​ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ | አባ ቡና እና ወልቂጤ ነጥብ ሲጋሩ ሀዲያ ሆሳዕና ተሸንፏል

የኢትዮጵያ ከፍተኛ ሊግ ምድብ ለ ጨዋታዎች እሁድ በተደረጉ 7 ጨዋታዎች ሲቀጥሉ ናሽናል ሴሜንት ፣ ካፋ ቡና ፣ ስልጤ ወራቤ እና ዲላ ከተማ 3 ነጥብ ሰብስበዋል።

ጅማ ስታዲየም ላይ በሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታ ጅማ አባቡና ወልቂጤ ከተማን አስተናግዶ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተለያይቷል። በደመቀ ድጋፍ እና ፈጣን እንቅስቃሴ በተጀመረው ጨዋታ አባቡናዎች በ5ኛው እና 7ኛው ደቂቃ በብዙአየሁ እንዳሻው ጥሩ የግብ ማግባት አጋጣሚ ቢያገኙም ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።

በተመሳሳይ ለግብ የቀረቡ ሙከራዎች ማድረግ የቻሉት ወልቂጤዎች በ34ኛው ደቂቃ በተከላካዮች ስህተት የተገኘውን ኳስ በመጠቀም በአትክልት ንጉሴ አማካኝነት ቀደሚ በመሆን እረፍት ወጥተዋል።

ከእረፍት መልስ አባቡናዎች ሙሉ ለሙሉ የእንቅስቃሴ የበላይነት በማሳየት ተጭነው ቢጫወቱም እስከ ጨዋታው መገባደጃ ደቂቃዎች ግብ ማስቆጠር አልቻሉም። በመጨረሻም በ85ኛው ደቂቃ በወልቂጤ የግብ ክልል አክሊሉ ተፈራ በእጅ ኳስ መንካቱን ተከትሎ የተሰጠውን ፍፁም ቅጣት ምት ሱራፌል አወል ወደ ግብ ቀይሮ ጨዋታው 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተጠናቋል፡፡  [ በቴዎድሮስ ታደሰ ]

ዱራሜ ላይ ከአንደኛ ሊግ ምድብ ሠ ተያይዘው ወደ ከፍተኛ ሊግ ያለፉት ሀምበሪቾ እና ቡታጅራ ያደረጉት ጨዋታ 1-1 በሆነ አቻ ውጤት ተፈፅሟል። የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ አንተነህ ፍቃዴ በተገኙበት በተደረገው ጨዋታ የመጀመሪያው አጋማሽ በሁለቱም ቡድኖች በኩል ተመጣጣኝ እንቅስቃሴ ቢታይም ቀዳሚ መሆን የቻሉት ባለሜዳዎቹ በመስቀሌ ለቴቦ የ25 ደቂቃ ጎል ነበር። ከ10 ደቂቃዎች በኋላ ደግሞ ቡታጅራዎች አፀፋቸውን በመመለስ በወንድወሰን ዮሐንስ የ37 ደቂቃ ጎል አቻ ሆነዋል።

በሁለተኛው አጋማሽ ላይ ሀምበሪቾ የተሻለ እንቅስቃሴ ቢያሳዩም ቡታጀራዎች በማፈግፈግ የአቻነት ውጤታቸውን አስጠብቀው ለመውጣት ያደረጉት ጥረት ሰምሮ ጨዋታው 1-1 ተጠናቋል። [ በበይድ አፍሪካ ]

በሌሎች የምድብ ለ ጨዋታዎች መቂ ላይ መቂ ከተማ ዲላ ከተማን አስተናግዶ 2-0 በሆነ ውጤት ተሸንፏል፡፡ ሁለት የድሬዳዋ ቡድኖችን ያገናኘው የ የናሽናል ሴሜንት እና የድሬዳዋ ፖሊስ ጨዋታ መሀሙድ መሀመድ ባስቆጠረው ብቸኛ ግብ በናሽናል ሴሜንት 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል። ቦንጋ ላይ ካፋ ቡና በኦኒ ኡጅሉ እና በአቡበከር ግቦች ታግዞ ሀዲያ ሆሳዕናን 2-1 ማሸነፍ ሲችል በተመሳሳይ ስልጤ ወራቤ ቤንጂ ማጂ ቡናን 2-1 አሸንፏል። ነገሌ ቦረና ከሻሸመኔ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ ደግሞ ያለ ግብ የተጠናቀቀ ነው።

ቅዳሜ በተደረገ ብቸኛ ጨዋታ ሀዋሳ ላይ ደቡብ ፖሊስ ከ ሀላባ ከተማ 1-1 በሀነ አቻ ውጤት ተለያይተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *