​ኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 6ኛ ሳምንት የእሁድ ጨዋታዎች ቅድመ ዳሰሳ

በሊጉ የ6ኛ ሳምንት መርሀ ግብር መሰረት ስድስት ጨዋታዎች በእለተ እሁድ ሊደረጉ ቀጠሮ የተያዘላቸው የነበረ ቢሆንም የሸገር ደርቢ ወደ ማክሰኞ በመዘዋወሩ  ምክንያት በክልል ከተሞች የሚደረጉት አምስት ጨዋታዎች ቀጥለው የሚደረጉ ይሆናል። እነዚህን አምስት ጨዋታዎችንም እንዲህ ተመልክተናቸዋል።

ሲዳማ ቡና ከ ወልድያ

የአምናውን አቋሙን መድገም የተሳነው ሲዳማ ቡና በእስካሁኑ የሊጉ ጉዞው የሰበሰባቸው አራት ነጥቦች በሙሉ ከአቻ ውጤቶች የተገኙ ናቸው። ቡድኑ ከነዚህ መሀል ግብ ማስቆጠር የቻለው ደግሞ በሁለቱ ላይ ብቻ መሆኑ በደረጃ ሰንጠረዡ መጨረሻ ላይ ከሚመኙ ክለቦች አንዱ እንዲሆን አስገድዶታል።  ተጋጣሚው ወልድያም ከሲዳማ በሁለት ደረጃ ከፍ ብሎ ይቀመጥ እንጂ እስካሁን ማሸነፍ የቻለው በአንድ ጨዋታ ብቻ ነው። የሳምኑቱ የመቐለ ጨዋታ በረብሻ ምክንያት ሲተላለፍ ከዛ በፊት ሁለት ጨዋታዎችን በአቻ ውጤት ማጠናቀቁ እና በሀዋሳ ከተማ 4-1 መሸነፉ የሚታወስ ነው። አምና ክለቦቹ 22ኛው ሳምንት ላይ ሲገናኙ ሲዳማ ቡና 2-1 ማሸነፍ ችሎ የነበረ ሲሆን ፌ/ዳኛ ዳዊት አሳምነው በሚመሩት የነገው ጨዋታ ማሸነፍ የቻለ ቡድን የእፎይታ ጊዜ እንደሚያገኝ ይጠበቃል።

አዲስ ግደይ እና አበበ ጥላሁን ከሲዳማ እንዲሁም ተስፋዬ አለባቸው እና ብሩክ ቃልቦሬ ከወልድያ በኩል ለብሔራዊ ቡድን የተመረጡ መሆኑ ይታወቃል። ከዚህ ውጪ ወልድያ አዳሙ መሀመድን ፣ ተስፋውን ሸጋውን እና አንዷለም ንጉሴን በጉዳት ያጣል። መሳይ አያና እና ትርታዬ ደመቀ በቅጣት ከሲዳማ የቡድን ስብስብ ውጪ ሲሆኑ መሀመድ ኮናቴ እና ቀለል ያለ ልምምድ መስራት የጀመረው ፈቱዲን ጀማልም ለጨዋታው ላይደርሱ እንደሚችሉ ሰምተናል።

በሜዳው የግብ ዕድሎችን በመፍጠሩ ረገድ ተሻሽሎ የታየው ሲዳማ ቡና ከአምናው በተቃራኒ ከሜዳው ውጪም ግብ ስለማስቆጠር የሚያስበውን ወልድያን ሲያስተናግድ ክፍት ጨዋታን እንድንጠብቅ ቢያደርገንም ክለቦቹ ካሉበት ጫና አንፃር ቀድሞ ግብ የሚያስቆጥረው ቡድን ለአሸናፊነት የተሻለ ዕድል እንደሚያገኝ ይታሰባል። ከተከላካይ መስመር ፊት ቡድኑ በዋነኝነት የሚተማመንባቸው ብሩክ ቃልቦሬ እና ተስፋዬ አለባቸው አለመኖር ወልድያ መሀል ላይ የፍፁም ተፈሪን እንቅስቃሴ ለመግታት እንዲቸገር ሊያደርገው የሚችል ሲሆን የፈጣኑ የመስመር አጥቂ አብድለጢፍ መሀመድ የግራ መስመር ጥቃትም እንዲሁ ለእንግዶቹ ስጋት ይሆናል። ሆኖም በርካታ የማጥቃት ባህሪ ያላቸው አማካዮች እና አጥቂዎች ባለቤት የሆነው ወልድያ በማጥቃት ሂደቱ በመረጠው ቅርፅ የተጋጣሚውን ደካማ ጎን ለመፈተሽ ላይቸገር ይችላል።

አርባምንጭ ከተማ ከ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲ

አርባምንጭ እና ወልዋሎ በአምስተኛው ሳምንት ድል ከቀናቸው የሊጉ አራት ክለቦች መሀከል የሚጠቀሱ ናቸው። በውጤቱም ወልዋሎ ሊጉን በ9 ነጥቦች መምራት ሲችል አርባምንጭ የአመቱን የመጀመሪያ ሶስት ነጥቦች ሰብስቦ ከነበረበት የመጨረሻ ደረጃ ወደ 10ኛ ከፍ ማለት ችሏል። የነገው ጨዋታም ሁለት ከማሸነፍ የተመለሱ ቡድኖች የሚገናኙበት እንደመሆኑ መጠን ተከታታይ ድልን ለማስመዝገብ ብርቱ ፉክክር የሚደረግበት እንደሚሆን የሚጠበቅ ሲሆን ኢ/ዳኛ ለሚ ንጉሴም ጨዋታውን ለመምራት ተመድበዋል።

ለረጅም ጊዜ ጉዳት ላይ የነበረው አማኑኤል ጎበና ቀለል ያለ ልምምድ መስራት ቢጀምርም ለጨዋታው የማይደርስ ሲሆን ለብሔራዊ ቡድን የተጠሩት ተመስገና ካስትሮ እና እንዳለ ከበደ ጨምሮ ጉዳት ላይ ያለው ወንደሰን ሚልኪያስ እና ቅጣት ላይ የሚገኘው አንድነት አዳነ ወልዋሎን ከሚገጥመው የአርባምንጭ ቡድን ውጪ ሆነዋል። በወልዋሎ ዓ.ዩ በኩል የጉዳት ዜና ባይሰማም ከብሔራዊ ቡድኑ ጋር ኬንያ የሚገኘው በረከት አማረ ጨዋታው ያልፈዋል።

እስካሁን ባለው ሂደት ወልዋሎዎች ከሜዳቸው ውጪ በሚያደርጓቸው ጨዋታዎች ላይ ያላቸው የማጥቃት አቀራረብ በዚህ ጨዋታም ላይ እንደሚታይ ይጠበቃል። ይህም ጥሩ የአማካይ ስብስብ ላለው የአርባ ምንጭ ቡድን ክፍተቶችን እንዲያገኝ በር የሚከፍት በመሆኑ ጨዋታው ሳቢ እንቅስቃሴ ሊታይበት እንደሚችል የሚጠቁም ነው። የምንተስኖት አበራ እና ታዲዮስ ወልዴ ጥምረት ከዋለልኝ ገብሬ እና አፍወርቅ ሀይሉ የሚገናኙበት የአማካይ ክፍል በጨዋታ ትኩረት እንደሚስብ የሚጠበቅ ሲሆን በወንድሜነህ ዘሪሁንን የሚመራው የአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪ/ማርያም የማጥቃት ሀላፊነት ያላቸው አማካዮች ስብስብም የወልዋሎ የመስመር ተከላካዮች ሮቤል ግርማ እና እንየው ካሳሁን የማጥቃት ተሳትፎን ተከትሎ የሚገኙ ክፍተቶችን እንዴት ሊጠቀሙበት ይችላሉ የሚለው ጥያቄ መልስ የሚያገኝበት ጨዋታ ይሆናል። ከዚህ ውጪ ለወልዋሎ በሊጉ አናት መቀመጥ ትልቁን ድርሻ የተወጡት ፕሪንስ ሰቨሪንሆ እና ከድር ሳሊህ በሁለት ተከላካይ አማካዮች ሽፋን ቢሰጠውም ክፍተቶችን ሲፈጥር ከሚታየው የአርባምንጭ የመስመር ተከላካይ ክፍል ጋር የሚያደርጉት ፍልሚያ እጅግ ወሳኝነት ይኖረዋል።

ፋሲል ከተማ ከ ወላይታ ድቻ

የፋሲል ከተማ የዘንድሮው አጀማመር ከአምናው ጋር ሲነፃፀር ደብዘዝ ያለ ይመስላል። ጅማ አባጅፋርን ከሜዳው ውጪ አሸንፎ የነበረው ፋሲል የመጨረሻዎቹን ሁለት ተከታታይ  ግብ ሳያስቆጥር ቢጨርስም ሁለት ነጥቦችን ግን ማሳካት አልተሳነውም። በዚህም አንድ ቀሪ ጨዋታ እያለው 6ኛ ደረጃ ላይ መርጋት ችሏል። እንዳጀማመሩ መዝለቅ ያልቻለው ወላይታ ድቻ ደግሞ 12ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠ ሲሆን ሳምንት ከድሬደዋ ከተማ ጋር ነጥብ የተጋራበት ጨዋታ ከደረሰበት ሁለት ተከታታይ ሽንፈቶች በኃላ በመጠኑ ያገገመበት ሆኖ አልፏል። ቡድኖቹ ነገ ጎንደር ላይ በ6ኛ ሳምንት ጨዋታ ሲገናኙ ኢ/ዳኛ ኢብራሂም አጋዥ በመሀል ዳኝነት ተመድበዋል።

አምሳሉ ጥላሁንን እና አብዱርሀማን ሙባረክን በብሔራዊ ቡድን ጥሪ ምክንያት ማይጠቀመው ፋሲል ከተማ ዳዊት እስጢፋኖስ ከጉዳት ሲመበስለት በአንፃሩ በልምምድ ላይ ጉዳት ያጋጠመውን ይስሀቅ መኩሪያን የማይጠቀም ይሆናል። ፀጋዬ አበራ ለሴካፋ ያስመረጠው ወላይታ ድቻ አሁንም ከጉዳቱ ያላገገመውን በዛብህ መለዮን መጠቀም ባይችልም አምበሉን ተክሉ ታፈሰን ከጉዳት እንዲሁም ኃይማኖት ወርቁን ከቅጣት መልስ ማግኘቱ ለክለቡ መልካም ዜና ሆኗል።

ጨዋታው በፈጣን የማጥቃት ሽግግር የሜዳውን ስፋት በአግባቡ ለመጠቀም በሚሞክሩ የመስመር አጥቂዎች የተዋቀረውን ፋሲል ከተማን የመስመር ተመላላሾችን ከሚጠቀመው ብቸኛው የሊጉ ቡድን ወላይታ ድቻ የሚያገናኘው ይህ ጨዋታ የክንፍ እንቅስቃሴዎች ትኩረት የሚስቡበት እንደሚሆን ይገመታል። በተጋጣሚ ሜዳ ላይ በቶሎ ሲደርሱ የሚታዩት ፋሲሎች ክፍተት በመፍጠሩ በኩል ስኬታማ ናቸው ሊ ባል ቢችልም የመጨረሻ ውሳኔዎቻቸው ደካማ መሆን ምናአልባትም በሁለት ተከታታይ ጨዋታዎች ግብ ላለማስቆጠራቸው እንደ ምክንያትነት ይጠቀሳል። ወላይታ ድቻም በተመሳሳይ በማጥቃቱ በኩል ሙሉ ለሙሉ በጃኮ አራፋት ላይ የተመሰረተ መሆኑ በቀላሉ ዕድሎችን ለመፍጠር ከሚቸገሩ ቡድኖች መሀል አንዱ አድርጎታል። በነገው ጨዋታ ከሚጠበቁት ሁነቶች ውስጥም ጃኮ አራፋት በፋሲል ከተማ የተከላካይ መስመር ፊት በሚኖረው እንቅስቃሴ ወላይታ ድቻዎች በምን መንገድ ተጠቃሚ ሊሆኑ ይችላሉ የሚለው አንዱ ነው። በዋነኝነት ትኩረት የሚስበው ግን ፋሲሎች በሁለቱ መስመሮች የሚሰነዝሩት ጥቃት የድቻን ተመላላሾች አማካይ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴ ወደየትኛው የሜዳ ክፍል ላይ ያደላ እንዲሆን ያደርገዋል የሚለው ነው። በዚህም ራምኬል ሎክ እና ኤርሚያስ ኃይሉ ከእሸቱ መና እና ያሬድ ዳዊት የሚገናኙባቸው የጨዋታው ሂደቶች ወሳኝነት ይኖራቸዋል። በጥቅሉ ጨዋታው ጥሩ ፉክክር ሊስተናገድበት እንደሚችል የሚታሰብ ሲሆን አምና የሁለተኛ ሳምንት ጨዋታቸው ለወራት ከተራዘመ በኃላ ጎንደር ላይ በተገናኙ ጊዜ ፋሲል ከተማ 2-0 ማሸነፉ የሚታወስ ነው።

መቐለ ከተማ ከ ደደቢት

በኢ/ዳኛ በላይ ታደሰ የመሀል ዳኝነት መቐለ ከተማ በሜዳው በሚያስተናግደው ሶስተኛ ጨዋታው ከደደቢት ብርቱ ፉክክር እንደሚገጥመው ይጠበቃል። ሳምንት በተፈጠረው ግጭት ከወልድያ ጋር የነበረው ጨዋታ ከመሰረዙ በፊት በሜዳው ጅማ አባጅፋርን ያሸነፈው መቐለ 7ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። እንደተጋጣሚው ሁሉ አንድ ጨዋታ ብቻ ያሸነፈው ደደቢት በበኩሉ ከአራት ያለግብ ከተጠናቀቁ ጨዋታዎች ጋር ሰባት ነጥቦችን ይዞ 5ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጧል። 

አማኑኤል ገ/ሚካኤልን ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጡት መቐለዎች በቡድናቸው ውስጥ የተሰማ የጉዳት ዜና የሌለ ሲሆን በደደቢቶች በኩል የብርሀኑ ቦጋለ ማገገም አጠራጣሪ ከመሆኑ ውጪ በነገው ስብስብ ውስጥ ማይካተቱት ተጨዋቾች ወደ ሴካፋ ያቀኑት ታሪክ ጌትነት እና አቤል ያለው ብቻ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

ደደቢት ግብ በማስቆጠሩ በኩል በጣሙን ተቸግሯል። የቡድኑ እንቅስቃሴ በዋነኝነት የተመሰረተበት ጌታነህ ከበደም አምና በዚህ ጊዜ አምስት ግቦችን ማስቆጠሩን ላስታወሰ ዘንድሮ አንድ ግብ ላይ መቆሙ ሊያስገርመው ይችላል። ኳስ ይዞ ለመጫወት የሚሞክረው የአሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ ቡድን በግብ ፊት አስፈሪነቱ እየቀነሰ ነው። አኩዌር ቻሞን ከጌታነህ ጋር አጣምሮ በጀመረበት የፋሲሉ ጨዋታም ችግሩ እንዳልተቀረፈ ታይቷል። ሆኖም ከቅያሪዎች በኃላ አምስት አማካዮችን ሲጠቀም የታየው ደደቢት ቢያንስ ከመጀመሪያው በተሻለ ጫና ለመፍጠር ሞክሮ ነበር። ተጋጣሚው መቋለ በሜዳው እስካሁን ግብ አለማስተናገዱ ሲታሰብ ደግሞ የደደቢት ይህ ችግሩ በነገውም ጨዋታ ሊንፀባረቅ እንደሚችል ፍንጭ ይሰጣል። ሆኖም መቐለዎችም ተመሳሳይ ነጥብ ይነሳባቸዋል። እካሁን ቡድኑ በጨዋታ ያስቆጠረው ግብ በጅማ አባጅፋሩ ጨዋታ በያሬድ ከበደ አማካይነት የተገኘው ግብ ብቻ ነው። ከኃላ በቀላሉ የማይታለፉት መቐለዎች የመጀመሪያ አሰላለፋቸው አለመለዋወጥ ለቡድን ውህደታቸው ጥንካሬ እየሰጠ ይገኛል። በተለይም የተከላካይ መስመሩ እና የተከላካይ አማካዮቹ ዐመለ ሚልኪያስ እና ሚካኤል ደስታ ጥምረት ለቡድኑ የስካሁን መልካም የሚባል ጉዞ ድርሻው ከፍ ያለ ነበር። በነገው ጨዋታም ከፋሲካ አስፋው እንዲሁም ከመስመሮች ከሽመክት ጉግሳ እና ኤፍሬም አሻሞ ወደ ጌታነህ ከበደ የሚላኩ ኳሶችን በማቋረጡ ሀላፊነት የሚጠመዱ ይሆናል። በከድር ኩሊባሊ የሚመራው የደደቢት የተከላካይ መስመርም በዋነኝነት ከፊት አጥቂው አቼምፖንግ አሞስ እና ከአጥቂ አማካዩ ያሬድ ከበደ እንቅስቃሴ ጋር የሚጋፈጥ ይሆናል።

ድሬደዋ ከተማ ከ አዳማ ከተማ

10፡00 ሰዐት ላይ በድሬደዋ የሚደረገው ጨዋታ ጎል በማስቆጠሩ በኩል የሚታሙትን ሁለት ክለቦች የሚያገናኝ ሲሆን በኢ/ዳ አማኑኤል ኃ/ሥላሴ እንደሚመራም ይጠበቃል ። 7ኛ ደረጃ ላይ የተቀመጠው ድሬደዋ ከተማ አመቱን በማሸነፍ ቢጀምርም በቀጣይ ያደረጋቸውን ሶስት ጨዋታዎች በአቻ ውጤት ሲያጠናቅቅ በሁለቱ ያለግብ ነበር የተለያየው። አዳማ ከተማ ሳምንት ሀዋሳን አስተናግዶ ማሸነፉ ነጥቡን ወደ ስምንት በማሳደግ ደረጃውን ከዘጠኝ ወደ ሁለት ማያሳደግ እንሲችል ቢያደርገውም ከዛ በፊት ሁለት ጨዋታዎችን ያለግብ ማጠናቀቁ አሁንም ጥያቄ እንዲነሳበት ምክንያት ሆኗል።

ወሰኑ ማዜን ፣ ያሬድ ታደሰን እና ሀብታሙ ወልዴን ከጉዳት መልስ የሚያገኘው ድሬደዋ የሚያጣው ተጨዋች እንደማይኖር ሰምተናል። በአንፃሩ ከንአን ማርክነህን እና ዳዋ ሁቴሳን ለብሔራዊ ቡድን ያስመረጠው አዳማ ከተማ አሁንም ታፈሰ ተስፋዬን እና በሀዋሳው ጨዋታ ከጉዳት መልስ ለ14 ደቂቃዎች ብቻ በሜዳ ላይ ቆይቶ የወጣው ቡልቻ ሹራን በጉዳት የማይጠቀም ይሆናል።

አምና በሁለተኛው ዙር የመጀመሪያ ጨዋታ ድሬደዋ ላይ ተገናኝተው 1-1 የተለያዩት ሁለቱ ክለቦች በነገው ጨዋታቸውም ጨዋታቸው በአቻ ውጤት ሊጠናቀቅ እንደሚችል ብዙዎች ይገምታሉ። አጥቂ መስመር ላይ ጥቂት  አማራጮችን የያዘው አደማ በድሬደዋ ከተማ ላይ ሊፈጥራቸው የሚችሉ ዕድሎችን ወደግብ በመቀየሩ በኩል ሊቸገር እንደሚችል ቢታሰብም ተጋጣሚው ድሬደዋ በቀላሉ ክፍተት የማይሰጥ ቡድን መሆኑ ደግሞ አዳማ ዕድሎችን የማግኘቱንም ነገር አጠራጣሪ ያየርገዋል። በሀዋሳው ጨዋታ ላይ አዳማዎች ጥሩ የሚባሉ አጋጣሚዎችን ሲፈጥሩ ብንመለከትም የሀዋሳን የተከላካይ መስመር ለድሬው ጨዋታ እንደማሳያ መውሰድ የሚከብድ ነው የሚሆነው። አማካይ መስመር ላይ የሚገኙት አብዛኞቹ የድሬደዋ ተሰላፊዎች ያላቸው የመከላከል ባህሪ ከኃላ መስመሩ ጥንካሬ እና ከቡድኑ አቀራረብ ጋር ተዳምሮ ቡድኑ ለአዳማ በቀላሉ ክፍተት እንደማይሰጥ የሚያሳዩ ነጥቦች ናቸው። በተቃራኑውም ስንመለከት ድሬደዋዎች ከመልሶ ማጥቃት የሚገኙ ዕድሎችን ለመጠቀምም ሆነ ከቆሙ ኳሶች ግቦችን ለማግኘት በተለይ በአካል ብቃቱ ረገድ ከማይታማው የአዳማዎች የተከላካይ መስመር ጋር መጋፈጥ ይጠበቅባቸዋል። በዚህም ምክንያት ጨዋታው በጥንቃቄ የተሞላ እና የሁለቱም ቡድኖች የኃላ መስመሮች ተፅዕኖ ጎልቶ የሚወጣበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *