​ሴካፋ 2017፡ ቡሩንዲ እና ኬንያ ወደ ግማሽ ፍፃሜ አልፈዋል

በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የምድብ የመጨረሻ ጨዋታዎች ዛሬ ሲካሄዱ ቡሩንዲ እና ኬንያ ማለፋቸውን ያረጋገጡ የመጨረሻዎቹ ሃገራት ሆነዋል፡፡ አስተናጋጇ ኬንያ ታንዛኒያን 1-0 ስትረታ ቡሩንዲ ከደቡብ ሱዳን ጋር ያለግብ አቻ በመለያየት ነው ወደ ግማሽ ፍፃሜ ማምራታቸውን ያረጋገጡት፡፡ የዛሬውን ውጤት ተከትሎም ኢትዮጵያ ከምድብ ሁለት መውደቋን አረጋግጣለች፡፡ ሊቢያ ዛንዚባርን 1-0 ብታሸንፍም ከምድብ ከመሰናበት አልዳነችም፡፡

ማቻኮስ ላይ በተደረገ ጨዋታ ኬንያ ታንዛኒያን በቪንሰንት ኦቡሩ ግብ 1-0 በማሸነፍ የምድብ አንድን በመሪነት ጨርሳለች፡፡ ሊቢያ በበኩሏ በአልሃሪሳ ዛካሪያ ግብ ታግዞ አስቀድሞ ወደ ግማሽ ፍጻሜ ያመራችውን ዛንዚባርን 1-0 ማሸነፍ ብትችልም የአዘጋጇ ሙሉ ሶስት ነጥብ ማሳካት ተከትሎ ከውድድር ተሰናብታለች፡፡

በምድብ ሁለት ካካሜጋ ላይ ደቡብ ሱዳን እና ቡሩንዲ ያለግብ አቻ ተለያይተዋል፡፡ ደቡብ ሱዳን በሁለት ጨዋታ 8 ግብ ማስተናገዷን ተከትሎ በቡሩንዲም የግብ ናዳ ይወርድባታል የሚል ግምት አስቀድሞ ቢኖርም ዛሬ በተደረገው ጨዋታ ግን በተቃራኒው መረቧን ሳታስደፍር ወጥታለች፡፡ ይህንን ተከትሎም በጨዋታ ውጤት ላይ ተንጠልጥሎ የነበረው የዋሊያዎቹ የማለፍ ተስፋ ጨልሟል፡፡ ቡሩንዲ ዩጋንዳን ተከትሎ ከምድቡ በአምስት ነጥብ ማለፏን አረጋግጣለች፡፡

ኬንያ እና ቡሩንዲ እንዲሁም ዩጋንዳ እና ዛንዚባር በፍፃሜ ግማሹ የሚገናኙ ይሆናል፡፡ የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታዎ በኪሱሙ በሚገኘው ሞይ ስታዲየም ሲካሄዱ የፍፃሜው ጨዋታ በማቻኮስ በሚገኘው ኬንያታ ስታዲየም ይደረጋል፡፡

ሐሙስ

9፡00 – ኬንያ ከ ቡሩንዲ

አርብ

9፡00 – ዩጋንዳ ከ ዛንዚባር

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *