የኢትዮጵያ ፕሪምየር ሊግ 9ኛ ሳምንት – የሰኞ ጨዋታዎች ቅድመ ጨዋታ ዳሰሳ

ከትናንት በስትያ ጅምሮ ሲደረጉ የቆዩት የሊጉ የዘጠነኛ ሳምንት ጨዋታዎች ዛሬ ወልድያ አርባምንጭ ከተማን እንዲሁም ወላይታ ድቻ ኢትዮ ኤሌክትሪክን በሚያስተናግዱባቸው ጨዋታዎች ይገባደዳሉ። ሶከር ኢትዮጵያም ሁለቱን ጨዋታዎች አስመልክቶ የሚነሱ ነጥቦችን እንደሚከተለው ታስነብባችኃለች። 

ወልድያ ከ አርባምንጭ ከተማ

አመቱን በድል ጀምሮ የነበረው ወልድያ አሁን ላይ በወራጅ ቀጠና ውስጥ ለመቀመጥ ተገዷል። ሆኖም ቡድኑ ከዛሬው ጨዋታ ውጪ እጁ ላይ ሁለት ተስተካካይ ጨዋታዎችን መያዙ ደረጃውን በፍጥነት ለማሻሻል የሚችልበት ዕድል ይኖረዋል። አምና በሜዳው የአንድ ጨዋታ ሽንፈት ብቻ ያስተናገደው ወልድያ በዚህ ጨዋታ ከሶስተኛው ሳምንት በኃላ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ሜዳው የሚመለስ በመሆኑ ውጤት ይዞ በመውጣት ደረጃውን የማሻሻል ግምት ያሰጠዋል። ከአሰልጣኝ ፀጋዬ ኪዳነማርያም ስንብት በኃላ በምክትል አሰልጣኙ በረከት ደሙ እየተመራ ወደ ሜዳ የሚገባው አርባምንጭ ከተማ ሁሉንም ጨዋታዎች አድርጎ የሰበሰበው ነጥብ ግን ከተጋጣሚው ጋር ዕኩል ነው። በተለይ ባለፉት ሁለት ጨዋታዎች ስድስት ግቦችን አስተናግዶ ለሽንፈት መዳረጉ ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ይከተዋል። ጨዋታውም ቡድኑ በጥቂቱም ቢሆን ከወራጅ ቀጠናው ለመውጣት የሚያደርገው ይሆናል።

ወልድያ ከኢትዮጵያ ቡና ጋር በነበረው ጨዋታ አማረ በቀለን እና ብሩክ ቃልቦሬን በቀይ ካርድ ማጣቱ የሚታወስ ነው። ባሳላፍነው ሳምንት አጋማሽም ፌዴሬሽኑ ብሩክ ቃልቦሬ ላይ የአራት ጨዋታዎች ቅጣት ሲያስተላልፍ አማረ በቀለን ደግሞ ለስድስት ወራት ቀጥቷል። ከሁለቱ ተጨዋቾች በተጨማሪ ሰለሞን ገ/መድህንም ከበድ ያለ ጉዳት እንዳጋጠመው ሰምተናል። አንድነት አዳነን ከቅጣት መልስ በሚያገኘው አርባምንጭ በኩል ደግሞ ወንድሜነህ ዘሪሁን ፣ ወንደሰን ሚልኪያስ ፣ አማኑኤል ጎበና እና ተሾመ ታደሰ ጉዳት ላይ በመገኘታቸው ጨዋታው የሚያልፋቸው ይሆናል።

ሊጠናቀቅ አንድ ሳምንት በቀረው የታህሳስ ወር ሁለት ጨዋታዎችን ብቻ ያደረገው ወልድያ ሁኔታው የተጨዋቾቹ የጨዋታ ብቁነት ላይ የሚኖረው ተፅዕኖው ከፍ ያለ ነው። ሆኖም ሁለተኛው ጨዋታ ባሳለፍነው ሳምንት መካሄዱ ቡድኑን ወደ ነበረበት የውድድር መንፈስ እንደሚመልሰው መናገር ይቻላል። የወልድያ ከወገብ በላይ ያለው ስብስብ ውጤትን የመቀየር አቅም ያለው ቢሆንም አጥቂዎቹን እየተጠቀመበት ያለው መንገድ በቀላሉ ግብ የማያስቆጥር ቡድን እንዲሆን ያደረገው ይመስላል። በተለይ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ፍፁም ገ/ማርያምን በግራ መስመር አማካይነት ሚና ላይ ሲጠቀም የተስተዋለው ወልድያ አጥቂው ከተቃራኒ የግብ ክልል ርቆ እንዲጫወት ማድረጉ ዕድሎችን እንዳይጠቀም ሲያደግ የተጨዋቹ የመከላከል ባህሪ እምብዛም በመሆኑ ደግሞ መስመሩ ለጥቃት ሲጋለጥ ተስተውሏል። ከዚህ ውጪ የብሩክ ቃልቦሬ እና ሰለሞን ገ/መድህን አለመኖር መሀል ሜዳ ላይ የሚፈጥረው ክፍተት ቡድኑ ለአንዷለም ንጉሴ በቀጥታ በሚደርሱ ኳሶች ላይ ተመስርቶ እንዲጫወት በር ይከፍታል። አርባምንጭ ከተማ ከአሰልጣኝ ለውጡ ጋር ተያይዞ የተለየ አቀራረብን ይዞ ሊገባ የሚችል ቢሆንም እንደተጋጣሚው ሁሉ በፊት አጥቂው ላኪ ሳኒ ላይ ተመስርቶ ሜዳ እንደሚገባ ይጠበቃል። በመሆኑም ጨዋታው በጉዳት እና ቅጣት ሳቢያ ቁልፍ የአማካይ ክፍል ተጨዋቾቻቸውን ያጡ ቡድኖችን የሚያገናኝ በመሆኑ እና ሁለቱም በተመሳሳይ የአንድ የፊት አጥቂ ተጠቃሚዎች በመሆናቸው እነዚህን ተጨዋቾች የእንቅስቃሴዎቻቸው የመጨረሻ መዳረሻ በማድረግ እንደሚጫወቱ ይገመታል። በዚህ መሰረትም አንዷለም ንጉሴ እና ላኪ ሳኒ በተቃሪኒ ቡድን የተከላካይ መስመር ፊት የሚኖራቸው እንቅስቃሴ ጨዋታው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ ከፍተኛ እንደሚሆን ይጠበቃል።


ወላይታ ድቻ ከ ኢትዮ ኤሌክትሪክ

ሁለቱን ተጋጣሚዎችን የሚያመሳስላቸው ሁለቱም በአሰልጣኝ ለውጥ ላይ መሆናቸው ነው። በተለይ ወላይታ ድቻ ጨዋታው ከዘጠኝ አመታት በኃላ ከአሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ ጋር ከተለያየ በኃላ የሚያደርገው የመጀመሪያ ጨዋታ መሆኑ ለየት ያለ መንፈስ ይፈጥራል። ኢትዮ ኤሌክትሪክም አሰልጣኝ ብርሀኑ ባዩን ካሰናበቀ በኃላ በሳምንቱ አጋማሽ ኢትዮጵያ ቡናን በግብ ጠባቂዎች አሰልጣኝ ሀላፊነቱ በሚታወቀው አሰልጣኝ ቅጣው ሙሉ መሪነት ካሸነፈ በኃላ ዛሬ በአዲሱ አሰልጣኝ አሸናፊ በቀለ እንደሚመራ ይጠበቃል። ሶስት ተከታታይ ሽንፈቶችን ያስተናገዱት ድቻዎች በደረጃ ሰንጠረዡ ግርጌ ላይ ሲገኙ ይህን ጨዋታ የማሸነፍ ግዴታ ውስጥ ገብተዋል። በሳምንቱ አጋማሽ ካገኘው ድል በኃላ ደረጃውን በትንሹም ቢሄን ያሻሻለው  ኢትዮ ኤሌክትሪክም ከረጅም ጊዜያት በኃላ ሁለት ተከታታይ ጨዋታዎችን የማሸነፍ ታሪክ ለመፃፍ ብሎም ክለቡ ከለመደው የወራጅ ቀጠና ለመራቅ የዛሬውን ጨዋታ አሸንፎ መመለስ ይኖርበታል።

ፀጋዬ ብርሀኑ እና እርቅይሁን ተስፋዬ ከወላይታ ድቻ በኩል ጉዳት ላይ የሚገኙ ተጨዋቾች ሲሆኑ አምበሉ አዲስ ነጋሽን ከቅጣት መልስ የሚያገኘው ኢትዮ ኤሌክትሪክ ሁለተኛውን አምበል ዐወት ገ/ሚካኤልን እንዲሁም ኃይሌ እሸቱን እና ቢንያም አሰፋን በጉዳት ምክንያት ያጣል።

በደደቢቱ ጨዋታ የመሻሻል ምልክትን መስጠት የጀመረው ኢትዮ ኤሌክትሪክ በኢትዮጵያ ቡናው ጨዋታ ላይ ወደ ትክክለኛው ቅርፅ የመጣ ይመስላል። ከሁሉም በላይ የካሉሻ አልሀሰን ሁነኛ  ቦታ ማግኘት ለቡድኑ የማጥቃት ሂደት ትልቅ ጉልበት ሆኖታል። ተጨዋቹ ደደቢት እና ቡና ላይ ያስቆጠራቸውን ግቦች ስንመለከት ሁለቱም ከፊት አጥቂዎቹ ጀርባ በመነሳት በተከላካዮች መሀል በተፈጠረ ክፍተት መሀል በድንገት በመገኘት እና ያገኛቸውን ዕድሎች በአግባቡ በመጨረስ ያስቆጠራቸው ነበሩ። ይህ የተጨዋቹን ከኳስ ውጪ ክፍተቶችን የማየት እና ዕርጋታ የተሞላበት አጨራረስ በዛሬው ጨዋታ ለድቻ ተከላካዮች ራስ ምታት እንደሚሆን ይጠበቃል። ወላይታ ድቻ አሰልጣኝ መሳይ ተፈሪ በሚታወቁበት በሶስት ተከላካዮች በሚጀምር አሰላለፍ መጠቀም የሚቀጥል ከሆነ ቡድኑ የኢትዮ ከኤሌክትሪክ ሁለት የፊት አጥቂዎች በተጨማሪ የካሉሻን ቀጥታኛ እንቅስቃሴን ለመግታት ሁለቱን አማካዮቹን ኃይማኖት ወርቁን እና አብዱልሰመድ ዓሊን ወደ ኃላ ስቦ እንደሚጫወት ይጠበቃል። በተመሳሳይ እሳቤ በጨዋታው የድቻ የመስመር ተመላላሾች እሸቱ መና እና ያሬድ ዳዊት ኢትዮ ኤሌክትሪክ በካሉሻ እና በሔኖክ ካሳሁን መሀል ከሚጠቀማቸው ጥላሁን ወልዴ እና በሀይሉ ተሻገር ጋር የሚገናኙባቸው ቦታዎች ጨዋታውን የመወሰን ሀይል ይኖራቸዋል። በወላይታ ድቻ በኩል እስካሁን ቡድኑ ካስቆጠራቸው አራት ግብምች የሶስቱ ባለቤት የሆነው ጃኮ አራፋት ወደ ኃላ በመሳብም ሆነ የጎንዮምሽ ሩጫዎችን በማድረግ በተጋጣሚ ተከላካዮች ላይ የሚፈጥረው ግርታ ተደጋጋሚ ስህተት ሲሰራ በሚታየው የኢትዮ ኤሌክትሪክ የፊት መስመር መሀል ክፍተቶችን ለማግኘት ዕድል እንደሚሰጠው ይጠበቃል።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *