በኢትዮጵያ ዋንጫ የግማሽ ፍጻሜ ጨዋታዎች ምክንያት ለቀናት ተቋርጦ የነበረው የሲቢኢ የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ዛሬ በሶስት ጨዋታዎች ጅማሮውን ሲያደርግ ጨዋታዎቹን የተመለከቱ መረጃዎችም እንደሚከተለው አሰናድተንላችኋል።
ሀዋሳ ከተማ ከ ኢትዮጵያ ቡና
በደረጃ ሰንጠረዡ በ45 ነጥብ እና በ+6 የግብ ክፍያ 7ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው ሀዋሳ ከተማ በአሁኑ ወቅት አስከፊ የሚባል የድል ረሃብ ውስጥ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት 10 ተከታታይ የሊግ ጨዋታዎች ማሸነፍ ያልቻለ ሲሆን ለመጨረሻ ጊዜ ድል ያስመዘገበው መቐለ 70 እንደርታን 1 ለ 0 በሆነ ባሸነፈበት ውጤት ነበር። የዛሬውን የጨዋታ ቀን ላይ ለመድረስ በትክክል 79 ቀናትን የፈጀ የድል ድርቅ ያሳለፈው ሀዋሳ ባለፉት አምስት ጨዋታዎቹም 3 ሽንፈት እና 2 አቻ በመለያየት 2 ነጥብ ብቻ ማሳካት ችሏል። የቡድኑ ዋና ጥንካሬ በሊጉ 26 ግቦች ብቻ ያስተናገደው የተከላካይ ክፍሉ ቢሆንም ባለፉት አምስት ጨዋታዎች 1 ግብ ብቻ ያስቆጠረው የማጥቃት መስመሩ ግን ክለቡን ለከፍተኛ ችግር ዳርጎታል።
በተቃራኒው በ46 ነጥብ እና በ0 የግብ ዕዳ ሰንጠረዡ ላይ በ5ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ኢትዮጵያ ቡና ከተጋጣሚው የተሻለ ተስፋ ሰጪ ወቅታዊ እንቅስቃሴ እያሳየ ይገኛል። ቡድኑ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎቹ 2 ድል 2 አቻ እና 1 ሽንፈት በማስተናገድ 8 ነጥቦችን የሰበሰበ ሲሆን በተለይም በመጨረሻው ጨዋታ ጠንካራውን ፋሲል ከነማን ከመመራት ተነስቶ 2 ለ 1 ማሸነፉ ለዛሬው ጨዋታ ትልቅ የስነ-ልቦና መነሳሳትን ይፈጥርለታል። የኢትዮጵያ ቡና ዋናው ጠንካራ ጎን በሊጉ 36 ግቦችን ማስቆጠር የቻለው አስፈሪው የማጥቃት መስመሩ ቢሆንም በተመሳሳይ መልኩ 36 ግቦችን መልሶ ያስተናገደው እና በቀላሉ የሚጋለጠው የኋላ ክፍሉ ግን የቡድኑ ደካማ ጎን ሆኖ ቀጥሏል።
ሀዋሳ ከተማ በረከት ሳሙኤል ከቅጣት መልስ ለዛሬው ጨዋታ ዝግጁ ሆነለታል። በኢትዮጵያ ቡና በኩል አሰልጣኙ መረጃ ለመስጠት ፍቃደኛ ሳይሆኑ ቀርተዋል።
ከሊጉ የተሳትፎ ዝርዝር ጠፍተው የማያውቁት ክለቦቹ ከዚህ ቀደም ለ53 ጊዜ ተገናኝተዋል። በጨዋታዎቹ ኢትዮጵያ ቡና 18 ጊዜ ድል ሲያደርጉ በአንፃሩ ሀዋሳ ከተማዎች 16 ድል አድርገዋል የተቀሩት 19 ግንኙነቶች ደግሞ ነጥብ በመጋራት የተደመደሙ ነበሩ። ኢትዮጵያ ቡና 65 ሀዋሳ ከተማ ደግሞ 56 ግቦችን ማስመዝገብ ችሏል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ
በደረጃ ሰንጠረዡ 18ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጦ በ-15 የግብ ዕዳ እና በ35 ነጥብ የህልውና ትግል እያደረገ የሚገኘው ድሬዳዋ ከተማ ድል ካደረገ በትክክል 50 ቀናትን አስቆጥሯል። ቡድኑ ለመጨረሻ ጊዜ ምድረገነት ሽረን ካሸነፈ በኋላ ባደረጋቸው 7 ተከታታይ ጨዋታዎች ድል አድርጎ 3 ነጥብ ማግኘት ያልቻለ ሲሆን ባለፉት አምስት ፍልሚያዎቹም የሰበሰበው 3 ነጥብ (3 አቻ እና 2 ሽንፈት) ብቻ ነው። በሜዳ ላይ በተጋጣሚዎች በቀላሉ ላለመሸነፍ የሚያሳየው አልሸነፍ ባይነት እና ጨዋታን የማቀዝቀዝ ብቃቱ እንደ ጥንካሬ የሚነሳለት ቢሆንም በተደጋጋሚ የሚታይበት የዲሲፕሊን መጓደል (ተደጋጋሚ ቀይ ካርዶች) እና ከቀጥተኛ ኳሶች ውጪ የፊት መስመሩ ላይ የሚስተዋለው የፈጠራ አቅም ማነስ የቡድኑ ዋነኛ ድክመቶች ናቸው።
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ መካከለኛ ክፍል ላይ በ43 ነጥብ እና በ-3 የግብ ዕዳ 10ኛ ደረጃን ይዞ የሚገኘው ቅዱስ ጊዮርጊስ በአንፃራዊነት በተሻለ የመረጋጋት ስሜት ላይ ይገኛል። ፈረሰኞቹ ባለፉት አምስት ጨዋታዎቻቸው 2 ድል 1 አቻ እና 2 ሽንፈት በማስመዝገብ 7 ነጥቦችን ያጠራቀሙ ሲሆን በመጨረሻው ሳምንት ሀዋሳን 1 ለ 0 አሸንፈው መውጣታቸው ለዛሬው ጨዋታ የሞራል የበላይነት ይሰጣቸዋል። ቡድኑ በስብስቡ ውስጥ ባለው አማካይ ክፍሉ ጨዋታን በመቆጣጠር ረገድ የተሻለ ጥንካሬ ያለው ቢሆንም አልፎ አልፎ በሚያደርጋቸው ጨዋታዎች ላይ የሚታይበት ወጥ ያልሆነ አቋም እና በተከላካዮች ዘንድ የሚስተዋለው ድንገተኛ መዘናጋት ጨዋታዎችን በቀላሉ እንዳያሸንፍ እንቅፋት ሆኖበታል።
በድሬዳዋ ከተማ በኩል በብሔራዊ ቡድኑ ጥሪ የተደረገለት ሬድዋን ሸረፋ በቅጣት ምክንያት ቡድኑን አያገለግልም። በቅዱስ ጊዮርጊስ በኩል ተገኑ የመሰለፉ ነገር አጠራጣሪ ሲሆን በቅርቡ ቡድኑን የተቀላቀሉት የውጭ ሀገር ዜግነት ያላቸው ተጫዋቾች ከፊፋ ጋር ያለው ጉዳይ አለማለቁን ተከትሎ ከዛሬው ጨዋታ ውጪ መሆናቸውን ማወቅ ተችሏል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ27 ጊዜያት ተገናኝተው ቅዱስ ጊዮርጊስ 16ቱን በማሸነፍ ቀዳሚ ሲሆን ድሬዳዋ ከተማ ደግሞ 5ቱን አሸንፏል። ቀሪዎቹ 6 ጨዋታዎች ደግሞ በአቻ ውጤት ፍፃሜያቸውን አግኝተዋል። ፈረሰኞቹ 44፣ ብርቱካናማዎቹ 20 ጎሎች አስቆጥረዋል።
መቻል ከ አርባምንጭ ከተማ
በሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ሁለተኛ ደረጃ ላይ በ53 ነጥብ እና በ+18 የግብ ክፍያ የተቀመጠው መቻል የዋንጫ ተፎካካሪነቱን ለማረጋገጥ ዛሬ ወደ ሜዳ ይገባል። ቡድኑ ባለፉት አምስት ጨዋታዎች ምንም ሽንፈት ያላስተናገደ ሲሆን በጠንካራ ግስጋሴ 2 ድል እና 3 አቻ በማስመዝገብ 9 ነጥቦችን ሰብስቧል። የመቻል ትልቁ ጥንካሬው የተረጋጋው የኳስ ቁጥጥር ስልቱ ሲሆን በተለይም የአጥቂ መስመሩ እና አማካዮቹ ያላቸው የተቀናጀ ግንኙነት ተጋጣሚ ላይ በቀላሉ የግብ ዕድል እንዲፈጥሩ አግዟቸዋል። ሆኖም ግን ቡድኑ ጨዋታዎችን ቀድሞ መርቶ የማጠናቀቅ እና እድሎችን በአንድ ጊዜ ወደ ግብ የመቀየር ጉድለት የሚታይበት መሆኑ ብዙ ጨዋታዎችን ወደ አቻነት እንዲቀየሩበት ያደረገው ዋነኛ ደካማ ጎኑ ነው።
በተቃራኒው የደረጃ ሰንጠረዡን ግርጌ ታች ላይ በ29 ነጥብ እና በ-15 የግብ ዕዳ 20ኛ ደረጃ ላይ የሚገኘው አርባምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለማምለጥ እጅግ አስቸጋሪ ፈተና ከፊቱ ይጠብቀዋል። ክለቡ ባለፉት አምስት የሊግ ጨዋታዎች ማሳካት የቻለው 4 ነጥብ ብቻ ሲሆን 1 ድል፣ 1 አቻ እና 3 ሽንፈት ያስመዘገበበት ደካማ ስታቲስቲክስ አለው። የአርባምንጭ ዋነኛ ጥንካሬው በአንጻራዊነት ፈጣን በሆኑት ተጫዋቾቹ አማካኝነት በድንገተኛ መልሶ ማጥቃት የሚፈጥሩት አስደናቂ ፍጥነት ቢሆንም የተከላካይ ክፍሉ ከአማካይ መስመሩ ጋር ያለው ርቀት ሰፊ መሆኑ ቡድኑን ለተጋጣሚ ጥቃት በቀላሉ ተጋላጭ ያደረገው ትልቁ ደካማ ጎኑ ነው።
በመቻል በኩል የተሟላ የቡድን ዜና ማግኘት ባንችልም ባሳለፍነው የጨዋታ ሳምንት አምስተኛ ቢጫ ካርድ ያየው የመስመር ተከላካዩ ዓለምብርሃን ይግዘው በቅጣት ከዛሬው ጨዋታ ውጭ መሆኑን አውቀናል። አርባምንጭ ከተማ ከጉዳትም ሆነ ከቅጣት ነፃ የሆነ ስብስቡን ይዞ ለጨዋታው ይቀርባል።
ሁለቱ ቡድኖች ከዚህ ቀደም ለ21 ጊዜያት ያህል የተገናኙ ሲሆን መቻል 8 ጨዋታ አርባ ምንጭ ከተማ ደግሞ 6 ጨዋታዎችን ሲያሸንፉ በቀሪዎቹ 7 ጨዋታዎች ነጥብ ተጋርተዋል። አዞዎቹ 16 መቻሎች ደግሞ 19 ጎሎችን በግንኙነታቸው አስቆጥረዋል።

