ዮርዳኖስ አባይ በክብር ይሸኛል

በኢትዮዽያ እግርኳስ ታሪክ ጎልተው ከወጡ ግብ አነፍናፊዎች አንዱ የነበረው ዮርዳኖስ አባይ ከየካቲት ወር ጀምሮ በሚዘጋጁ የተለያዩ ፕሮግራሞች አማካኝነት በክብር እንደሚሸኝ ዛሬ ከቀኑ 08:00 ጀምሮ በዋቢ ሸበሌ ሆቴል በተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ ይፋ ተደርጓል። ዮርዳኖስ አባይ ፣ ፌዴሬሽኑን በመወከል አቶ ሰለሞን ገብረስላሴ ፣ የኢትዮዽያ ኩላሊት በጎ አድራጎት ማህበር ፕሬዝደንት እንዲሁም የመሸኛ አዘጋጅ ኮሚቴ አባል በተገኙበት ነው ጋዜጣዊ መግለጫው የተሰጠው።

የፌዴሬሽኑ ጊዜያዊ ዋና ፀኃፊ አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ ፌዴሬሽኑን በመወከል ባደረጉት ንግግር እጅግ ከምናከብራቸው ተጫዋቾች መካካል ዮርዳኖስ አባይ አንደሆነ ገልፀው ፌዴሬሽኑ ለጠየቃቸው ጥያቄዎች ሁሉ በቂ የሆነ ምላሽ እንደሚሰጥና በሚያስፈልገው ነገሩ ሁሉ ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል። ዮርዳኖስ ለሚመጣው ትውልድ የሚቀር የተለያዩ የሽኝት ዝግጅቶችን ማዘጋጀቱ ለሌሎች ተጨዋቾች ምሳሌ የሚሆን ተግባር መሆኑንም ተናግረዋል።

የኢትዮዽያ ኩላሊት እጥበት የበጎ አድራጎት ማህበር ዋና ስራ አስኪያጅ በበኩላቸው ታዋቂ ሰዎች ለሚዲያ ራሳቸውን ለማስተዋወቅ ካልሆነ በስተቀር ስም እና ዝናቸውን ለበጎ ተግባር ሲጠቀሙበት እንደማይሰተዋል ጠቁመው ዮርዳኖስ አባይ በዚህ ደረጃ ለበጎ አላማ ይህን ማድረጉ ክብር የሚገባውና ለሌሎቹም ትልቅ አርያነት ያለው ተግባር መሆኑን ገልፀዋል።

በመቀጠል የአዘጋጅ ኮሚቴው አባል እንደተናገሩት ዮርዳኖስ በኢትዮዽያ እግርኳስ ውስጥ ትልቅ አሻራ ጥለው ካለፉ ስመጥር ተጨዋቾች መካከል አንዱ በመሆኑ እሱን የእግርኳስ ህይወቱ ማብቅያ አስመልክቶ የተለያዩ ፕሮግራሞች እንደተዘጋጁ  ገልፀው ዝግጅቶቹ በአአ እና ድሬደዋ ከተሞች ላይ ከየካቲት ወር ጀምሮ እንደሚደረግ አብራርተዋል።

* በአአ ተጫውቶ ባለፈባቸው ኢትዮ ኤሌክትሪክ እና ኢትዮዽያ ቡና መካከል የወዳጅነት ጨዋታ ሲደረግ ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ በተጨዋችነት ዘመኑ አብረውት የተጫወቱት ተጨዋቾች ጋር ለሁለት የተከፈለ የወዳጅነት ጨዋታ ይደረጋል።

* ለ1 ሰአት ከ15 ደቂቃ የፈጀ በእግርኳስ ህይወቱ ዙርያ ዘጋቢ ፊልም ተዘጋጅቷል።

* በ8844 አጭር የፅሁፍ መልዕክት A በመጫን ከሚገኘው ገቢ በተጨማሪ በሌሎቹ የመሸኛ ፕሮግራሞች የሚገነው ገቢ ለኩላሊት እጥበት ህክምና በጎ አድራጎት ማህበር ይውላል።

* በገነነ መኩርያ (ሊብሮ) አዘጋጅነት የዮርዳኖስ አባይን የህይወት ታሪክ የሚተርክ መፅሐፍ እየተዘጋጀ የሚገኝ ሲሆን በየካቲት ወር ተጠናቆ ሊመረቅ ይችላል።

*በትውልድ ከተማው ድሬደዋ የተለያዩ ፕሮግራሞች የሚኖሩ ሲሆን በርካታ ህዝብ ይሳተፍበታል ተብሎ የሚጠበቅ የጎዳና ላይ ሩጫ የዝግጅቱ አካል ነው።

በማስከተል ንግግር ያደረገው ዮርዳኖስ አባይ ፈጣሪ ለዚህ ጊዜ ስላደረሰው አመስግኖ የነዚህ ሁሉ ስኬቶች ምክንያት የበርካታ ሰዎች እገዛ ድምር ውጤት መሆኑን ገልጿል። “የሽኝት ፕሮግራሙ የእኔ ብቻ መሆን የለበትም። አስተማሪ መሆን እንዳለበት በማሰብ የበጎ ተግባራት የእርዳታ ፕሮግራም እንዲኖረው  እና ለሚመጣው ትውልድ ሊቀር የሚችል ፕሮግራሞች ታስበዋል። ወደፊት ለሀገር የሰሩ ሰዎች በትልቅ ፕሮግራም በክብር እንዲሸኙ በማሰብ የሽኝት ፕሮግራሙ ተዘጋጅቷል። ” ያለው ዮርዳኖስ ድጋፍ ላደረጉለት አካላት በሙሉ ልባዊ ምስጋና አቅርቦ በቀጣይ ለሚኖረው ዝግጅት መሳካት ሁሉም አካላት ጎኑ እንዲሆኑ ጥሪውን አስተላልፏል።

ዮርዳኖስ አባይ የተጨዋችነት ዘመን

ከ1989 – 1991 ከድሬደዋ ጨርቃጨርቅ ቢ እስከ ዋናው ቡድን

ከ1992 – 1995 በኢትዮ ኤሌክትሪክ

በ1995 በኢትዮዽያ ቡና

ከ1996 – 2006 በየመኑ አልሳከር ክለብ

2007 ሁለተኛው ዙር ኢትዮ ኤሌትሪክ

2008 ድሬደዋ ከተማ ፣ ድሬደዋ ፖሊስ ፣ ናሽናል ሴሜንት የተጫወተ ሲሆን ከዚህ በተጨማሪ በቤልጅየሙ አንደርሌክት በ1995 የሙከራ ጊዜ አሳልፏል።

በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በ1993 የአፍሪካ ወጣቶች ዋንጫ 4ኛ በመውጣት በአርጀንቲና አስተናጋጅነት በተዘጋጀው የአለም ታዳጊዎች ዋንጫ ላይ ተሳታፊ ከመሆኑ ባሻገር በሴካፋ ፣ በአፍሪካ ዋንጫ ማጣርያ ለኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን አገልግሎት መስጠት ችሏል።

የዮርዳኖስ አባይ ስኬቶች

በ1993 በ24 ጎል ከፍተኛ ጎል አግቢ

በ1994 በ21 ጎል ከፍተኛ ጎል አግቢ

በ1995 በ14 ጎል ከፍተኛ ጎል አግቢ በመሆን ለተከታታይ ሦስት አመት ኮከብ ጎል አግቢ ክብርን ተቀዳጅቷል ።

በየመን 3 ጊዜ ኮከብ ጎል አስቆጣሪ ሲሆን የክለቡ አልሳክር ብቻ 8 ጊዜ ኮከብ ተጨዋች በመባል ተሸልሟል ።

በ1995 በኢትዮዽያ ብሔራዊ ቡድን በአሰልጣኝ አስራት ኃይሌ በፀበተመራውና ለመጀመርያ ጊዜ ከሀገር ውጪ በተስናገደ የሴካፋ ውድድር ዋንጫ ይዞ በተመለሰው ስብስብም ወሳኝ ተጫዋች ነበር።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *