ያሬድ ካሳየ ቅጣት ተላልፎበታል

ያሬድ ካሳየ ቅጣት ተላልፎበታል

ባለፉት ሁለት ቀናት መነጋገሪያ የነበረው የኢትዮጵያ መድኑ ተጫዋች ያሬድ ካሳየ እንዲሁም ሲዳማ ስፖርት ክለብ ከፌዴሬሽኑ ቅጣት ተጥሎባቸዋል።

ከትናንት በስቲያ በአበበ ቢቂላ ስታዲየም በተካሄደው የኢትዮጵያ ዋንጫ ግማሽ ፍጻሜ ጨዋታ ሲዳማ ቡና በመለያ ምቶች ኢትዮጵያ መድንን አሸንፎ ወደ ፍጻሜው ማለፉ ይታወሳል። በዚሁ ጨዋታ ላይ በኢትዮጵያ መድን በኩል 32ኛ ደቂቃ ላይ ላይ በረመዳን የሱፍ ተቀይሮ እንዲወጣ የተደረገው ያሬድ ካሳየ ተቀይሮ በሚወጣበት ቅጽበት መለያውን አውልቆ በመወርወሩ መነጋገሪያ እንደነበር እርሱም አመሻሽ ላይ ለሶከር ኢትዮጵያ በማሳወቅ በይፋ ይቅርታ ጠይቋል።

የኢትዮጵያ ዋንጫ ውድድር አዘጋጅ ኮሚቴም የቀረቡለትን ሪፖርቶች ከመረመረ በኋላ ተጨዋቹ የክለቡን መለያ ለዋናው አሰልጣኝ ክብር ባለመስጠቱ አውልቆ መወርወሩ አስነዋሪ ድርጊት ነው በማለት ለፈጸመው ጥፋት በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት 10,000 (አስር ሺህ ብር) የገንዘብ ቅጣት እንዲቀጣ ተወስኖበታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጨዋታው ከተጠናቀቀ በኃላ የሲዳማ ቡና እግር ኳስ ቡድን ዓርማ የያዙና መለያ የለበሱ ደጋፊዎች ካታንጋ አካባቢ የነበሩ 20 (ሃያ) መቀመጫዎች በመሰባበር ከቦታቸው ተነቅለው የተጣሉ በመሆኑ በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የዲሲፕሊን መመሪያ መሠረት ክለቡ እንዲተካ እና እንዲያሠራ ተወስኗል፡፡ ለመተካት እና ለማሠራት እንዲቻል ባለንብረቱ በሚያቀርበው ግምት መሰረት እንዲከፍልም ተወስኗል።