​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ሲዳማ ቡና ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ አራተኛ ሳምንት ዛሬ ይርጋለም ላይ ሲዳማ ቡና ቅዱስ ጊዮርጊስን በሚያስተናግድበት ጨዋታ ይገባደዳል። በጨዋታው ዙርያ የሚነሱ አብይ ነጥቦችንም እንደሚከተው ተመልክተናቸዋል።

በ2009 የውድድር አመት ስድስተኛ ሳምንት ላይ ተገናኝተው ያለግብ የተለያዩት ሁለቱ ቡድኖች እስካሁን ዘንድሮ ያደረጓቸው ጨዋታዎች በሙሉ በአቻ ውጤቶች የተጠናቀቁ ነበሩ። በብሔራዊ ቡድን የተጨዋቾች ምርጫ ምክንያት ሁለት ጨዋታዎች በቀሪ የተያዙለት ቅዱስ ጊዮርጊስ ከመቐለ ከተማ  ጋር ያደረገውን ብቸኛ ጨዋታ በ 1-1 ውጤት ደምድሟል። ሲዳማ ቡናም ሜዳው ላይ ከአርባምንጭ ከተማ እንዲሁም ከሜዳው ውጪ ከወልዋሎ ዓ.ዩ እና ኢትዮጵያ ቡና ጋር ባደረጋቸው ጨዋታዎች በሙሉ ነጥብ እየተጋራ ወጥቷል።

በዛሬው ጨዋታ ቡድኖቹ ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጧቸው ተጨዋቾችን አገልግሎት የማያገኙ ይሆናል። በዚህም የሲዳማ ቡናዎቹ አበበ ጥላሁን እና አዲስ ግደይ እንዲሁም የቅዱስ ጊዮርጊሶቹ አበባው ቡታቆ እና አቡበከር ሳኒ ጨዋታው ላይ የማይኖሩ ይሆናል። ይህ ሁኔታም በተለይ ለሲዳማ ቡና ጨዋታውን እንደሚያከብድበት ግልፅ ነው። አምና ከነበረው የተከላካይ ክፍሉ በብቸኝነት የቀረው አበበ ጥላሁን አለመኖሩ የቡድኑን የኋላ መስመር መሰረት የሚያናጋው ነው የሚሆነው ። በአብዛኛው የሲዳማ ማጥቃት እንቅስቃሴ መሳሪያ የሆነው እና በቡድኑ የስካሁን ጉዞ የተገኙ ሁለት ጎሎች ባለቤት የነበረው አዲስ ግደይ አለመኖርም ተፅዕኖው ቀላል የሚባል አይደለም። ከዚህ በተጨማሪ የአማካይ መስመር ተሰላፊው ትርታዬ ደመቀ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ በተመለከተው ቀይ ካርድ ምክንያት በቅጣት እንዲሁም አዲስ ፈራሚው ፈቱዲን ጀማል ደግሞ በጉዳት ሳቢያ ጨዋታው ያልፋቸዋል። በቅዱስ ጊዮርጊስ ቤት ረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የሚገኙት ሳላዲን ሰይድ እና ታደለ መንገሻ አሁንም ከጉዳታቸው ያላገገሙ ሲሆን አዳነ ግርማም የስድስት ወር ቅጣቱን ባለማገባደዱ ወደ ይርጋለም አልተጓዘም። ሆኖም የአስቻለው ታመነ እና በሀይሉ አሰፋ ከጉዳት መመለስ ለሻምፒዮኖቹ መልካም ዜና ሆኗል።

አምና ተከታታይ ሶስት ጨዋታዎችን በማሸነፍ እና ስምንት ግቦችን ከመረብ በማዋሃድ ምንም ግብ ሳያስተናግዱ ሊጉን ጀምረው የነበሩት ጊዮርጊሶች ዘንድሮም ጅማሯቸውን መልካም ለማድረግ ይህን ጨዋታ ማሸነፍ ይጠበቅባቸዋል። አሰልጣኝ ቫዝ ፒንቶ ወደ ቡድኑ ይዘውት የመጡት አዲስ አጨዋወት እስካሁን በአዲስ አባባ ስቴድየም ላይ ከገጠመው ፈተና አንፃር በመጀመሪያው የክልል ጨዋታው ምን አይነት ውጤት ሊገጥመው እንደሚችልም ይጠበቃል። ቡድኑ በአዲስ አበባ ዋንጫ እና በመቐለው የመጀመሪያ ጨዋታ ላይ ያስቆጠራቸው ግቦች መነሻ የነበሩት ረጃጅም ኳሶች ከአሁኑ አጨዋወቱ ጋር አብረው ባይሄዱም ውጤት ለማግኘት የነበራቸው አስተዋፅኦ ግን የማይካድ ነው። በዛሬው የሲዳማ ቡና ጨዋታ ላይም ቅዱስ ጊዮርጊስ የኳስ ቁጥጥር የበላይነቱን ለመውሰድ ቢችልም የግብ ዕድሎችን ለመፍጠር ግን ቀጥተኛ ኳሶችን የመጠቀም አዝማሚያ እንደሚኖረው ይታሰባል።

እንደ አምናው ባይሆንም ዘንድሮም ጠንካራ የመከላከል አደረጃጀት ያለው ሲዳማ ቡና በኳስ ቁጥጥር ላይ ለተመሰረተ ቡድን በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ ለመሆኑ የኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ጥሩ ማሳያ ሆኖ አልፏል። ከአማካይ ክፍሉ ሰፊ ሽፋን የሚያገኘው የተከላካይ መስመር በማጥቃት ላይ እምብዛም ተሳትፎ አለማድረጉ ከቅዱስ ጊዮርጊስ የመስመር አጥቂዎች የተለጠጠ አቋቋም ጋር ተደምሮ በሲዳማ በኩል እምብዛም ከራሳቸው ሜዳ የማይወጡ የመስመር ተከላካዮችን በዛሬው ጨዋታ ላይ እንድንጠብቅ ያደረጋል። በማጥቃቱ በኩል ሲዳማ ቡናም እንደተጋጣሚው ሁሉ በዋነኝነት በመስመር አጥቂዎቹ እንቅስቃሴ ላይ የተመሰረተ መሆኑ  ከቡድኖቹ የአማካይ እና የተከላካይ ተሰላፊዎች ለመስመር አጥቂዎች የሚላኩ ኳሶች በጨዋታው ላይ ለሚታዩ ወሳኝ ፍልሚያዎች ምክንያት የመሆናቸው ዕድል ሰፊ ነው። በጥቅሉ በሁለቱ ክንፎች በኩል ፍጥነት ባለው አኳኃን ወደ ማጥቃት በሚደረጉ ሽግግሮች የተጋጣሚውን የተከላካይ መስመር ክፍተት ለማግኘት የሚችል እና በቁሙ ኳሶች አጠቃቀሙ የተሻለ የሚሆነው ቡድን ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ዕድል ይኖረዋል።

ኢ/ዳ አማኑኤል ኃይለስላሴ ይርጋለም ላይ የመጨረሻውን የአራተኛ ሳምንት ጨዋታ በዋና ዳኝነት እንዲመራ የተመደበ ሲሆን ኢ/ዳ ሀይለራጉኤል ወልዳይ እና ፌ/ዳ ታምራት ቅጣው በረዳት ዳኝነት ወደ ስፍራው አምርተዋል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *