​ሴካፋ 2017፡ ኬንያ ለፍፃሜ አልፋለች

በሴካፋ ሲኒየር ቻሌንጅ ዋንጫ የግማሽ ፍፃሜ የመጀመሪያ ጨዋታ ኪሲሙ ላይ ተደርጎ ኬንያ ቡሩንዲን 1-0 በማሸነፍ ለፍፃሜ ደርሳለች፡፡ የሃራምቤ ከዋክብቶቹ በመጀመሪያው 45 በፈጣን እንቅስቃሴ ወደ ግብ በሚደርሱት ቡሩንዲዎች ቢፈተኑም በተጨማሪ 30 ደቂቃ በተቆጠረ ግብ አሸናፊ መሆን ችለዋል፡፡

በሞዬ ስታዲየም በተደረገው ጨዋታ ኬን በመከላከሉ ጥሩ ብትሆንም በእንቅስቃሴ ደረጃ ገና እንደሆነች የታየበት ጨዋታ ነበር፡፡ በምድብ ጨዋታዎች ጠንካራ የነበረችው ቡሩንዲ በግማሽ ፍፃሜውም በተለይም በመጀመሪያው 45 አዘጋጇን መፈተን ችላለች፡፡ የኬንያው ግብ ጠባቂ ፓትሪክ ማታሲ የቡሪንዲው የአጥቂ አማካይ ሻሲር ናሂማና የሻገረውን የማዕዘን ምት በ10ኛው ደቂቃ ወደ ውጪ ሲያወጣ ከአራት ደቂቃዎች በኃላ ሙሳ መሃመድ የሻባን ሁሴንን የግንባር ኳስ ከመስመር ላይ ግብ ከመሆን ታድጓል፡፡ ቡሩንዲዎች በፈጠን እንቅስቃሴ አጋማሹን ከተጋጣሚያቸው ተሽለው ታይተዋል፡፡ በተለይም የፊስቶን አብዱልራዛክ ወደ ቡድኑ መመለስ ለቡሩንዲ አስፈሪነት የበኩሉን አስተዋፅኦ አድርጓል።

በሁለተኛው አጋማሽም የቡሩንዲ የበላይነት የታየ ሲሆን ግብ ለማስቆጠር ግን ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ ቡድቹ ጨዋታቸው ያለግብ አቻ ከተለያዩ በኃላ በጭማሪው 30 ደቂቃ የመጀመሪው አጋማሽ ተቀይሮ የገባው ሳሙኤል ኦኒያንጎ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ዋይቮን ኢሱዛ ከመረብ አዋህዶ ሃገሩን ለፍፃሜ አብቅቷል፡፡ ከሁለት አመት በፊት በሩብ ፍፃሜው የተሰናበተችው ኬንያ ከ2013 በኃላ ለመጀመሪያ ግዜ ለፍፃሜ ደርሳለች፡፡ 

የኬንያ ተጋጣሚ ለመሆን አርብ ዩጋንዳ እና ዛንዚባር ኪሲሙ ላይ በሌላኛው የግማሽ ፍፃሜ ጨዋታ ይገናኛሉ፡፡

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *