​“ኢትዮጵያም ሆነ ዩጋንዳ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሚያሸንፉን ሀገራት ነበሩ” የቡሩንዲ አሰልጣኝ ኒዩንጊኮ ኦሊቨር

ስለጨዋታው

“የመጀመሪያ ግብ ካስቆጠርን በኃላም ሆነ እነሱ (ኢትዮጵያ) አቻ ሲሆኑ ተጫዋቾች እንዲረጋጉ ነበር ስራ ስሰራ የነበረው፡፡ ቀሪ ደቂቃዎች እንዳሉ አውቀው ወደ ጨዋታውን እንዲመለሱ ነበር ያደረኩት፡፡ ኢትዮጵያም ሆነ ዩጋንዳ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የሚያሸንፉን ሃገራት ነበሩ፡፡ አሁን ግን ከዩጋንዳ ጋር አቻ ስንለያይ ኢትዮጵያን 4-1 አሸንፈናል፡፡ ይህ የሚያሳየው እየተዘጋጀን እንደመጣን ነው፡፡ በቂ አይደለም ግን መሻሻል እንችላለን፡፡ ምድባችንን በመሪነት ለማጠናቀቅ እና ቀጣይ ጨዋታችንን ለማሸነፍ ወደ ሜዳ እንገባለን፡፡ በቡድናችን ጉዳት የለም ግን ዛሬ በጨዋታው ላይ ተጫዋቾቼ የበዙ ቢጫ ካርዶችን አይተዋል፡፡ ወጣት ስለሆኑ እንዲረጋጉ አድርጌያለው፡፡ ለቀጣዩ ጨዋታ በደንብ እንዘጋጃለን፡፡”

ስለፊስተን አለመሰለፍ እና የኢትዮጵያ ተከላካይ መስመር

“ፊስተን አብዱልራዛክ በአንጎላው ፕሬሜሮ አውጉስቶ ለዝውውር ስለተጠየቀ ማክሰኞ ወደ ስፍራው በማቅናቱ ዛሬ ሊያገለግለን አልቻለም፡፡ ሆኖም አርብ ከሰዓት ተመልሶ መጥቶ ይቀላቀለናል፡፡

“ከዩጋንዳ ጋር ስንጫወት ዩጋንዳ በጣም ጠንካራ ነበር፡፡ ከባድ ከመሆኑ አንፃር የእነሱን ተከላካዮች ለማለፍ ተስኖን ነበር፡፡ የኢትዮጵያ የተከላካይ መስመር በአንፃሩ በጣም የሳሳ ሆኖ ነው ያገኘሁት፡፡ ምንአልባት አንድ ላይ አብረው የቆዩ እና የተዘጋጁ እንዳልሆነ ያስታውቃል፡፡ እኛ እንደሰራነው እነሱም ጠንክረው ሰርተው መሻሻል ይችላሉ ብዬ አስባለው፡፡”

ስለፍፁም ቅጣት ምቱ እና ቀጣይ ጨዋታ

“ዳኛው ተሳስቷል፡፡ ፍፁም ቅጣት ምት አልነበረም፡፡ ዳኛ ሰው ነው ይሳሳታል፡፡ ለእኔ የፍፁም ቅጣት ምት አልነበረም ግን ተጫዋቾቼን በማረጋጋት ጨዋታው እንዳላለቀ በማስረዳት ውጤት ይዘን ለመውጣት ችለናል፡፡

“ሁሉንም ጨዋታዎች ለማሸነፍ ነው የተገኘነው፡፡ ይህ ቀላል ተጋጣሚ ነው ይህ ከባድ የሚል እሳቤ የለንም፡፡ ተጫዋቾቼ ያሉበትን ደረጃ ነው ማየት የምፈልገው። ምክንያቱም ለአፍሪካ ዋንጫ ለማለፍ በማጣሪያው ጨዋታ ይህ ውድድር ግብአት ይሆነናል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *