታ ላይ የመጀመርያውን ሳምንት በድል ባጠናቀቁት ሰበታ ከተማ እና አማራ ውሃ ስራ መካከል የተደረገው ጨዋታ በስዩም ከበደ በሚሰለጥነው ሰበታ ከተማ አሸናፊነት ተጠናቋል።

በመጀመርያው አጋማሽ ተጭነው የተጫወቱት ሰበታዎች በ2ኛው ደቂቃ በጌቱ ኃይለማርያም ፣በ21ኛው ደቂቃ በዓቢይ ቡልቲ ፣ በ34ኛው ደቂቃ በዜናው ፈረደ እንዲሁም በ35ኛው ደቂቃ በኄኖክ መሀሪ አማካኝነት ያደረጓቸው ሙከራዎች ፍሬያማ ያልሆኑ ሲሆን 38ኛው ደቂቃ ላይ ዓቢይ ቡልቲ ከሔኖክ ካሳሁን የተሻገረለትን ኳስ ወደ አክርሮ በመምታት ባለሜዳዎቹን ቀዳሚ ማድረግ ችሏል።

በመጀመርያው አጋማሽ እምብዛም የግብ ሙከራ ማድረግ ያልቻሉት አውስኮዶች በ24ኛው ደቂቃ ካርሎስ ዳምጠው እና በ41ኛው ደቂቃ በይታያል ዳኛቸው አማካኝነት ካደረጓቸው ሙከራዎች ውጪ እምብዛም የሰበታን የግብ ክልል ሳይፈትሹ ወደ እረፍት አምርተዋል።

ከዕረፍት መልስ አማራ ውሃ ስራ የአቻነት ጎል ለማግኘት የተሻለ እንቅስቃሴ ማድረግ የቻሉ ሲሆን በ48ኛው ደቂቃ ተዘራ መንገሻ እና በ74ኛው ደቂቃ አብዱልከሪም ቃሲም ለጎል የቀረበ ዕድል መፍጠር ችለው ነበር፡፡

ሰበታ ከተማዋች ከዕረፍት መልስ ኳስን በመሀል ሜዳ እና በራሳቸው የሜዳ አጋማሽ በማንሸራሸር አዘነበለው የቆዩ ሲሆን በ81ኛው ደቂቃ ላይ ዜናው ፈረደ ሁለት ተጫዋቾችን በማለፍ የመታው ኳስ ወደ ግብነት ተለውጦ የሰበታን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ጨዋታውም በሰበታ 2-0 አሸናፊነት ተጠናቋል፡፡

በሌሎች የምድብ ሀ ጨዋታዎች ወሎ ኮምቦልቻ ከ ባህርዳር ከተማ ያደረጉት የሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ያለግብ በአቻ ውጤት ተፈፅሟል። አክሱም ላይ አክሱም ከተማ ሱልልታ ከተማን 4-0 በማሸነፍ ከመጀመርያ ሳምንት ሽንፈት ሲያገግም መድን ሜዳ ላይ የተጫወተው አዲስ አበባ ከተማ አዲስ አዳጊው የካ ክፍለ ከተማን 2-0 ሲረታ ለገጣፎ ለገዳዲ ነቀምት ከተማን 2-1 ፣ ቡራዩ ከተማ ደሴ ከተማን በሚካኤል ደምሴ እና ሚልዮን ኢስማኤል ግቦች በተመሳሳይ 2-1 አሸንፏል፡፡ ወደ ኦሜድላ ሜዳ ያቀናው ኢትዮጵያ መድንም በሀብታሙ መንገሻ ብቸኛ ጎል ፌዴራል ፖሊስን 1-0 ማሸነፍ ችሏል።  ቅዳሜ በተደረገው ብቸኛ ጨዋታ ሽረ እንዳስላሴ  ኢኮስኮን 1-0 አሸንፏል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *