አምና በርካታ አዳዲስ ተጫዋቾችን ያስፈረመው ሀዋሳ ከነማ ዘንድሮ ከአዳዲስ ተጫዋቾች ይልቅ ውል በማደስ ላይ ትኩረቱን አድርጓል፡፡
ክለቡ የኮንትራት ጊዜያቸውን ካጠናቀቁ 13 ተጫዋቾች መካከል የ11 ተጫዋቾቹን ውል አድሷል፡፡ ከሌሎች ክለቦች ጋር ስሙ ተያይዞ የሚገኘውና ውሉን አላደሰም የተባለው ግርማ በቀለ እና ለአዳማ ከነማም ፈርሟል ሲባል የነበረው አዲስአለም ተስፋዬ ውላቸውን ካደሱት መካከል የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
የክለቡ አሰልጣኝ ውበቱ አባተ ለሶከር ኢትዮጵያ በሰጡት አስተያየት ከአዳዲስ ተጫዋቾች ይልቅ በቡድኑ ለሚገኙ ተጫዋቾች ትኩረት እንደሰጡ ተናግረዋል፡፡ ‹‹ 13 ውላቸውን ከጨረሱ ተጫዋቾች መካከል የ11ዱን ውል ማደስ ትልቅ ነገር ነው፡፡ ብሩክ ቃልቦሬ እና ባዬ ገዛኸኝን ለማስፈረም ብንስማማም ኋላ ላይ ለሌላ ክለብ ፈርመዋል፡፡ ስለዚህ ትኩረት ማድረግ የፈለግነው እዚሁ ባሉ ተጫዋቾች ላይ ነው፡፡ ውላቸው ተጠናቆ በለቀቁት 2 ተጫዋቾች ምትክ ተጫዋች እናስፈርማለን፡፡ ኤፍሬም ዘካርያስን ከቡና ያስፈረምን ሲሆን ደደቢት በረከት ይስሃቅን ለመልቀቅ ፍቃደኛ በመሆኑ እሱንም የማስፈረም ፍላጎት አለን፡፡ ›› ብለዋል፡፡
ሙሉጌታ ምህረት ፣ አዲስአለም ተስፋዬ ፣ ክብረአብ ዳዊት ፣ አዲስአለም ተስፋዬ ፣ ግርማ በቀለ ፣ ጋዲሳ መብራቴ ፣ አመለ ኤባ ፣ ታፈሰ ሰለሞን ፣ ተመስገን ተክሌ እና ዳንኤል ደርቤ ውል ካራዘሙት መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ክለቡ የቅድመ ውድድር ዝግጅቱን በነሃሴ ወር አጋማሽ እንደሚጀመር ሲጠበቅ በርካታ አዳዲስ ፊቶች ባለመኖራቸው ቡድኑ ለከርሞ በተሻለ ውህደት ሊቀርብ ይችላል ተብሏል፡፡