ሪፖርት| ደደቢት ሶስተኛ ተከታታይ ድሉን አስመዝግቧል

በኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 8ኛ ሳምንት የመጀመሪያ ቀን ውሎ አዲስ አበባ ስታዲየም ላይ በ11:30 ደደቢትንና ኢትዮ ኤሌክትሪክን ባገናኘው ጨዋታ ሰማያዊዎቹ በሁለተኛው አጋማሽ ባስቆጠሯቸው ሶስት ግቦች በመታገዝ ኢትዮ ኤሌክትሪክን 3ለ1 በሆነ ውጤት አሸንፈው ነጥባቸውን ወደ 16 በማሳደግ ሊጉን መምራታቸውን ቀጥለዋል፡፡ 

በዛሬው ጨዋታ ደደቢቶች በ4-3-3 አሰላለፍ ባሳለፍነው ሳምንት ሲዳማን 5-2 ካሸነፈው የቡድን ስብስብ ውስጥ አቤል እንዳለን በአለምአንተ ካሳ ከተኩበት ብቸኛ ቅያሬ በስተቀር ባሳለፍነው ሳምንት የተጠቀሙትን የቡድን ስብስብ መጠቀም ሲችሉ በአንፃሩ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች በ7ኛው ሳምንት ከወልዲያ ከተማ ጋር ሊያደርጉት የነበረው ጨዋታ ለሌላ ጊዜ መታላለፉን ተከትሎ ባሳለፍነው ሳምንት ጨዋታ አለማከናወናቸው የሚታወስ ነው። በዛሬው የቡድን ስብስባቸው ውስጥ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ኤሌክትሪክን የተቀላቀለው ቢኒያም አሰፋ በሊጉ ለክለቡ የመጀመሪያ ጨዋታውን ማድረግ ችሏል፡፡ 

በደደቢት በኩል ከተደረጉ ሁለት የግብ ማግባት አጋጣሚዎች በስተቀር ይህ ነው የሚባል የግብ ማግባት አጋጣሚዎች ያልታየበት በመጀመሪያው አጋማሽ የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ኢትዮ ኤሌክትሪክ በተጋጣሚው ላይ ፍፁም የሆነ የጨዋታ የበላይነት ማሳየት ችሏል፡፡ በተለይ በመጀመሪያዎቹ 15 ደቂቃዎች በበ4-1-3-2 ቅርፅ ጨዋታውን የጀመሩት ኤሌክትሪኮች በሜዳው ቁመት በሁሉም የሜዳ ክፍሎች ላይ እንደነበራቸው የተጫዋቾች የቁጥር ብልጫ በርካታ የተሳኩ የኳስ ቅብሎሎችን በተጋጣሚያቸው የሜዳ ክፍል ቢያደርጉም የጠሩ የግብ እድሎችን በመፍጠር በኩል ግን እጅግ ደካሞች ነበሩ፡፡ 

