​ሪፖርት | ኢትዮጵያ ቡና አርባምንጭን በማሸነፍ ሊጉን መምራት ጀመረ

የአመቱ ሶስተኛ ጨዋታውን በአዲስ አበባ ስታድየም ያደረገው ኢትዮጽያ ቡና በአራተኛው ሳምንት የሊጉ መርሀ ግብር አርባምንጭ ከተማን አስተናግዶ 2-0 አሸንፏል።

ጨዋታው ከመጀመሩ በፊት በተለምዶው ዳፍ ትራክ ተብሎ በሚጠራው የስታድየሙ ክፍል የነበሩ ደጋፊዎች ወደ ካታንጋ ለመግባት ባደረጉት ጥረት ከፀጥታ ሀይሎች ጋር ግጭት ውስጥ ገብተው ታይተዋል።

እንግዶቹ አርባምንጮች በኢትዮ ኤሌክትሪክ ከተሸነፉበት ጨዋታ የአራት ተጨዋቾች ቅያሪ አርገው ሲገቡ ሶስቱ ቅያሪዎቻቸው በተከላካይ መስመር ላይ የተደረጉ ነበሩ። በዚህም ተመስገን ካስትሮ እና አሌክስ አሙዙ ለመጀመሪያ ጊዜ በመሀል ተከላካይ ቦታ ላይ ተጣምረዋል። ኢትዮጵያ ቡናም ከሲዳማው ጨዋታ በተመሳሳይ አራት ተጨዋቾችን ሲቀይር አክሊሉ አያናው እና አማኑኤል ዮሀንስ የአመቱን የመጀመሪያ ጨዋታቸውን አድርገዋል።

የመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ ማለት በሚያስችል ሁኔታ በኢትዮጵያ ቡና ብልጫ የተገባደደ ነበር። የአሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ቡድን ይታይበት የነበረውን የሜዳውን ስፋት የመጠቀም ችግር ዛሬ በመስመር ተከላካዮቹ የማጥቃት እንቅስቃሴ አሻሽሎት ገብቷል። ይህ በመሆኑም ቡድኑ በኤልያስ ማሞ፣ አክሊሉ ዋለልኝ እና አማኑኤል ዮሀንስ አማካይነት ካረጋቸው የረጅም ርቀት ሙከራዎች ውጪ ተጋጣሚው ሳጥን ድረስ ዘልቆ የፈጠራቸው ዕድሎች በርካታ ነበሩ። በተለይም ሳሙኤል ሳኑሚ 18ኛው ደቂቃ ላይ ከአማኑኤል ዮሀንስ የተላከለትን እንዲሁም 40ኛው ደቂቃ ላይ ከቀኝ መስመር የተሰነጠቀለትን ኳሶች ከአርባምንጭ የፍፁም ቅጣት ምት ክልል ውስጥ የሞከረ ሲሆን የመጀመሪያውን ሲሳይ ባንጫ ሲያድንበት ሁለተኛው በግቡ አግዳሚ ተመልሶበታል። 44ኛው ደቂቃ ላይም የቡድኑ ተጨዋቼች በፈጣን ማጥቃት የአርባምንጭ ሳጥን ውስጥ ቢገቡም አጋጣሚውን ወደ ሙከራ ሳይቀይሩት ቀርተዋል። ኢትዮጵያ ቡና የመጀመሪያውን አጋማሽ እየመራ ወደመልበሻ ክፍል እንዲይመራ ያስቻለው በረከት ይስሀቅ ነበር። 31ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ከመሀል ሜዳ ለሳኑሚ ያሳለፈለትን ኳስ ሲሳይ ባንጫ ከግብ ክልሉ ወጥቶ በእጁ ቢመልሰውም በአቅራቢያው ይገኝ የነበረው በረከት ይስሀቅ በቀጥታ በመምታት አስቆጥሯል። ሳሙኤል ሳኑሚ ከኤልያስ ኳሷን  ሲቀበል ከጨዋታ ውጪ ነበር በሚል የአርባምንጭ ተጨዋቾች ተቀውሟቸውን በመስመር ዳኛው ላይ ቢያሰሙም ጓሏ ግን መፅደቋ አልቀረም።

በተጋጣሚው የኳስ ቁጥጥር ብልጫ የተወሰደበት የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም ቡድን ወደኃላ እየተገፋ መምጣቱ ቡድኑ ወደፊት ሊሄድ ሚችልባቸውን አጋጣሚዎች ሲያገኝ እስከተጋጣሚው ግብ ድረስ ያለውን ሰፊ ርቀት አቋርጦ ሙከራዎችን ለማድረግ እንዲቸገር አድርጎታል። ቡናዎች ኳስ ይዘው በአርባምንጭ የሜዳ ክልል ውስጥ በሚገኙበት እና የመሀል ተከላካዮቻቸውን እስከ ሜዳው አጋማሽ በሚያመጡበት ወቅት እንኳን አርባምንጭምች ኳስን በፍጥነት አስጥለው ከሀሪሰን ፊት ባለው ሰፊ  ክፍት ቦታ ለመግባት የሚያረጉት ጥረት ደካማ ነበር። አጠቃላይ የቡድኑ ተሰላፊዎች ከኳስ ውጪ በነበራቸው እንቅስቃሴ የተጋጣሚ ተጨዋቾችን ኳስ ለመንጠቅ ያሳዩ የነበረው ተነሳችነት ዝቅተኛ መሆን ከተወሰደባቸው ብልጫ በቀላሉ እንዳያገግሙ አድርጓቸዋል። በሙከራ ረገድ ቡድኑ የመጀመሪያው አጋማሽ ሊጠናቀቅ ሲል በተሻለ የማጥቃት ሂደት ሁለት ጊዜ በቡና የፍፁም ቅጣት ምት ክልል አካባቢ መድረስ ሲችል በወንድሜነህ ዘሪሁን የተሞከረው አንደኛው ኳስ ኢላማውን ሳይጠብቅ ሲቀር ሌላኛው የገ/ሚካኤል ያዕቆብ ሙከራ ደግሞ በሀሪሰን በቀላሉ ተይዟል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው አንፃር የተቀዛቀዘ ነበር። በመጀመሪያው አጋማሽ መጨረሻ ላይ የቡድኑን ብቸኛ ሙከራዎች ያደረጉትን ወንድሜነህ ዘሪሁን እና ገ/ሚካኤል ያዕቆብን በብርሀኑ አዳሙ እና አለልኝ አዘነ ቀይረው ያስገቡት አርባምንጮች ከመጀመሪያው በተሻለ ወደ ኢትዮጵያ ቡና የሜዳ ክልል ለመግባት ድፍረት ታይቶባቸዋል። እንዲሁም በአንድ ለአንድ ግንኙነቶች ወቅት ተጨዋቾቹ ላይ ይታይ የነበረው ቸልተኝነትም በሁለተኛው አጋማሽ ተሻሽሎ ታይቷል። ሆኖም ንፁህ የግብ ዕድል በመፍጠሩ በኩል የተለየ ነገር አልታየም ። አርባምንጮች በጨዋታው ማብቂያ ላይ ተካልኝ ደጀኔ ከቀኝ መስመር ያሻማውን ኳስ ሀሪሰን በአግባቡ ሳይዝ ቀርቶ ሲለቀው አግኝቶ አለልኝ አዘነ ከሞከረበት እና በኢትዮጵያ ቡና ተከላካዮች ተጨርፎ ከወጣው ውጪ የነበሩት የማጥቃት ሙከራዎቻቸው እምብዛም ለሙከራነት የቀረቡ አልነበሩም።

ኢትዮጵያ ቡናዎች እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሙሉ ለሙሉ የጨዋታ ብልጫውን ባይወስዱም የአርባምንጮችን የተሻለ የማጥቃት ፍላጎት ተከትሎ በሜዳቸው የሚነጥቁትን ኳስ በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ ሜዳ ይዘው በመግባት ዕድሎችን ለመፍጠር ሞክረዋል ። በተመሳሳይ እንቅስቃሴ ሳሙኤል ሳኑሚ 71ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር ይዞ ገብቶ ለማናዬ ፋንቱ ያሳለፈውን ኳስ የአርባምንጩ የመሀል ተከላካይ አሌክስ አሙዙ ለማውጣት ብሎ በራሱ ግብ ላይ አስቆጥሯል ። ከግቡ ዉጪ 55ኛው ደቂቃ ላይ የኢትዮጵያ ቡናዎቹ ሳሙኤል ሳኑሚ ኤልያስ ማሞ እና ማናዬ ፋንቱ በፈጣን ማጥቃት ከአራቱ የአርባምንጭ ተከላካዮች ጋር ተገናኝተው የፈጠሩትን ዕድል ሳኑሚ አመከነው እንጂ ቡድኑ አሙዙ በራሱ መረብ ላይ ካስቆጠረው ጎል በፊት መሪ መሆን ሚችልበት ዕድል ነበር። ያም ቢህምን ተጨማሪ ጎሎችን ማስቆጠር ባይችሉም ቡናማዎቹ ለተጋጣሚያቸው የማንሰራሪያ ዕድል ሳይሰጡ በአሸናፊነት ጨዋታውን በመጨረስ በሰባት ነጥቦች ሊጉን መምራት ጀምረዋል።

የአሰልጣኞች አስተያየት 

ኮስታዲን ፓፒች (ኢትዮጵያ ቡና)

” ቡድኔ ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻለ ነው። ዛሬ በመጀመሪያው አጋማሽ የተጫወትንበት መንገድ አመቱን ሙሉ እንድንጫወትበት የምፈልገው አይነት ነበር። አሁንም በየጨዋታው እየተሻሻልን መሄዳችንን እንቀጥላለን። ሁሉም የቡድኑ ክፍል ላይ መሻሻል ያለባቸው ነገሮች አሉ። በተለይም በአጥቂ መስመራችን ላይ። ችግሮቹንም በልምምድ ፕሮግራሞቻችን ወቅት ሰርተንባቸው ተሻሽለን እንመጣለን። እውነት ለመናገር የዛሬው የመጀመሪያ አጋማሽ ጨዋታችን ግን በጣም ጥሩ ነበር።”

ፀጋዬ ኪዳነማርያም – አርባምንጭ ከተማ

” በሜዳችን ያደረግነውን ጨዋታ በመሸነፋችን ይህንን ጨዋታ አሸንፈን ቡድናችንን ለማረጋጋት አስበን ነበር። ሆኖም ግን በተከላካያችን እና ግብ ጠባቂያችን መዘናጋት ምክንያት በገባብን ጎል ያሰብነውን ታክቲክ መተግበር አልቻልንም። እንደ ቡድን ግን የዛሬው ቡድኔ ከሌላው ጊዜ የተሻለ ነበር።

የኤልያስ ማሞ ዛሬ የደረገው እንቅስቃሴ ጥሩ ነበር። ለኢትዮጵያ ቡና ውጤት ቀያሪም ነበር። በኛ በኩል የአማኑኤል እና ላኪ ሳኒ አለመኖር ጎድቶናል። በተረፈ ጥሩ ከነበረው ዳኝነት ጋር ኢትዮጵያ ቡና በደጋፊዎቹ እየታገዘ አሸንፎ ወጥቷል። “

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *