ኢትዮጵያ ለ2018 የአለም ዋንጫ ለማለፍ በሚደረገው የማጣርያ ምድብ ላይ ለመካፈል በቅድሚያ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ታደርጋለች፡፡ በጁላይ ወር የሃገራት የደረጃ ሰንጠረዥ ላይ ባላቸው ደረጃ መሰረትም ኢትዮጵያ በመጀመርያው የቅድመ ማጣርያ ከሚካፈሉት 26 ሃገራት መካከል ውስጥ እንድትካተት አድርጓታል፡፡
ነገ በሩስያዋ ሴንት ፒተርስበርግ ከተማ ነገ ድልድሉ የሚወጣ ሲሆን ኢትዮጵያ በቋት አንድ ውስጥ በመደልደሏ በቅድመ ማጣርያው የተሻሉ የሚባሉ 12 ሃገራትን አታገኝም፡፡ ነገ በሚወጣው እጣ መሰረትም ከታንዛንያ ፣ ደቡብ ሱዳን ፣ ላይቤርያ ፣ ሴንትራል አፍሪካ ፣ ሲሸልስ ፣ ጋምቢያ ፣ ቻድ ፣ ሞሪሸስ ፣ ኮሞሮስ ፣ ሳኦቶሜ ፣ ኤርትራ ፣ ሶማልያ ወይም ጅቡቲ አንዳቸውን ትገጥማለች፡፡
ኦክቶበር 5 እና 13 በሚደረገው የደርሶ መልስ የቅድመ ማጣርያ ጨዋታ ኢትዮጵያ ተጋጣሚዋን አሸንፋ ካለፈች በ2ኛው ዙር ቅድመ ማጣርያ ከፍተኛ ደረጃ ካላቸው 27 ቡድኖች መካከል አንዷን ሃገር በደርሶ መልስ ትገጥማለች፡፡ ይህንን ዙር በብቃት ከተወጣችም የመጨረሻዎቹን 20 ሃገራት ተቀላቅላ የምድብ ማጣርያ ውስጥ ትገባለች፡፡
በ5 ምድብ ተከፍሎ በሚደረገው የምድብ ማጣርያ ምድባቸውን በአንደኝነት ያጠናቀቁ 5 ሃገራት ወደ 2018 የሩስያ የአለም ዋንጫ ያመራሉ፡፡
ኢትዮጵያ በሴፕቴምበር የአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ፣ በኦክቶቨር የቻን ማጣርያ እነ የአለም ዋንጫ ማጣርያ እንዲሁም በዲሴምበር በራሷ አስተናጋጅነት የሚካሄደው የሴካፋ ውድድርን ያካተተ ተደራራቢ የውድድር ካሌንደር ይኖራታል፡፡ ይህም ወትሮውንም የተንዛዛው የውስጥ ውድድር በቀጣዩ አመት ምን መልክ ሊኖረው እንደሚችል አሳሳቢ ሆኗል፡፡