በነዚሁ የመጀመሪያ ደቂቃዎች እንደወትሮው ሁሉ ለዝርግ የኃላ አራት ተከላካይ የቀረበው የሚመስለው የደደቢት የተከላካይ መሰመር በተለይም የግራ መስመር ተከላካይ የነበረው ሰለሞን ሀብቴ በመሀል አማካዩ ወደ መሀል እጅግ ያጋደለ እንቅስቃሴ እንዲሁም ከመስመር አጥቂው አቤል ያለው በቂ የሆነ ሽፋን ማግኘት ባለመቻሉ በተደጋጋሚ ከኤሌክትሪኩ ፈጣን የመስመር ተከላካይ በሆነው አወት ገ/ሚካኤል ከፍተኛ ጫና ሲፈጥርበት ተስተውሏል፡፡ በአንጻሩ በደደቢት በኩል ከተከላካይ አማካዩ አስራት መገርሳ አጠገብ በግራና በቀኝ የተሰለፉት አለምአንተ ካሳና ያብስራ ተስፋዬ ወደ ተቃራኒ የሜዳ አጋማሽ በሚገቡበት ወቅት በኤሌክትሪክ የተከላካይ መስመርና በአማካይ ክፍሉ መካከል የሚገኙትን አደገኛ ቀጠና እንዳይጠቀሙ በማድረግና የደደቢት የፊት አጥቂዎች ከተቀረው የቡድኑ ተጫዋቾች እንዲነጠሉ ማድረግና የደደቢትን የመጥቃት እንቅስቃሴ በመግታት በኩል ጉልህ አስተዋፅኦን መወጣት ችሏል፡፡ ወደፊት ሲሄዱ እጅግ በጠበበ ቅርፅ ሲያጠቁ የነበሩት ደደቢቶች በ35ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ ያብስራ ተስፋዬ በረጅሙ ያቀበለውን ኳስ ተጠቅሞ ጌታነህ ከበደ ከኤሌክትሪክ የግብ ክልል ጨርቃው ላይ በግሩም ሁኔታ ወደ ግብ የላከውን ኳስ ሱሊይማን አቡ በአስደናቂ ሁኔታ ሊያድንበት ችሏል፡፡ 
በተመሳሳይ በቀደመው ሙከራ ከተገኘችው የማእዘን ምት ሰለሞን ሀብቴ ያሻማውን ኳስ አስራት መገርሳ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውን በድጋሚ ሱሌይማን አቡ አድኖበታል፡፡ ከነዚህ ሁለት ሙከራዎች በስተቀር ይህ ነው የሚባል የግብ ሙከራ ያልታየበት የመጀመሪያው አጋማሽ ያለግብ ተጠናቋል፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ ላይ የደደቢቱ አሰልጣኝ ንጉሴ ደስታ አለምአንተ ካሳን አስወጥተው በአቤል እንዳለ ሲተኩ በተመሳሳይ ሁለቱ የመስመር አጥቂዎች አቤል ያለውንና ሽመክት ጉግሳን ቦታ አቀያይረው ሁለተኛውን አጋማሽ መጀመር ችለዋል፡፡ 


በሁለተኛው አጋማሽ ጅማሮ በ46ኛው ደቂቃ ላይ በመልሶ ማጥቃት ያገኙትን አጋጣሚ ዲዲዬ ለብሪ ያሳለፈለትን ኳስ በኃይሉ ተሻገር በአየር ላይ በግሩም ሁኔታ ወደግብ የላካትና ክሌመንት ያዳናት ኳስ በኤሌክትሪክ በኩል የተደረገ የመጀመሪያው ኢላማውን የጠበቀ ሙከራ ነበር፡፡ 
በሁለተኛው አጋማሽ በተለይ የመጀመሪያዎቹ 20 ደቂቃዎች ከመጀመሪያው አጋማሽ በተሻለ ሁለቱ የደደቢት የመስመር አጥቂዎች ወደ መሀል በይበልጥ በመቅረብ ሚዛናዊ የሆነ እንቅስቃሴ በማድረግ በመጀመሪያው አጋማሽ ተወስዶባቸው የነበረው የበላይነት ማስመለስ ችለዋል፡፡ በ50ኛው ደቂቃ ላይ ደደቢቶች ከቀኝ መስመር ያሻሙትን ኳስ የኢትዮ ኤሌክትሪኩ ተከላካይ ግርማ በቀለ በአግባቡ ማራቅ ያልቻለውን ኳስ በቅርብ ርቀት የነበረውና ከሰሞኑ ምርጥ ብቃቱን እያሳየ የሚገኘው አቤል ያለው ወደ ግብ በመላክ ቡድኑን መሪ ያደረገችውን የመጀመሪያ ግብ ማስቆጠር ችሏል፡፡ 

ከግቧ መቆጠር በኃላ ጫና መፍጠራቸውን አጠናክረው የቀጠሉት ደደቢቶች በደቂቃዎች ልዩነት በ52ኛው ደቂቃ ላይ ያብስራ ተስፋዬ የሄኖክ ካሳሁንን ስህተት ተጠቅሞ ያገኛትንና በግሩም ሁኔታ ወደፊት ያሳለፈለትን ኳስ ጌታነህ ከበደ በግሩም አጨራረስ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ ያደረገችውን ግብ አስቆጥሯል። ወደ ቀኝ ባደላ መልኩ በተደጋጋሚ ወደ ግብ በፍጥነት መድረስ የቻሉት ደደቢቶች በተመሳሳይ በ58ኛው ደቂቃ ስዮም ተስፋዬ ወደ ግብ የላካት ኳስ ከሱሌይማና አቡ የተሳሳተ ቦታ አያያዝ ጋር ተዳማራ የግቡን አግዳሚ ለትማ ወደ ውጪ ወጥታለች። 

በ64ኛው ደቂቃ ላይ ኢትዮ ኤሌክትሪኮች ተከላካዩ ተስፋዬ መላኩ እና አማካዩ በኃይሉ ተሻገርን አስወጥተው በምትካቸው ሰኢድ አብዱልፈታህ እና ኃይሌ እሸቱን በማስገባት የአጥቂ ቁጥራቸውን ወደ ሶስት በማሳደግ በተቀሩት ደቂቃዎች ላይ በ4-3-3 ቅርፅ ይበልጥ አጥቅተው ለመጫወት ጥረት አድርገዋል፡፡ በ65ኛው ደቂቃ ላይም በጥሩ ቅብብል ወደ ግብ ያደረሱትን ኳስ ካሉሻ አልሀሰን በግሩም ሁኔታ በማስቆጠር የኤሌክትሪኮችን ተስፋ ማለምለም ችሎ ነበር፡፡ 
ከግቧ መቆጠር በኃላ ኤሌክትሪኮች የተከላካይ መስመራቸውን በይበልጥ ወደ መሀል በማስጠጋት እንደመጀመሪያው አጋማሽ ሁሉ የኳስ ቁጥጥር ብልጫን ዳግም መውሰድ ቢችሉም በተለይ የመሀል ሜዳ ተጫዋቾች በቁጥር በርከት ብለው በተመሳሳይ የሜዳ ክፍል በቅርብ ርቀት ተሰባስበው በመገኘታቸው የኳስ ቅብብሎቻቸው በአመዛኙ በጎንዬሽና በኃልዬሽ ብቻ ተገድቦ ወደ ጎል ለመድረስ ሲቸገሩ ተስተውሏል፡፡ 80ኛው ደቂቃ ላይ ዲዲዬ ለብሪ ከእጅ ውርወራ በረጅሙ የላከለትን ኳስ ተጠቅሞ ግርማ በቀለ ወደ ግብ የላከውን አስደንጋጭ ሙከራ ክሌመንበት ያዳነበት ኳስም ከጎሉ በኋላ ሊጠቀስ የሚችል ብተኛ ሙከራ ነበር። 

የጨዋታ የበላይነት የተወሰደባቸው ደደቢቶች በ85ኛው ደቂቃ ላይ በፈጣን ሽግግር ያገኙትን ኳስ አቤል ያለው አመቻችቶለት ጌታነህ ከበደ በጨዋታው ለራሱ ሁለተኛው እንዲሁም በውድድር ዘመኑ በአጠቃላይ አራተኛዋን ግብ አስቆጥሮ ጨዋታውም በደደቢት 3-1 አሸናፊነት ተጠናቋል። 

የአሰልጣኞች አስተያየት  
ብርሃኑ ባዩ – ኢትዮ ኤሌክትሪክ  

“የማይችል ቡድን ነው ያሸነፈን፡፡ እንደዚህ አይነት የወረደ እንቅስቃሴ አድርጎ ያሸነፈ ቡድን አይቼ አላውቅም፡፡ በተለይ በመጀመሪያው አጋማሽ ደደቢቶች ተመልካቾች ነበሩ፡፡” 

ንጉሴ ደስታ-ደደቢት 

” በመጀመሪያው አጋማሽ እነሱ ከአንድ ሳምንት እረፍት እንደመምጣታቸው ብልጫ ተወስዶብን ነበር፡፡ በሁለተኛው አጋማሽ የነበሩብን ክፍተቶች አርመን በመቅረብ ጨዋታውን አሸንፈን ልንወጣ ችለናል፡፡”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *