ሪፖርት| ​ጅማ አባ ጅፋር የአመቱን ሁለተኛ ድል አስመዘገበ

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ሰባተኛ ሳምንት የመጨረሻ ጨዋታ ጅማ ላይ ኢትዮጵያ ቡናን ያስተናገደው ጅማ አባ ጅፋር  2-0 በማሸነፍ ከአምስት ሳምንታት በኃላ ግብ ወደማስቆጠር እና ሶስት ነጥቦችን ወደ ማሳካት ተመልሷል።

ቀኑ የስራ ቀን በመሆኑ ይመስላል ከተጠበቀው በታች ተመልካች ተገኝቶበት ቀስ በቀስ ድባቡ እያማረ በሄደው የዛሬው የጅማ ጨዋታ ላይ ሁለቱም ቡድኖች መጠነኛ ለውጦችን አድርገው ወደ ሜዳ ገብተዋል። ከረጅም ጊዜ ጉዳት በኃላ ሳምንት ተሰልፎ ያየነውን አስቻለው ግርማን ያልያዘው ኢትዮጵያ ቡና ከሴካፋ ለተመለሰው ሳምሶን ጥላሁን የመጀመሪያ አሰላለፍ ዕድል ሲሰጥ እንደ ሸገር ደርቢው ሁሉ በ4-2-3-1 አሰላለፍ ጨዋታውን ጀምሯል። የአሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌው ጅማ አባ ጅፋርም ከኢትዮ ኤሌክትሪክ ያለ ግብ ከተለያየበት ጨዋታ ጋር ሲነፃፀር ከሴካፋ የተመለሰውን ሔኖክ አዱኛን በእንዳለ ደባልቄ ምትክ በመጀመሪያ አሰላለፍ ውስጥ ያካተተ ሲሆን ከወትሮው በተለየ የ4-4-2ን አሰላለፍ ተጠቅሟል። በዚህም ተመስገን ገ/ኪዳን እና ኦኪኪ አፎላቢ ፊት ላይ ሲጣመሩ ባልተለመደ መልኩ ሔኖክ ኢሳያስ እና ዮናስ ገረመው በመስመር አማካይነት ሚና ታይተዋል። 

የጨዋታው የመጀመሪያ አጋማሽ በሙሉ ጨዋታው ላይ ከታዩት ወሳኝ የሜዳ ላይ እንቅስቃሴዎች አመዛኙን የተመለከትንበት ነበር። በመጀመሪያዎቹ ደቂቃዎች ላይ የኳስ ቁጥጥራቸውን ወደ ሁለተኛው የሜዳ ክፍል እንኳን ማድረስ የተሳናቸው ኢትዮጵያ ቡናዎች ኳስ በሚነጠቁባቸው አጋጣሚዎች ደግሞ ይበልጥ ሲጋለጡ ታይተዋል። ከቅዱስ ጊዮርጊሱ ጨዋታ በተሻለ ወደፊት ገፍቶ ሲጫወት የነበረው ኤልያስ ማሞም ሆነ ሳምሶን ጥላሁን ፣ እያሱ ታምሩ እና አስራት ቱንጆ በአሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው የተዋቀረውን የጅማ አባ ጅፋር የአማካይ መስመር ማለፍ ተስኗቸዋል። 11ኛው ደቂቃ ላይ አክሊሉ ዋለልኝ ከርቀት ከሞከራት ኳስ ውጪም ቡናማዎቹ በመጀመሪያዎቹ 25 ደቂቃዎች እንቅስቃሲያቸው ያስገኘላቸው ሌላ የግብ ዕድል አልነበረም። በአንፃሩ 3ኛው ደቂቃ ላይ በኦኪኪ አፎላቢ አማካይነት የመጀመሪያ ሙከራ ያደረጉት ጅማ አባ ጅፋሮች እጅግ ፈጣን በሆነ የማጥቃት ሽግግር በተደጋጋሚ የቡና የሜዳ አጋማሽ ላይ በመገኘት አስፈሪ የማጥቃት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ ተስተውሏል። በዚህ መነሻነትም በርካታ የቆሙ ኳሶችን ሲያገኙ ቆይተው 24ኛው ደቂቃ ላይ ከማዕዘን የተነሳን ኳስ የቡና ተከላካዮች ከጨረፉት በኃላ ኦኪኪ ከቅርብ ርቀት አስቆጥሮ ቀዳሚ አድርጓቸዋል። ከግቡ መቆጠር በኃላ ጅማዎች ቀድሞ የነበራቸው ፍጥነት ጋብ ሲል በተቃራኒው ኢትዮጵያ ቡናዎች ከመጀመሪያው በተሻለ የኳስ ቁጥጥራቸው እስከ ተጋጣሚያቸው የግብ ክልል ድረስ ሲዘልቅ ይታይ ነበር። ምንም እንኳን ከሳጥኑ ጠርዝ ላይ ቢሆንም የ28ኛ እና 41ኛ የሳምሶን ጥላሁን ሙከራዎች የዚሁ የቡናዎች እንቅስቃሴ ውጤት ነበሩ። ሆኖም ግብ ማስቆጠር የቻሉት አልፎ አልፎ በተለይም ከሔኖክ ኢሳያስ እና ዮናስ ገረመው ወደ ኦኪኪ በሚላኩ ኳሶች ጥቃት ሲፈፅሙ የቆዩት አባ ጅፋሮች ነበሩ። 44ኛው ደቂቃ ላይ በግራ መስመር በከፈቱት የመልሶ ማጥቃት ከሔኖክ ኢሳያስ የደረሰውን ኳስ ተመስገን ገ/ሚካኤል ሁለት የቡና ተከላካዮችን እና ሀሪሰን ሄሱን በማለፍ በተረጋጋ መንገድ ሁለተኛ ግብ አስቆጥሮ ቡድኖቹ ወደ መልበሻ ክፍል አምርተዋል። 

የጨዋታ እንቅስቃሴው ይሄን ይመስል የነበረው የመጀመሪያ አጋማሽ በርካታ የሜዳ ላይ ግጭቶችንም ሲያስተናግድ ነበር። በዚህ ምክንያትም የአባ ጅፋሮቹ አሚኑ ነስሩ እና ይሁን እንዳሻው እንዲሁም የኢትዮጵያ ቡናው ቶማስ ስምረቱ የማስጠንቀቂያ ካርድ ተመልክተዋል። ቶማስ በዚሁ አጋማሽ ባስተናገደው ጉዳት በወንድይፍራው ጌታሁን ተቀይሮ ወጥቷል።

ሁለተኛው አጋማሽ ከመጀመሪያው ጋር ሲነፃፀር ቀዝቀዝ ያለ ነበር። ሁለት ግቦችን ያስቆጠሩት ጅማ አባ ጅፋሮች በመጠኑ ጥንቃቄን መርጠው የታዩ ቢሆንም ባገኙት አጋጣሚ ግን ተጋጣሚያቸውን ማስጨነቃቸው አልቀረም። በኦኪኪ አፎላቢ እና ተቀይሮ በገባው ሳምሶን ቆልቻ አማካይነት ያደረጓቸው ሙከራዎችም ለዚህ ተጠቃሽ ነበሩ። አሚኑ ነስሩን በእረፍት ቀይረው ያስወጡት ጅማዎች ይሁን እንዳሻውንም በጉዳት ለመቀየር መገደዳቸው ደቂቃዎች በገፉ ቁጥር ለጥቃት እንዲጋለጡ በር ቢከፍትም የዳዊት አሰፋ መረብ ሳይደፈር ነበር ጨዋታው የተጠናቀቀው። ሌላኛውን የመሀል ተከላካያቸውን አክሊሉ አያናውን እና የፊት አጥቂውን ሳሙኤል ሳኑሚን በጉዳት ለመቀየር የተገደዱት ኢትዮጵያ ቡናዎች በተቻላቸው መጠን ገፍተው ቢጫወቱም ወደ ጅማዎች የመከላከል ወረዳ ለመግባት የቻሉት በጥቂት አጋጣሚዎች ብቻ ነበር። 51ኛው ደቂቃ ላይ ሳሙኤል ሳኑሚ ከአለማየው ሙለታ የተሻማለትን ኳስ በግንባር እና 56ኛው ደቂቃ ላይ ኤልያስ ማሞ ከቅጣት ምት በቀጥታ በመምታት ለማስቆጠር የሞከሩባቸው አጋጣሚዎች በእንግዶቹ የሁለተኛ አጋማሽ እንቅስቃሴ ውስጥ እንደ ሙከራ የሚነሱ ናቸው። መደበኛው ደቂቃ ተጠናቆ የተጨመሩት ሰባት ደቂቃዎች ላይ ግን ሁለቱም ቡድኖች በእጅጉ ለጎል ቀርበው ታይተዋል ሆኖም በጅማ በኩል ኦኪኪ አፎላቢ እንዲሁም በኢትዮጽያ ቡና በኩል አስራት ተንጆ በቅርብ ርቀት የሞከሯቸው ኳሶች በተመሳሳይ በግቡ አግዳሚ ተመልሰዋል። ጨዋታውም በመጀመሪያው አጋማሽ ውጤት በቀይ ለባሾቹ አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አባ ጅፋሮች በደረጃ ሰንጠረዡ ወደ ስምንተኛነት ከፍ ሲሉ በአዲሱ አሰልጣኝ ዲዲዬ ጎሜዝ የትሪቡን እይታ ስር ሽንፈት ያስተናገደው ኢትዮጵያ ቡና ወደ ሶስተኝነት ከፍ ሊል የሚችልበትን ዕድል ሳይጠቀምበት ወደ ዘጠነኛነት ለመንሸራተት ተገዷል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *