የፈረሰኞቹ መታገድ ቀጥሏል

የፈረሰኞቹ መታገድ ቀጥሏል

የቅዱስ ጊዮርጊስ የዝውውር እገዳ ሳይነሳ ሲቀር ክለቡ በቀጣዩ የዝውውር መስኮትም የውጪ ተጫዋች ማስፈረም እንደማይችል ታውቋል።

አንጋፋው ክለብ ቅዱስ ጊዮርጊስ ከዓለም አቀፉ የእግር ኳስ ማኅበር (ፊፋ) ጋር የነበረበትን የገንዘብ ዕዳ ሙሉ በሙሉ ከፍሎ ቢያጠናቅቅም የተጣለበት አዳዲስ የውጪ ተጫዋቾችን የመመዝገብ እገዳ ሳይነሳለት መቅረቱንና በቀጣዩ የዝውውር መስኮትም የውጪ ተጫዋቾችን ማስፈረም እንደማይችል በይፋ አስታወቀ።

ክለቡ ዛሬ ግንቦት 21 ቀን 2018 ዓ/ም ባወጣው ዝርዝር መግለጫ ጉዳዩን በሕጋዊ መንገድ ለመፍታት ከፍተኛ ጥረት ቢያደርግም የፊፋ እገዳ መፅናቱን ይፋ አድርጓል።

የዚህ አወዛጋቢ እገዳ መነሻ በ2017 ዓ/ም የውድድር ዘመን ላይ የተፈጠረ ሲሆን ቅዱስ ጊዮርጊስ በወቅቱ ላስፈረማቸው አራት የውጭ ሀገር ተጫዋቾች ተገቢውን ደመወዝ መክፈል ባለመቻሉ ተጫዋቾቹ ለፊፋ የክስ አቤቱታ አቅርበው ነበር። ፊፋም የሁለቱንም ወገኖች ክርክር ተመልክቶ በፊፋ የግጭት አፈታት ችሎት (FIFA Dispute Resolution Chamber) አማካኝነት ሕዳር 11 ቀን 2018 ዓ/ም በሰጠው ውሳኔ ክለቡ ለሁለት ተከታታይ የዝውውር ወቅቶች አዳዲስ ተጫዋቾችን እንዳይመዘግብ እገዳ ጥሎበት ነበር።

ክለቡ በወቅቱ በተሰጠው የ30 ቀናት ጊዜ ውስጥ ክፍያውን ባለመፈጸሙና ይግባኝም ባለመጠየቁ ምክንያት ቅጣቱ የጸና ሆኗል።

ይሁንና ክለቡ ከአቶ ጀማል አህመድ በስጦታ ባገኘው ከ26 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆን የገንዘብ ድጋፍ ለአራቱም ተጫዋቾች መከፈል ያለበትን ዕዳ ከነወለዱና ከነቅጣቱ ሙሉ በሙሉ ከፍሎ አጠናቋል። ይህንን ክፍያ ተከትሎም በእያንዳንዱ አራቱ ተጫዋቾች ምክንያት ተጥሎ የነበረው የዝውውር እገዳ መነሳቱን የሚገልጹ አራት ደብዳቤዎችን ክለቡ ከፊፋ በይፋ ተቀብሏል።

ክለቡ ይህንን መረጃ መነሻ በማድረግና የያዝነውን የውድድር ዘመን በጥሩ ደረጃ ለማጠናቀቅ በማሰብ አራት አዳዲስ የውጭ ሀገር ተጫዋቾችን ወደ ሀገር ውስጥ ያስገባቸው ሲሆን ተጫዋቾቹ መፈረም የሚችሉ መሆናቸውን ከኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽንም ማረጋገጫ አግኝቶ ነበር። ነገር ግን ተጫዋቾቹ የሕክምና ምርመራቸውን አጠናቅቀው በክለቡ የዓለም አቀፍ የዝውውር ሥርዓት (TMS) ላይ ለመመዝገብ ሲሞከር እገዳው አሁንም በሲስተሙ ላይ እንዳልተነሳ ለማወቅ ተችሏል።

ይህንን ተከትሎ ክለቡና የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እንዲሁም የተጫዋቾቹ ጠበቃ ጭምር ክፍያው ሙሉ በሙሉ መጠናቀቁን የሚገልጽ ማብራሪያ ለፊፋ በተደጋጋሚ ቢልኩም ከፊፋ የተሰጠው ምላሽ ግን የሕዳር 11 ውሳኔ የጸና መሆኑን የሚገልጹ አውቶሜትድ (የአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ) መልዕክቶች ብቻ ነበሩ። ቅዱስ ጊዮርጊስ ጉዳዩን በበላይነት ለመቋጨት በአሜሪካ ማያሚ እና በስዊዘርላንድ ዙሪክ የሚገኙ ሁለት የፊፋ ፈቃድና የረጅም ጊዜ ልምድ ያላቸውን ዓለም አቀፍ ጠበቆች ቀጥሮ ሁሉንም ሕጋዊ አማራጮች ቢጠቀምም ፊፋ ግን በደንቡ (RSTP) አንቀጽ 17 ንዑስ አንቀጽ 4 መሠረት የተቀረው የምዝገባ እገዳ ሙሉ በሙሉ ሊጠናቀቅ ይገባል የሚለውን ጠንካራ አቋሙን አጽንቷል። ይህም ማለት ክለቡ በቀጣዩ የዝውውር መስኮትም የሀገር ውስጥ ብቻ እንጂ ከውጪ አዳዲስ ተጫዋቾችን ማስፈረም አይችልም ብሏል።

የቅዱስ ጊዮርጊስ ስፖርት ክለብ የዓለም አቀፍ እግር ኳስ ደንቦችንና ውሳኔዎችን እንደሚያከብር ገልጾ በአዲስ በተመረጠው የሥራ አመራር ቦርድ አማካኝነት የቡድኑን ጥንካሬ፣ ተቋማዊ መረጋጋት እና ስፖርታዊ ግቦችን ለማሳካት ሥራውን በትኩረት እንደሚቀጥል አስታውቋል።