ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባ ምንጭ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ሪፖርት | ቅዱስ ጊዮርጊስ እና አርባ ምንጭ ከተማ ወሳኝ ድል ተቀዳጅተዋል

ፈረሰኞቹ ድሬዳዋ ከተማን 2-1 በሆነ ውጤት ሲያሸንፉ መቻሎች በበኩላቸው የዋንጫ ጉዟቸውን አጣብቂኝ ውስጥ የከተተ ሽንፈት በአርባምንጭ ከተማ አስተናግደዋል።

ድሬዳዋ ከተማ ከ ቅዱስ ጊዮርጊስ

የመጀመሪያው አጋማሽ በድሬዳዋ ከተማ የኳስ ቁጥጥር የበላይነት ቢጀመርም ይበልጥ ውጤታማ የነበሩት ግን በአጫጭር ንክኪዎች በፍጥነት ወደ ተጋጣሚ የግብ ክልል መድረስ የቻሉት ቅዱስ ጊዮርጊሶች ነበሩ። በዚህ የጨዋታ ፍሰት መነሻነት ፈረሰኞቹ በ25ኛው ደቂቃ ላይ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። ቶሎሳ ንጉሴ በጥሩ እይታ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ታዳጊው ብሩክ አለማየው ለተከታታይ ሁለተኛ ጨዋታ ኳስን መረብ ላይ በማሳረፍ ክለቡን መሪ ማድረግ ችሏል።

ይሁን እንጂ የፈረሰኞቹ ደስታ መቆየት የቻለው ለሁለት ደቂቃዎች ብቻ ነበር። በጨዋታው ለመበለጥ ያልፈለጉት ድሬዳዋ ከተማዎች በ27ኛው ደቂቃ ላይ ከቅጣት ምት የተሻገረውን ኳስ በመጠቀም አፋጣኝ ምላሽ ሰጥተዋል። ድልአዲስ ገብሬ ያቆመውን ኳስ ወደ ግብ ሲሞክረው ግብ ጠባቂው ሻሂኪሎ ፋርክ ቢያድነውም በቅርብ አቋቋም ላይ ተሰናድቶ የነበረው አስራት ቱንጆ የተመለሰውን ኳስ ወደ ግብነት በመቀየር ብርቱካናማ ለባሾቹን በፈጣን ሁኔታ ወደ ጨዋታው መመለስ ችሏል።

ጨዋታው ይበልጥ ተመጣጣኝና ማራኪ መልክ መያዝ በጀመረበት በዚህ አጋማሽ ፈረሰኞቹ በድጋሚ ወደ መሪነት ለመመለስ ብዙ ጊዜ አልፈጀባቸውም። በ35ኛው ደቂቃ ላይ ፍፁም ጥላሁን ከሜዳው የቀኝ መስመር የተጋጣሚ ተጫዋቾችን በጥሩ ክህሎት በማለፍ ያሻገረውን ኳስ ያገኘው ሀብታሙ ጉልላት በእግሩ በመጨረስ ወደ ግብነት ቀይሮታል። ይህ ግብ ቅዱስ ጊዮርጊስን በድጋሚ መሪ ማድረግ የቻለና የመጀመሪያውን አጋማሽ በፈረሰኞቹ የበላይነት የደመደመ ነበር።

የሁለተኛው አጋማሽ የጨዋታ ክፍለ ጊዜ ረዘም ላለ ጊዜ ጥንቃቄ የተሞላበትና ምንም አይነት የጎላ የግብ ሙከራዎች ያልታዩበት ሆኖ ቆይቷል። ይሁን እንጂ በመጨረሻዎቹ አስር ደቂቃዎች ላይ የድሬዳዋ ከተማ ተጫዋቾች የአቻነት ግብ ፍለጋ ተጭነው በመጫወት ጠንካራ ጫና መፍጠር ችለው ነበር። ነገር ግን ብርቱካናማዎቹ ያደረጉት ተደጋጋሚ ጥረት በአልበገር ባዩ እና በጠንካራው የቅዱስ ጊዮርጊስ የተከላካይ መስመር ምክንያት ሳይሳካ ቀርቷል። በዚህም መሰረት ጨዋታው በፈረሰኞቹ የ 2-1 ጠባብ ግን አስገራሚ ድል ተጠናቋል።

መቻል ከ አርባ ምንጭ ከተማ

ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት ጥረት የሚያደርጉት አርባ ምንጭ ከተማዎች ለዋንጫ ክብር ከሚጫወተው መቻል ጋር ባደረጉት የምሽቱ ጨዋታ ግብ በማስቆጠሩ ረገድ ቀዳሚ መሆን ችለዋል። በ32ኛው ደቂቃ ላይ በፈጠሩት ፈጣን መልሶ ማጥቃት ኤፍሬም ታምራት በጥሩ ቅብብል ያመቻቸውን ኳስ አሸናፊ ተገኝ በጥሩ አጨራረስ ወደ ግብነት ቀይሮ አርባምንጭን መሪ አድርጓል። ከዚህ ግብ በኋላ መቻሎች የአቻነት ግብ ለማግኘት በቁጥር በዝተው ተጭነው ለመጫወት ቢሞክሩም የሚያደርጉትን ጫና የአርባምንጭ ተከላካዮች በመቋቋማቸው የመጀመሪያው አጋማሽ በአዞዎቹ 1ለ0 መሪነት ተጠናቋል።

ሁለተኛው አጋማሽ እንደተጀመረ መቻሎች በፍጥነት ወደ ጨዋታው የመለሳቸውን ግብ ማስቆጠር ችለዋል:: ከማዕዘን ምት ተሻግሮ በተጫዋቾች የተጨራረፈውን ኳስ ቻርለስ ሙሴጌ አግኝቶ ወደ ግብነት በመቀየር መቻልን አቻ ማድረግ ችሏል። ይሁን እንጂ አርባ ምንጭ ከተማዎች ሳይደናገጡ ወዲያውኑ ምላሽ ሰጥተዋል። በ60ኛው ደቂቃ ላይ መነሻውን ከቀኝ መስመር ያደረገውን ኳስ ጄሮም ፍሊፕ በጥሩ ቅልጥፍና ተጫዋቾችን አልፎ አመቻችቶ ያቀበለውን ኳስ ቴዎድሮስ በንቲ መረብ ላይ በማሳረፍ አዞዎቹን በድጋሚ መሪ አድርጓል።

ከግቧ መቆጠር በኋላ መቻሎች የአቻነት ግብ ፍለጋ በቁጥር በዝተው ወደፊት በመጠጋት ተከታታይ ጥረቶችን ሲያደርጉ በአንፃሩ የአርባምንጭ ከተማ ተጫዋቾች በራሳቸው የግብ ክልል በጥንቃቄ አፈግፍገውና ተጠቅጥቀው በመከላከል የመቻሎችን ሀሳብ ማክሸፍ ችለዋል። ጨዋታውም በአርባ ምንጭ 2ለ1 አሸናፊነት መጠናቀቁን ተከትሎ አርባ ምንጭ ከተማ ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያግዘውን ወሳኝ ሶስት ነጥብ ሲያገኝ መቻሎች በበኩላቸው ከሊጉ መሪ ጋር ያላቸውን የነጥብ ልዩነት የሚያጠቡበትን ወርቃማ ዕድል ሳይጠቀሙበት ቀርተዋል።