ሀዲያ ሆሳዕና እና ምድረገነት ሽረ 1ለ1 ሲለያዩ ሸገሮች ፋሲል ከነማን ባለቀ ደቂቃ በተቆጠረች ብቸኛ ግብ በማሸነፍ ደረጃቸውን አሻሽለዋል።

ምድረገነት ሽረ ከ ሀዲያ ሆሳዕና
በሀዲያ ሆሳዕና ጨዋታ የበላይነት ጅማሮውን ያደረገው በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም የተደረገው ቀዳሚው ጨዋታ በኢዮብ ዓለማየሁ ሁለት ከሳጥን ውጭ አደገኛ ሙከራዎች ለግብ የቀረቡ አጋጣሚዎችን እያሰመለከተን ሲቀጥል ቀዝቀዝ ብለው ጀምረው የኋላ ኋላ ኳስ ይዘው ለመጫወት ጥረት ያደረጉት ሽረዎች ግብ አስተናግደዋል።

ከተደጋጋሚ ሙከራ በኋላ በመልሶ ማጥቃት በቀኝ መስመር ኳስ ያገኙት ነብሮቹ ደስታ ዋሚሾ ወደ ሳጥን ያሻገረውን ኳስ ብቻውን ሆኖ ያገኘው ኢዮብ ዓለማየሁ 35ኛው ደቂቃ ላይ አስቆጥሮ መሪ አድርጓቸዋል። ከግቡ በኋላም ሁለቱም ቡድኖች ግብ ለማግኘት የሚያደርጉት እንቅስቃሴ የጠራ ሙከራ ሳያስመለክተን ለእረፍት ወጥተዋል።
ከእረፍት መልስ ጨዋታ ሲመለስ ነብሮቹ ያስቆጠሩት ግብ የበቃቸው በሚመስል ሁኔታ ወደኋላ አፈግፍገው ከኳስ ጋር እየቆዩ ሲመለሱ ምድረገነት ሽረዎች በበኩላቸው የሚያገኙትን አጋጣሚ ወደ ግብነት ለመቀየር ሙከራዎችን ለማድረግ በጥሩ የነብሮቹ ተከላካይ መስመር ቀላል ሳይሆንላቸው ቀርቶ እምብዛም ለግብ የቀረበ ሙከራ ማድረግ አልቻሉም።

በዚህም ጨዋታው በመጀመሪያ አጋማሽ በተቆጠረ ግብ የሚጠናቀቅ እየመሰለ ቀጥሎ ወደ መገባደጃው ሲቃረብ ምድረገነት ሽረዎች የአቻነት ግብ አግኝተዋል። 88ኛው ደቂቃ ላይ ከመስመር የተሻማውን ኳስ በእረፍት ተቀይሮ ወደ ሜዳ የገባው ዳንኤል ዳርጌ በግንባሩ ገጭቶ አስቆጥሮ ጨዋታው በአቻ ውጤት እንዲጠናቀቅ አድርጓል።
ፋሲል ከነማ ከ ሸገር ከተማ
ፋሲል ከነማን ከሸገር ከተማ ያገናኘው ሳቢ ያልነበረው ሁለተኛው ጨዋታ በአንደኛው አጋማሽ ሁለት ዒላማቸውን የጠበቁ ሙከራዎችን ሁለቱም ቡድኖች አድርገዋል። የዐፄዎቹን ግልፅ የግብ ማግባት ሙከራ አንዋር ሙራድ ከሳጥን ውጪ አክርሮ በመምታት አድርጎ ግብ ጠባቂው ሲያግድበት የሸገሮችን የመጀመሪያው አደገኛ ሙከራ የአጋማሹ መገባደጃ ላይ ቡልቻ ሹራ እንዲሁ ከሳጥን ውጪ አድርጎ ግብ ጠባቂው ተቆጣጥሮበታል። ከሙከራዎች ጋር መታጀብ ያልቻለው ጨዋታውም አጋማሹ ያለግብ ተገባዶ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል።

በተሻለ እንቅስቃሴ በተመለሰው በሁለተኛ አጋማሽ በተለይም ዐፄዎቹ ድንቅ ሙከራዎችን ማድረግ ችለዋል። ከሙከራዎቹ መካከልም ናትናኤል ገብረጊዮርጊስ ከሳጥን ውጪ መሬት ለመሬት አክርሮ መትቶ የግቡ ቋሚ ብረት የመለሰበት፣ ኪሩቤል ዳኜ ከሳጥኑ ጠርዝ መትቶት ባሕሩ ነጋሽ ጨርፎ ያወጣባቸው እንዲሁም አቤነዘር ከሳጥን ውጭ አድርጎ ለጥቂት ከግቡ ታክኮ የወጣባቸው ሙከራዎች ተጠቃሾች ነበሩ።
የዐፄዎቹን ማጥቃት እንቅስቃሴ እየተከላከሉ በመልሶ ማጥቃት ለመግባት ጥረት ያደረጉት ሸገሮች አሚር አብዶ በራሱ ጥረት ያገኘውን ኳስ ከሳጥን ውጪ አክርሮ መትቶ ሞይስ ፖዎቲ እንዴትም ጨርፍ ካወጣባቸው በኋላ ሌላ ሙከራ ሳያደርጉ ቆይተው ባለቀ ደቂቃ ግብ አግኝተዋል።

ከመሃል የሾለከለትን ኳስ ቡልቻ ሹራ በፍጥነት ለመድረስ ሲጥር ግብ ጠባቂው በሠራበት ጥፋት ፍፁም ቅጣት ተሰጥቷቸው አምበሉ ሄኖክ አዱኛ 90ኛው ደቂቃ ላይ ወደ ግብነት ቀይሮ ባለቀ ደቂቃ ለሸገሮች ሦስት ነጥብ አስገኝቶላቸዋል።

