​ከፍተኛ ሊግ [ምድብ ሀ] – አአ ከተማ ሰበታን በማሸነፍ መሪነቱን ተረክቧል

በከፍተኛ ሊግ የ7ኛ ሳምንት ጨዋታዎች አአ ከተማ ወደ መሪነቱ ሲመለስ ባህርዳር ከተማ እና አክሱም ከተማም ድል ቀንቷቸዋል።

በሰበታ ስታድየም ላይ በምድቡ አናት ላይ የሚገኙት ሰበታ ከተማ እና አዲስ አበባ ከተማ ያደረጉት ጨዋታ በእንግዳው አአ ከተማ 1-0 አሸናፊነት ተጠናቋል።
ቀዝቀዝ ባለ እንቅስቃሴ በተጀመረው በዚህ ጨዋታ በ16ኛው ደቂቃ በፀጋዬ ከፍያለው የመጀመሪያ ሙከራ የተደረገ ቢሆንም በሰበታ ግብ ጠባቂ በቀላሉ ድኖበታል፡፡
በሁለቱም መስመሮች የማጥቃት ጫና ሲያሳድሩ የነበሩት አዲስ አበባዎች በ21ኛው ደቂቃ ላይ እሱባለው ሙሉጌታ ከቀኝ መስመር ያሻገረውን ኳስ የሰበታ ግብ ጠባቂ ዘላለም ሊካሳ ስህተት ታክሎበት በነፃ አቋቋም ላይ የነበረው ፍቃዱ አለሙ በግንባሩ በመግጨት ወደ ግብነት ለውጦታል። በ45ኛው ደቂቃ ላይ ፀጋዬ ከፍያለው በግምት 35 ሜትር ርቀት አክርሮ የመታው እና የግቡን አግዳሚ የገጨበት ሙከራ የአአ ከተማን መሪነት ልታሰፋ የምትችል ነበረች።
ከዕረፍት መልስ ሰበታ ከተማዎች ሙሉ ለሙሉ ተጭነው የተጫወቱ ሲሆን ውጤቱን ግን መቀልበስ ሳይቻላቸው ቀርቷል። በተደጋጋሚ በግራ መስመር ኳስ ገፍቶ በመግባት የአዲስ አበባ ከተማ ተከላካይ ሲረብሽ የነበረው ሄኖክ ካሳሁን በ78ኛው ደቂቃ በግንባሩ ገጭቶ የሞከረውና የአዲስ አበባ ከተማው ግብ ጠባቂ ፍሬዘር ያመከነው ኳስ ሰበታዋችን ያስቆጨ ሙከራ ነበር፡፡

አዲስ አበባ ከተማ ጨዋታውን ማሸነፉን ተከትሎ አንድ ተስተካካይ ጨዋታ እየቀረው የምድቡ መሪነትን ከሰበታ ከተማ ተረክቧል።

በሌሎች የምድቡ ጨዋታዋች ባህርዳር ከተማ ፌዴራል ፖሊስን አስተናግዶ 5-1 በሆነ ውጤት አሸንፏል። የቀድሞ የፋሲል ከተማ አጥቂ ሙሉቀን ታሪኩ ሁለት ጎሎችን ሲያስቆጥር ወሰኑ አሊ፣ ሳላአምላክ ተገኝ እና ዳግማዊ ቀሩዎቹን ጎሎች አስቆጥረዋል።
ሱሉልታ ላይ ሱሉልታ ከተማ በኤርሚያስ ዳንኤል ብቸኛ ጎል ነቀምት ከተማን 1-0 ማሸነፍ ችሏል። የካ ክፍለከተማ ከ ደሴ ከተማ 1-1 ሲለያዩ ከሳምንቱ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል የነበረው የሽረ እንደዳስላሴ እና ለገጣፎ ጨዋታ በተመሳሳይ 1-1 አቻ ተጠናቋል። ልደቱ ለማ በቀድሞ ክለቡ ላይ አስቆጥሮ ሽረን ቀዳሚ ቢያደርግም ዳዊት ቀለምወርቅ በቅጣት ምት ግብ ለገጣፎን አቻ አድርጓል። በጨዋታው የሽረ ደጋፊዎች ከመደበኛው የጨዋታ ክፍለ ጊዜ በኋላ የተጨመረው ደቂቃ ሳይጠናቀቅ ፊሽካ ተነፍቷል በሚል ከዳኞች ጋ ውዝግብ ውስጥ ገብተዋል፡፡

መድን ሜዳ ላይ ወሎ ኮምቦልቻን ያስተናገደው መድን ደግሞ ያለ ግብ አቻ ሲለያይ ቅዳሜ በዚህ ምድብ በተደረገ ጨዋታ ባህርዳር ላይ አውስኮድ ከቡራዩ ከተማ በተመሳሳይ ያለ ጎል በአቻ ውጤት ተለያይተዋል፡፡ ሱሉልታ ያያ ቪሌጅ ላይ ኢኮስኮ በአክሱም ከተማ 1-0 ሲሸነፍ በሁለተኛው አጋማሽ የመገባደጃ ደቂቃዎች ላይ ኢኮስኮ ፍፁም ቅጣት ምት ተከልክለናል በሚል ክስ ያስመዘገቡ ሲሆን በተጫዋቾች መካከልም ውዝግቦች ተከስቶ ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *