ሪፖርት | ጅማ አባ ጅፋር በአስገራሚ ወቅታዊ አቋሙ ገፍቶበታል

ከኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ ዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች መሀከል ጅማ ላይ ወልዋሎ ዓዲግራት ዩኒቨርሲቲን ያስተናገደው ጅማ አባጅፋር 3-0 በሆነ ውጤት አሸንፏል።

ቀደም ብሎ የከፍተኛ ሊግ ጨዋታ የተካሄደ በመሆኑ ምክንያት የሠዐት ሽግሽግ ተደርጎበት 45 ደቂቃዎችን ዘግይቶ በጀመረው ጨዋታው በባለሜዳዎቹ በኩል ያለፉትን 2 ጨዋታዎች ላይ የተጠቀሙበትን አሰላለፍ ይዘው  የገቡ ሲሆን በወልዋሎዎች ከቅዲስ ጊዮርጊስ ጋር ያለግብ ከተለያዩበት ጨዋታ ብርሃኑ አሻሞን በተስፋዬ ዲባባ ቀይረው ጨዋታውን ጀምረዋል።

በመጀመሪያው አጋማሽ የጨዋታውን ክፍለ ጊዜ ወልዋሎዎች ረዣዥም ኳሶችን በመጠቀም ለመጫወት የሞከሩ ሲሆን ከተከላካይ እና አማካይ መስመር ተሰላፊዎቻቸው ለከድር ሳሊህ እና ሙሉአለም ጥላሁን የሚላኩትን ረጃጅም የአየር ላይ ኳሶች በጅማ አባጅፋር ተከላካዮች በቀላሉ እየተጨናገፉ ውጤታማ መሆን ተስኗቸዋል። በተመሳሳይ ጅማ አባጅፋር በኩል ኳስን መስርተው ለመጫወት የሚያደረጉት ሙከራ በወልዋሎ አማካዮች እየታፈነ ቡድኑ ውጤታማ ቅብብሎችን ለማድረግ ተቸግሮ ታይቷል። በጨዋታው ላይ የጎል ሙከራ ለመመልከት ስምንት ደቂቃዎችን የፈጀ ሲሆን ሙከራውም ከጅማ አባጅፋሩ አጥቂ  ኦኪኪ አፎላቢ የተገኘ ነበር። በ12ኛው ደቂቃ ላይም በቀኝ መስመር በኩል ኦኪኪ ላይ በተሰራ ጥፋት ምክንያት ከአስራስድስት ከሀምሳው የቀኝ ጠርዝ ላይ ከሄኖክ ኢሳያስ ጋር በንክኪ የተጀመረውን የቅጣት ምት ኦኪኪ ሞክሮ የግቡን ቋሚ ታካ ወደ ውጭ ወጥታበታለች። ከዚህች ሙከራ በኃላ 25ው ደቂቃ ላይ ከዮናስ ገረመው የተሻገረለትን ኳስ ተመስገን ገ/ኪዳን የግብ ጠባቂውን መውጣት ተመልክቶ ቺፕ በማድረግ የመጀመሪያውን ግብ አስቆጥሯል። 

ከግቧ መቆጠር በኃላ ጅማ አባጅፋሮች ይበልጥ ተጭነው መጫወት የቻሉ ሲሆን በኦኪኪ እና በኤልያስ አተሮ አማካይነት ለግብ የቀረቡ ሙከራዎችን አድርገዋል። በ43ኛው ደቂቃ ኦኪኪ በጉዳት ምክንያት በሳምሶን ቆልቻ ተቀይሮ መውጣቱ ጅማዎችን ሊያዳክም ይችላል ተብሎ ቢጠበቅም የመጀመሪያው አጋማሽ መገባደጃ ላይ ዮናስ ገረመው ተመስገን ገ/ኪዳን ተጨዋቾችን አታሎ ያቀበለውን ኳስ አስቆጥሮ የቡድኑን መሪነት ወደ ሁለት ከፍ አድርጓል። ከግቧ መቆጠር በኃላም ዮናስ ደስታውን በሚገልጽበት ጊዜ ጉዳት አጋጥሞታል።

ከእረፍት መልስ ወልዋሎዎች በጨዋታው ላይ እብዛም ጥሩ እቅስቃሴ ሲያደርግ ያልታየው ከድር ሳሊህን በእዮብ ወ/ማርያም የቀየሩ ሲሆን ሁለተኛ የጉዳት ቅያሪ ለማድረግ የተገደዱት አባጅፋሮች ዮናስ ገረመውን በንጋቱ ገ/ስላሴ ተክተው ጨዋታቸውን ጀምረዋል። ዮናስ እና ኦኪኪ በጉዳት ከወጡ በኃላ ጅማዎች ቀዝቀዝ ብለው ታይተዋል። በአንፃሩ ወልዋሎች ሮቤልን በወግደረስ ቀይረው በማስገባት የተወሰደባቸውን የጨዋታ ብልጫ ማስመለስ የቻሉ ሲሆን በ55 ደቂቃ ፕሪንስ ሰቨሪንሆ ከርቀት አክርሮ የመታው ኳስ በግቡ አግዳሚ የተመለሰበት አኳኃን ለቡድኑ እጅግ የሚያስቆጭ አጋጣሚ ነበር። በመቀጠልም ወልዋሎዎች በወግደረስ ፣ በሙሉአለም እንዲሁም በፕሪንስ ደጋግመው የባለሜዳዎቹን በር ቢፈትሹም  ወደ ግብነት ሊቀየሩ የቻሉት ኳስ ግን አልነበረም። 

በጨዋታው ላይ ጥሩ እንቅስቃሴ ሲያደርግ የነበረው ተመስገን 73 ደቂቃ በጉዳት ከወጣ በኃላ የወልዋሎዎች ጥቃት ይበልጥ የጨመረ ቢሆንም ግብ ማስቆጠር የቻሉት ግን ጅማዎች ነበሩ። የጨዋታው መደበኛ  ደቂቃዎች ተጠናቀው በጭማሪው ሰአት በመልሶ ማጥቃት ከእንዳለ ደባልቄ የተሻገረለትን ኳስ በመጠቀም ተቀይሮ የገባው  ንጋቱ  ገ/ስላሴ ለጅማ 3ኛውን ግብ አስቆጥሮ የቡድኑን አሸናፊነት አረጋግጧል። በጨዋታው ሶስት የጅማ አባ ጅፋር ተጨዋቾች በጉዳት ተቀይረው የወጡ ሲሆን ከጨዋታ በፊት በቂ የሟሟቂያ ሰአት ባለመኖሩ የተጎዱትንን ጨምሮ ሌሎች ተጨዋቾችም ሲቸገሩ መታዘብ ችለናል።

የአሰልጣኞች አስተያየት

አሰልጣኝ ገ/መድህን ኃይሌ – ጅማ አባ ጅፋር

” በጊዜ ጎል ማግባታችን ጠቅሞናል። በጉዳት ምክንያት የወጡብን ሦስት ተጨዋቾች የጨዋታውን እንቅስቃሴ ከዕረፍት መልስ እንዲቀዛቀዝ አድርገውት ነበር። በአጠቃላይ ዳዳኝነቱም ሆነ የጨዋታው እንቅስቃሴ ጥሩ ነው። እኔ ደስተኛ ነኝ። ”

አሰልጣኝ ብርሀኔ ገ/እግዚያብሔር – ወልዋሎ ዓ.ዩ

“ሙሉ ጨዋታውን ብልጫ ተወስዶብናል። ጅማ አባ ጅፋሮች ያገኟቸውን የግብ ዕድሎች በአግባቡ በመጠቀማቸው አሸንፈው ሊውጡ ችለዋል።”

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *