​ፋሲል ሮበርት ሴንቶንጎን ከቡድኑ አሰናበተ

ፋሲል ከተማ ለዘንድሮ የውድድር አመት በሊጉ  ጠንካራ ተፎካካሪ እንዲሆን እና ውጤታማ ጉዞ እንዲያደርግ በርካታ ተጫዋቾችን ከሀገር ውስጥ እና ከውጭ ማስመጣት የቻለ መሆኑ ይታወቃል።

በክረምቱ የዝውውር ወቅት አፄዎቹን ከተቀላቀሉ 5 የውጪ ዜጎች መካከል አንዱ የሆነው ዩጋንዳዊው አጥቂ ሮበርት ሴንቶንጎ ከ2006 ከቅዱስ ጊዮርጊስ ያልተሳካ አጭር ቆይታ በኋላ ዳግም ወደ ኢትዮዽያ በመመለስ ለፋሲል ከነማ ፊርማውን ቢያኖርም በሊጉ የዘጠኝ ሳምንት መርሀ ግብር ላይ ከተቀያሪ ወንበር በዘለለ በአንድም ጨዋታ ላይ ተሰልፎ ሳይጫወት ባሳየው ተደጋጋሚ ያልተገባ ባህሪ ምክንያት ክለቡ በወሰደው የዲሲፒሊን እርምጃ ምክንያት ወደ ሀገሩ ማቅናቱ ሰምተናል።

ከዚህ ቀደም በክረምቱ የዝውውር መስኮት ናይጄርያዊው የመስመር አጥቂ ክርስቶፈር አሞስ ኦቢ የሙከራ ጊዜውን በተሳካ ሁኔታ አጠናቆ እንደፈረመ ቢነገርለትም ብዙ ሳይቆይ ምክንያቱ ባልታወቀ ሁኔታ ከክለቡ ጋር መሰናበቱ ይታወሳል።
ከቅርብ አመታት ወዲህ ከፍተኛ በሆነ ወጪ  እየወጣባቸው ከውጭ የሚመጡ አፍሪካውያን ተጨዋቾች ከተቀያሪ ወንበር ከመቀመጥ ያላለፈ ለክለቦቹ በቂ የሆነ አገልግሎት ሳይሰጡ ወደመጡበት ሲመለሱ መመልከት የተለመደ እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ ክለቦች ቆም ብለው ሊያስቡበት እንደሚገባ ብዙሀኑ የስፖርት ቤተሰቡ የሚያነሳው ጥያቄ እየሆነ መጥቷል ።

በሌላ ዜና ፋሲል ከተማ በሁለተኛው ዙር ባሉበት ክፍተቶች ላይ እራሱን ለማጠናከር በማሰብ ከሀገር ውስጥም ከውጭ ተጫዋቾችን ለማስፈረም በከፍተኛ ሁኔታ እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ የሰማን ሲሆን በተለይ  ከሌሎች ክለቦች ጋር በመፎካከር ጋቶች ፓኖምን ለማስፈረም እየተንቀሳቀሰ እንደሆነ ከክለቡ አካባቢ ባገኘነው መረጃ ለማወቅ ችለናል ።

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *