​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ኢትዮዽያ ቡና ከ አርባምንጭ ከተማ 

ቅዳሜ እና እሁድ በተደረጉ ስድስት ጨዋታዎች የተጋመሰው የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ሰኞ ቀጥሎ በአዲስ አበባ ስታድየም ኢትዮጵያ ቡናን ከአርባምንጭ ከተማ ያገናኛል። ይህን ጨዋታ አስመልክተን ጥቂት ነጥቦች ልናነሳ ወደድን።

መከላከያን በማሸነፍ የአመቱን ጉዞውን የጀመረው ኢትዮጵያ ቡና ከሲዳማ ቡና ጋር አቻ ከተለያየበት ጨዋታ በመቀጠል አርባምንጭን የሚያስተናግድ ይሆናል። በአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ስር የሚሰለጥነው አርባምንጭ ሳምንት በኢትዮ ኤሌክትሪክ በሜዳው ሽንፈትን ቢቀምስም ከመጀመሪያዎቹ ሁለት ጨዋታዎች በተለመደው አኳኋን ሁለት ነጥቦችን አሳክቷል። በነገው ጨዋታም ሁለቱም ቡድኖች  ወደ ድል ለመመለስ ብርቱ ፉክክር እንደሚያደርጉ ይጠበቃል።

አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ኢትዮጵያ ቡናን ከተረከቡ በኋላ ቡድኑ በሜዳ ላይ ለውጦች እየተስተዋሉበት ይገኛል። ለወትሮው 4-3-3 አሰላለፍን ያዘወትር የነበረው ቡድን ሁለት የፊት አጥቂዎችን በመጠቀም እና የዳይመንድ ቅርፅ ያለው የአማካይ ክፍልን በማዋቀር ወደ 4-4-2 ዳይመንድ አሰላለፍ መጥቷል። በርግጥ ቡድኑ መከላከያን ባሸነፈበት የመጀመሪያ ጨዋታው ላይ ሲታይ አቀራረቡ በዚህ መንገድ የተቃኘ ባይመስልም በሲዳማው ጨዋታ ላይ ግን ለውጡ በግልፅ የሚታይ ነበር። ይህ አጨዋወት በተለይ በዳይመንዱ ጫፍ ላይ እንዲጫወት ኃላፊነት ለተሰጠው ኤልያስ ማሞ የተመቸ ይመስላል። ተጫዋቹ ካለው የመጨረሻ ኳሶችን ለአጥቂዎች የማድረስ ልምድ አንፃር አብዛኛውን ሰዐቱን ከሁለቱ አጥቂዎች ጀርባ እንዲያሳልፍ መሆኑ በበርካታ ክለቦች የተከላካይ እና የአማካይ ክፍል መሀል ክፍት ሆኖ ከሚታየው ቦታ በመነሳት ልዩነት እንዲፈጥር ዕድል ይሰጠዋል። አሰልጣኝ ፓፒች ከሲዳማው ጨዋታ በኃላ በሰጡት አስተያየት ቡድኑ እየተሻሻለ ቢሆንም ብዙ የሚስተካከሉ ነገሮች እንደሚኖሩም መጠቆማቸው አልቀረም። ቡድኑ ነገ ከአርባ ምንጭ ከተማ ጋር የሚያደርገው ጨዋታም የአማካይ ክፍሉ የሚፈተንበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት በመጨረስ የተካነው አርባምንጭ ከተማ በርካታ የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎችን በመጠቀም ይታወቃል። ከፊት ላኪ ሳኒን በብቸኛ አጥቂነት በማሰለፍ ከተከላካይ አማካዩ ታዲዮስ ወልዴ ፊት ተጨማሪ አራት አማካዮችን የሚያጫውቱት አሰልጣኝ ፀጋዬ የ4-1-4-1 አሰላለፍን እንደሚያዘወትሩ ይታወቃል። በነገው ጨዋታም ሁለቱ ቡድኖች መሀል ሜዳ ላይ የሚያደርጉት ፍልሚያ የጨዋታውን ውጤት ለመወሰን ትልቅ ዕድል ይኖረዋል። የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን መውሰድ የቻለ እና በእንቅስቃሴ ተቃራኒ ቡድን ክፍተቶችን እንዲፈጥር በማድረግ የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር በመሞከሩ ረገድ የተሻለ መንቀሳቀስ የሚችል የአማካይ ክፍል የሚኖረው ቡድን ጨዋታውን በበላይነት ለመጨረስ እንደሚችል ይገመታል። ነገር ግን ከዚህ በተለየ ደግሞ የሁለቱ ቡድኖች የመሀል ክፍል ተሰላፊዎች መበራከት በሊጉ በሰፊው የሚታየውን የተጫዋቾች በተመሳሳይ የሜዳ ክፍል ላይ ተደራርቦ መታየት እና የሜዳውን ቁመት እና ስፋት ከግምት ያላስገባ የቦታ አጠቃቀም እንዳያስመለክተንም የሚያሰጋ ነው።

የኢትዮጵያ ቡናው የመስመር አጥቂ አስቻለው ግርማ እና የአርባምንጩ የመሀል አማካይ አማኑኤል ጎበና በጉዳት ምክንያት ከጨዋታ ውጪ ሲሆኑ በሲዳማ ቡናው ጨዋታ በመጠነኛ ጉዳት ከሜዳ ተቀይሮ የወጣው መስዑድ መሀመድ ወደ ጨዋታ እንደሚመለስ ይጠበቃል።

ኢ/ዳ በላይ ታደሰ ጨዋታውን በመሀል ዳኝነት እንዲመሩት የተመረጡ ሲሆን ፌ/ዳ ዳንኤል ጥበቡ እና ፌ/ዳ ማርቆስ ፉፋ በረዳት ደኝነት ተመድበዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *