​ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ | ወልዋሎ ዓ.ዩ ከ ኢትዮጵያ ቡና

የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 5ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ነገና ከነገ በስትያ ቀጥለው ይደረጋሉ። ነገ ከሚደረጉ ጨዋታዎች መከከልም ዓዲግራት ላይ ወልዋሎ ዓ.ዩ ኢትዮጵያ ቡናን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ትኩረትን የሳበ ሆኗል። ሶከር ኢትዮጵያም ይህን ጨዋታ በጥልቀት ለመመልከት ወዳለች። 


ቦታ | ወልዋሎ ስታድየም

ቀን | እሁድ ህዳር 24 2010

ሰዐት | 09፡00

ዳኞች | ዋና ዳኛ  – ሰለሞን ገ/ሚካኤል (ፌዴራል ዳኛ)

             ረዳት ዳኞች  – ዳንኤል ጥበቡ (ፌዴራል ዳኛ) እና አበራ አብዱሬ (ፌዴራል ዳኛ)


የቅርብ ጊዜ ውጤቶች (ከቅርብ ወደ ሩቅ)

ወልዋሎ ዓ.ዩ | አሸአቻአቻአቻ

ኢትዮጵያ ቡና | አሸ–   አቻ–   አሸ


ሁለቱ ቡድኖች በሊጉ ሰንጠረዥ አናት ላይ መገኘታቸው ጨዋታው ትኩረት እንዲስብ ዋነኛ ምክንያት ቢሆንም እስካሁን በሊጉ ሽንፈት አለማስተናገዳቸው እና በአራተኛ ሳምንት ጨዋታዎች አሸናፊ የነበሩ መሆኑ ይበልጥ ግምት የሚሰጠው ፍልሚያን እንድንጠብቅ ያደርገናል።  ወልዋሎ ዓ.ዩ በሶስት ተከታታይ ጨዋታዎች አቻ በመውጣት ሊጉን ሲጀመር በሁለቱ ግብ ማስቆጠር አልቻለም ነበር። ሆኖም ቡድኑ ባሳለፍነው ሳምንት ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3-1 ማሸነፉ ለዚህ ጨዋታ የዐዕምሮ ዝግጅት ትልቅ እገዛ እንዳለው መናገር ይቻላል። አሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚአብሄርም ስለቀጣይ ጨዋታ ሲጠየቁ መልሳቸው “ቡናን እንሸንፋለን” የሚል ነበር። እስካሁን ሶስት ጨዋታዎችን ያደረገው ኢትዮጵያ ቡና መከላከያ እና አርባምንጭ ከተማን ማሸነፍ ሲችል ከሲዳማ ቡና አቻ ተለያይቷል። በዚህም ኢትዮጵያ ቡና በሰባት ነጥቦች ሊጉን መምራት ችሏል። ሆኖም ሶስቱም ጨዋታዎች አዲስ አበባ ስታድየም ላይ በመደረጋቸው የነገው የወልዋሎ ጨዋታ ለክለቡ የአመቱ የመጀመሪያ የሜዳ ውጪ ጨዋታ ይሆናል።


በጨዋታው ምን ይጠበቃል ?

ኢትዮጵያ ቡና በአዲሱ አሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች ስር ከጨዋታ ወደ ጨዋታ እየተሻሻለ መጥቷል። በተለይም ቡድኑ አርባምንጭን ባሸነፈበት ጨዋታ የመጀመሪያ አጋማሽ ያደረገው እንቅስቃሴ ከእስካሁኑ ሁሉ የላቀ ነበር። የዳይመንድ ቅርፅ ያለው የቡድኑ አማካይ ክፍል የነበረበት የሜዳውን ስፋት የመጠቀም ችግር በዚህ ጨዋታ በመስመር ተከላካዮቹ የተመጣጠነ የማጥቃት ተሳትፎ ተቀርፎ ታይቷል። የኤልያስ ማሞ ከተጋጣሚ ተከላካይ ክፍል ፊት ለፊት በሚፈጠረው ክፍተት ላይ በብዙ የጨዋታ እንቅስቃሴዎች ወቅት መገኘት መቻል ቡድኑ በተጋጣሚ ሳጥን ውስጥ ዕድሎችን ለመፍጠር እንዲጠቀምበት ረድቶትም ታይቷል ። የተለጠጡ የመስመር አጥቂዎችን እና የጠበበ የአጥቂ አማካይ ተሰላፊዎች ጥምረትን የሚጠቀመው ወልዋሎ ዓ.ዩም እንደተጋጣሚ ሁሉ መሻሻሎች ታይተውበታል። ተጨዋቾችን እያፈራረቀ የሚጠቀመው የአሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሄር ቡድን በተለይ ከመስመር የሚነሳው  የማጥቃት ሀይሉ ወደ መሀለኛው የተጋጣሚ የመከላከል ዞን ድረስ በመዝለቅ አደጋ መፍጠር የሚችል ሆኗል። ቡድኑ በማጥቃት ወቅት የሚኖረው ፈጠን ያለ ሽግግርም እንደ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ላሉ የመስመር አጥቂዎቹ ውጤታማነት አጋዥ መሆን ችሏል። ሆኖም ሁለቱም ቡድኖች በፊት አጥቂዎቻቸው ላይ ብዙ መስራት ይጠበቅባቸዋል። ሳሙኤል ሳኑሚን ከማናዬ ፋንቱ እና በረከት ይስሀቅ ጋር እየፈራረቀ የሚያጣምረው ኢትዮጵያ ቡናም ሆነ  ሙሉአለም ጥላሁንን በሁሉም ጨዋታዎች ላይ በአጥቂነት ያስጀመረው ወልዋሎ የፊት መስመራቸው ጥንካሬ ጥያቄ የሚነሳበት ነው።

በነገው ጨዋታ ላይ ወልዋሎዎች ጥቃት ለመሰንዘር ሚጠቀሙባቸው እና አብዛኛውን ሰዐታቸውን በተጋጣሚ ሜዳ ላይ የሚያሳልፉት የመስመር አጥቂዎች ማጥቃቱን ለማገዝ ወደፊት ከሚሄዱት የኢትዮጵያ ቡና የመስመር ተከላካዮች ጋር የሚኖራቸው ፍልሚያ የሚጠበቅ ነው። በተለይም የቀኝ መስመር አጥቂው ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከኢትዮጵያ ቡናው ግራ መስመር ተከላካይ አስራት ሞገስ ጋር ሚገናኝበት መስመር ወሳኝ ይሆናል። እጅጉን አጥበው በመጫወት በብዛት በተመሳሳይ የሜዳው ክፍል ላይ ሲንቀሳቀሱ የሚታዩት የወልዋሎዎች የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች በጥሩ ውህደት ላይ ካለው እና በተጨዋቾች ቅያሪም ተፈትኖ የታየው የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ዳይመንድ መሀል ብርቱ ፉክክር ይጠብቃቸዋል።


የቡድን ዜና

በሴካፋ ውድድር ላይ በሚሳተፈው የኢትዮጵያ ቤሔራዊ ቡድን ውስጥ የተካተቱት የወልዋሎው ዋና ግብ ጠባቂ በረከት አማረ እና የኢትዮጵያ ቡናው ሳምሶን ጥላሁን ጨዋታው ያመልጣቸዋል። በወልዋሎ በኩል አማካዩ ብሩክ አየለ ከጉዳት ሲመለስ ጨዋታው በጉዳት ሳቢያ ሚያመልጠው ሌላ ተጨዋች እንደሌለ ሰምተናል። በአንፃሩ የኢትዮጵያ ቡና የአማካይ ክፍል ተሰላፊዎች ክሪዚስቶም ንታንቢ እና መስዑድ መሀመድ ከጉዳት ባለማገገማቸው ለጨዋታው አይደርሱም። ከሁሉም በላይ የአሰልጣኝ ኮስታዲን ፓፒች በቤተሰብ ጉዳይ ወደ ሀገራችቸው ማምራት በሳምንቱ መጨረሻ ትልቅ ዜና የሆነ ሲሆን ኢትዮጵያ ቡናም በምክትል አሰልጣኙ ሀብተወልድ ደስታ እየተመራ ወደሜዳ ይገባል።


ግምታዊ አሰላለፍ

ወልዋሎ ዓ.ዩ (4-3-3)

ዘውዱ መስፍን

እንየው ካሳሁን –  በረከት ተሰማ –  ተስፋዬ ዲባባ – ሮቤል ግርማ

አፈወርቅ ኃይሉ – አሳሪ አልመሀዲ –  ዋለልኝ ገብሬ

ፕሪንስ ሰቨሪንሆ – ሙሉአለም ጥላሁን – ከድር ሳሊህ


ኢትዮጵያ ቡና (4-4-2 ♦)

ሀሪሰን ሄሱ

አስራት ቱንጆ  – ቶማስ ስምረቱ – አክሊሉ አየነው – አስናቀ ሞገስ

                         አክሊሉ ዋለልኝ

እያሱ ታምሩ                                 አማኑኤል ዮሃንስ

                         ኤልያስ ማሞ

           ሳሙኤል ሳኑሚ – በረከት ይስሀቅ


 

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *