ዳሽን ቢራ 7 አዳዲስ ተጫዋቾች አስፈርሟል

አዲስ አሰልጣኝ የሾመው ዳሽን ቢራ 7 አዳዲስ ተጫዋቾችን አስፈርሟል፡፡ ውላቸው የተጠናቀቁ ተጫዋቾችንም ሸኝቷል፡፡

የጎንደሩ ክለብ ካስፈረማቸው ተጫዋቾች መካከል ደረጄ መንግስቱ እና መስፍን ኪዳኔ ይጠቀሳሉ፡፡ ደረጄ በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ሁለተኛ ዙር በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የአማካይ ክፍል ድንቅ ብቃቱን ያሳየ ሲሆን መስፍን ኪዳኔ አመዛኙን የውድድር ዘመን ግልጋሎት ሳይሰጥ አጠናቋል፡፡ በ2006 ቅዱስ ጊዮርጊስን ለቆ ደደቢትን የተቀላቀለው መስፍን ኪዳኔ ደደቢትን በተቀላቀለበት አመት መልካም አቋም ቢያሳይም በተጠናቀቀው የውድድር ዘመን ግን የተጠበቀውን ያህል አቋም ማሳየት ሳይችል ቀርቷል፡፡

የኢትዮጵያ ንግድ ባንኩ ተክሉ ተስፋዬ ሌላው ክለቡን የተቀላቀለ ተጫዋች ነው፡፡ በክረምቱ ስሙ ከዳሽን ጋር ሲያያዝ የከረመ ሲሆን የዳሽንን የመስመር አጨዋወት ያሻሽለዋል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የወልድያዎቹ ብርሃኑ በላይ እና ማይክ ሰርጂ ክለቡን የተቀላቀሉ ሌሎች ተጫዋቾች ናቸው፡፡ ካሜሩናዊው አማካይ ማይክ ሰርጂ ከቶጓዊው ኤዶም ሆሶሮቪ በመቀጠል 2ኛው የቡድኑ የውጭ ተጫዋች ይሆናል፡፡

አዲሱ አላሮም ሙገርን ለቆ ዳሽንን ተቀላቅሏል፡፡ አዲሱ በግርማ ኃ/ዮሃንስ ቡድን ውስጥ ከፉልባክ እስከ አጥቂ ድረስ ግልጋሎት ሲሰጥ የቆየ ሁለገብ ተጫዋች ነው፡፡

ሀዋሳ ከነማን ከለቀቁ ተጫዋቾች አንዱ የሆነው አለማየሁ ተሰማ ለጎንደሩ ክለብ የፈረመ 7ኛው ተጫዋች ነው፡፡

ክለቡ ውላቸውን ያላደሰላቸው 5 ተጫዋቾችም ተሰናብተዋል፡፡ ዳዊት ሞገስ ፣ ፀጋዬ ገ/ሃና ፣ አልፋየሁ ሙላቱ እና ኤሌክትሪክን የተቀላቀለው ሃብታሙ መንገሻ ክለቡን የለቀቁ ተጫዋቾች ሲሆኑ አጥቂው ሚካኤል ጆርጅ ክለቡን ለቆ ወደ አዳማ ከነማ ለማምራት መቃረቡም ተነግሯል፡፡

ዳሽን ቢራ ከዚህ በፊት ውላቸው የተጠናቀቀው የተሸ ግዛው ፣ ኤርሚያስ ኃይሉ ፣ ምንያህል ይመር ፣ ደረጄ አለሙ እና ኤዶም ሆሶሮቪን ውል ለ2 አመታት አድሷል፡፡ በቀጣይነትም የአምበሉ አይናለም ኃይለን ኮንትራ ለማደስ እየተንቀሳቀሰ ሲሆን አስራት መገርሳ ደግሞ ስሙ ከአዲስ አበባ ክለቦች ጋር ተያይዟል፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *