__________________________________________________
(ይህ ዜና የተላከው ከኢትዮጵያ እግርኳስ ፌዴሬሽን ህዝብ ግንኙነት ነው፡፡)
_________________________________________________
ከመላ ኢትዮጵያ የተውጣጡ ትምህርት ቤቶች ተካፋይ የሚሆኑበትና እድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች የሆናቸው ህፃናት የሚሳተፉበት ኮፓ ኮካ ኮላ ሀገር አቀፍ የህፃናት እግር ኳስ ውደድር እሁድ ከሐምሌ 15 ቀን 2ዐዐ7 ጀምሮ በክልል መሰተዳድሮች በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡
የኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን እና የፌዴራል ስፖርት ኮሚሽን ከኮካ ኮላ ኢንተርናሽናል ኩባንያ/ COCA-COLA CENTRAL EAST AND WEST AFRICA LIMITED/ጋር በመተባበር ያዘጋጁትና በአይነቱ የመጀመሪያ በሆነው ሀገር አቀፍ ውድድር ላይ ዘጠኙ ክልላዊ መስተዳድሮች እንዲሁም የሁለት ከተማ አስተዳደሮች ምርጥ የህፃናት ቡድኖች በሁለቱም ፆታ ተወዳዳሪ ይሆናሉ፡፡
ተተኪና ሀገር የሚያስጠሩ ምርጥ ተጫዋቾችን ለማፍራት የታመነበት ይህ ውድድር በአፋር እና በቤኒሻንጉል ክልላዊ መስተዳድሮች በላፉት ሁለት ሳምንታት የተካሄደ ሲሆን፣ በተከታታይ እስከ ነሃሴ የመጀመሪያ ሳምንት ድረስ ሁሉም ተወዳዳሪ ክልሎችና የከተማ መስተዳድሮች የውስጥ ውድድራቸውን ያጠናቅቃሉ፡፡የአማራ ክልላዊ መስተዳድር የውስጥ ውድድሩን ሃምሌ 21/2007 በይፋ የጀመረ መሆኑን ከክልሉ እግር ኳስ ፌዴሬሽን የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡ በተጨማሪም የትግራይ የሶማሌና የድሬዳዋ ውድድሮች ከሃምሌ 26-30/2007 ዓ.ም ባሉት ቀናት ወስጥ እንደሚጀመሩ ከወጣው የውድድር ፕሮግራም ለመገንዘብ ተችሏል፡፡ከዚያም ከነሐሴ 16 እስከ 3ዐ/2ዐዐ7 ዓ.ም በክልሎች ምርጥ ቡድኖች መካከል የመጨረሻው ውድድር በአዳማ ከተማ በደማቅ ስነስርዓትና ልዩ ዝግጅት ታጅቦ እንደሚካሄድ ይጠበቃል፡፡
በውድድሩ በክልል መስተዳድርና በከተማ አስተዳደር ደረጃ 64 የወጣት ወንዶችና 54 የልጃገረድ ቡድኖች በጠቅላላው 114 ቡድኖች የሚሳተፉ ሲሆን አማራ፣ ደቡብ፣ አዲስ አበባ እና ኦሮሚያ 16 ቡድኖች በማሳተፍ ቀዳሚነቱን ይዘዋል፡፡በተጨማሪም በአፋር 6፣ በትግራይ 1ዐ፣ በቤኒሻንጉል 8፣ በድሬዳዋ 8፣ በሐረር 8፣ በሶማሌ ደግሞ 6 ቡድኖች እንደሚወዳደሩ ለማወቅ ተችሏል፡፡
ውድድሩን በተሳካ ሁኔታ ለማካሄድ በኮፓ ኮካ ካላ ኢንተርናሽናል ኩባንያና በኢትዮጵያ እግር ኳስ ፌዴሬሽን መካከል ሁሉን አቀፍ ስምምነት ከሁለት ወራት በፊት የተፈረመ ሲሆን የውድድሩን አጠቃላይ ወጪ ኩባንያው ይሸፍናል፡፡ በስምምነቱ መሠረት ኮካኮላ ለአጠቃላይ ውድድሩ ወደ200 ሺህ ዶላር የሚጠጋ በጀት የመደበ ሲሆን ክፍያው በቅርቡ ተፈጻሚ እንደሚሆን ለማወቅ ተችሏል፡፡የትጥቅና ሌሎች ለውድድሩ የሚያስፈልጉ መገልገያዎችን ኩባንያው እንደሚያሟላም ታውቋል፡፡
ውድድሩ ሲጠናቀቅ በፌዴሬሽኑ በተዘጋጀውና ክህሎትን መሠረት ባደረገው የመመልመያ መስፈርት መሠረት እስከ 100 የሚደርሱ ህፃናት በእግር ኳስ አካዳሚዎች የመሰልጠን እድል እንደሚያገኙ ተስፋ ተደርጓል፡፡ ለህፃናቱ በሚደረገው ተከታታይ ድጋፍና ክትትልም ወደፊት ለታዳጊና ወጣት ቡድኖች ልዩ ችሎታና ብቃት ያላቸውን ተተኪዎች ማፍራት እንደሚቻል ይታመናል፡፡